የቡና ልማትና ግብይትን አስመልክተው የሚወጡ ዓለም-አቀፍ ህጎችን አክብሮ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

የቡና ልማትና ግብይትን አስመልክተው የሚወጡ ዓለም-አቀፍ ህጎችን አክብሮ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 07/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቡና ልማትና ግብይትን አስመልክተው የሚወጡ ዓለም-አቀፍ ህጎችን አክብሮ መስራት እንደሚገባ የካፋ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት መምሪያ አሳሰበ።

የአውሮፓ ህብረት “ከደን ጭፍጨፋ ነፃ የምርት አቅርቦት” በሚል ያወጣውን ህግ አስመልክቶ ከካፋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ የግብርና ስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው።

ስልጠናው በካፋ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት መምሪያ አዘጋጅነት በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እና በቦንጋ የትምህርት ኮሌጅ እየተሰጠ ይገኛል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጋዎ አባመጫ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ከዓለም አቀፍ ህጎች ጋር የሚጣጣም የቡና ልማት ስራን ማከናወን አስፈላጊ በመሆኑ ስልጠናው እንደሚሰጥ ጠቁመው፥ የቡና ልማትና ግብይትን በተመለከተ የሚወጡ ዓለም-አቀፍ ህጎችን አክብሮ መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።

የአውሮፓ ህብረት “ማንኛውም ምርት ሲመረት የተፈጥሮ ሀብት ላይ ጉዳት መድረስ የለበትም” የሚል ህግ ማውጣቱን ጠቁመው፥ ለአውሮፓ ገበያ ከሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ቀዳሚው፣ ከካፋ ዞን ህዝብ ማህበራዊ ህይወትና ታሪክ ጋር የተቆራኘ፣ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም ከፍተኛ የሆነውን ቡና ለዓለም ገበያ በሚመጥን መንገድ ማምረት ይገባል ነው ያሉት።

ህጉን ከዓለም-አቀፍ፣ ከሀገራዊና ከአካባቢያዊ ነባራዊ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ጋር በተናበበ መንገድ ማክበርና የእውቀት ሽግግር ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ለሶስት ቀናት የሚዘልቀው ይህ ስልጠና የአርሶ-አደሮችን የቡና ማሳ ልኬት እና መረጃ አያያዝን፣ የአውሮፓ ህብረት ህግና መመሪያን፣ መረጃን በዲጂታል አሰራር መያዝን እና ሌሎችን ጉዳዮች በሚመለከት የጽንሰ-ሀሳብና የተግባር ስልጠናዎች የሚሰጡበት ነው።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን