“አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል”

“አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል”

በፈረኦን ደበበ

ነገሮች ሲበላሹ መያዣ መጨበጫ ማጣቷን ነው የግብጽ ሰሞንኛ እንቅስቃሴ የሚያሳየው፡፡ ፍላጎት ያለማሳካት ብቻ ሳይሆን ከሰው ምክንያታዊ አስተሳሰብ የወጣ ተግባር መፈጸሟ በኃጢአት መንገድ የመሰማራቷ ግልጽ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ያለችው “ነይ ከአካባቢ ተፈጥሯዊ ጸጋ አብረን እንቋደስ” እንጂ መተነኳኮል ይቅር ነበር፡፡ በምላሹ ግን ግብጽ የክፋት መንገድን በመምረጥ ሤራዋን ማጧጧፏ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ የሚለውን ቃል ሁሉ ያፋልሳል።

አዎን ሰው ቃሉን ካላከበረና በእምቢተኝነት አቋሙ ከቀጠለ ምን ይሄ ብቻ እስከ አዕምሮ መቃወስ የሚያደርስ ጭንቀት እንዴት ሳይገጥመው ይቀራል ምክንያቱም ህግ ካፋለሰና ለዚህ ንስሀ ካልገባ በቀር ቅጣቱ ወደር የለሌው ስለሚሆን፡፡

የግብጽ ባለሥልጣናት እስካሁን ከፈጸሙትና ካደረጉት ከንቱ መፍጨርጨር ሳይማሩ በመጨረሻው 12ኛው ሰዓት ላይ ማክረራቸው ለትዝብት ሲዳርጋቸው በአሁኑ ጊዜ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከዓለም ማህበረሰብ ጋር ወደሚናቆሩበት መንገድ እየተጓዙ ናቸው፡፡

ከዚህ ለማምለጥ ብለው ሰሞኑን የዘረጉት መሥመር የባሰ ገደል ውስጥ ከተታቸው እንጂ ምንም የተሻለ ነገር አላስገኘላቸውም፡፡ ከክፋትም ፈጣሪ ይሰውረን!

ሰሞኑን ምን ታይቶ ነው እንዲህ እንዲባል ያስገደደው ከተባለም በእርግጥ የሀገራችን ታሪካዊ ጠላት የሆነችው ግብጽ ሳይሆን እሷ ዓላማዬን ማሳካት ያስችለኛል ብላ የምትደግፈው ጽንፈኛ ቡድንንና ጀሌዎች፣ እንዲሁም ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆነው አይዞህ በሚሉ ወገኖቹ ላይ ስኬታማ ወታደራዊ እርምጃ መወሰዱ ነው፡፡

እስከ መጨረሻው ድረስ በተለያዩ ዘዴዎች የጸጥታ ኃይሉን እየሸወዱና ውስጥ ድረስ ዘልቀው የመንግሥትና የህዝብ ንብረት ማውደማቸው ለወዳጅ ተስፋ አስቆራጭ መስሎ ነበር፡፡ ይህ ነው የሚባል የፖለቲካ ዓላማ ሳይኖረው በእጁ በያዘው የጦር መሣሪያ ብቻ የተማመነው ራሱን “ፋኖ” ብሎ የሚጠራው ኃይል ግጭት በመቀስቀስ በክልሉ ንጹሀን ዜጎች እንዲጎዱና የመንግሥት ሀብትና ንብረትም በከንቱ እንዲወድም አድርጓል፡፡

የሠላም ትሩፋቶችን እየተቋደሰ፣ ህይወቱን ብሩህ ለማድረግ የሚጣጣረው አርሶ አደርና ሠራተኛውን ህዝብ አሸብሯል፤ ወንድም ከሆነው ህወሀትና የኤርትራ መንግሥት በሚያገኘው ድጋፍ፡፡

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቅርቡ ከሀገራቸው መገናኛ ብዙሀን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ መንግሥት በቡድኑ ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አምርረው መቃወማቸው የዚህ ግልጽ ማሳያ ሲሆን ሰሞኑን ወደ መቀሌ በመሄድ ቡድኑ ከህወሀት ጋር ተወያይቷል መባሉም ያለውን ዝምድና በግልጽ ያሳያል፡፡

“የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚለው መርህ የሁሉም አባት ከሆነችውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአሜሪካንን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ማማለል የቻሉት እነዚህ ቡድኖች በእርግጥ ሀገራችንን ለማተራመስ አመቺ ሁኔታ መፍጠር እንደቻሉ ነው በተከታታይ ሰጠን በሚሏቸው መግለጫዎች ማረጋገጥ የቻሉት፡፡

ሂደቱ ያለመሳካቱ ግን ሰሞኑን ግብጽም ሆነ የቡድኑ ጀሌዎች የማይመስል መግለጫ እንዲሰጡ አስገድዷቸዋል፡፡ ሰሞኑን የመንግሥት ሀብትና ንብረት ዘርፈው አቃጥለው ነበር የተባለው ዜና ውሎ ሳያድር በተለያዩ ግንባሮች የደረሰበትን ሽንፈት አሳይቷል፡፡

እኛ የእገሌ ታጣቂ ቡድን አባላት ነን እያሉ በእንግሊዝ የቢቢሲ ሬዲዮ ቅጥር ግቢ የተሰበሰቡት አባላቱ የኢትዮጵያ መንግሥትን አላወገዛችሁም በሚል የሬዲዮ ጣቢያውን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትን መሳደባቸው ምን ያህል ፈላጭ ቆራጭና ጀብደኛ እንደሆኑ በግልጽ ያሳያል፡፡

ተዋጊና የተዋጊ ቡድኑ ደጋፊ ሆነው እያሉ በወታደራዊ ኪሳራ ደርሶብናል ስም ቅሬታ ይዞ ማቅረብ የት ሀገር ነው የተለመደው፡፡ ቅዥት ባይሆን እንኳ ራሳቸውን በራሳቸው ማጋለጥና ሸፍጥ መሆኑን በይፋ አያሳይም ወይ?

“ፋኖ አንድነት ስላጣ ተመቷል“ እያሉ ውስጥ ለውስጥ እየተሽለኮለኩ ለመብላት የሚጠቀሙበትን የሽፍትነት ዘዴ ለመኮነን መነሳሳታቸውስ?

ኩሩ የሆነውን የሀገራችን ህዝብ ብሂል የሚያራክስና ለሀገራቸው ያላቸውን ተነሳሽነት የሚያፋልስም ነው እርካሽ ለሆነ ዓላማቸው የሰው ህይወት መገበርና ለባዕዳን አሽከር መሆን፡፡

የአማራ ክልል ህዝብ በቅርቡ ባካሄደው ትዕይንተ ህዝብ እንደ ቆሻሻ እንደተፋው የተረዳው ቡድኑ ከሀቅ ይልቅ በሚዲያ ፕሮፓጋንዳ ዕድሜውን ለማራዘም ቋምጦ ድሮ ጊዜ የቀረውን የደፈጣ ውጊያ ሁሉ ተግባራዊ ሲያደርግ ነው የቆየው ህዝብን በማሰቃየት ትርፍ ለማግኘት ፈልጎ፡፡

ሰሞኑን የተወሰደበት እርምጃ ግን እዚያና እዚህ እየተሽሎከለከና የውሸት ፕሮፓጋንዳውን እየነዛ እንዲኖር የሚፈቅድለት አይመስልም፡፡ መንግሥት የወሰደውን እርምጃ ማስተባበልና በነጋታው ሌላ ፕሮፓጋንዳ መጀመርንም አላስቻለውም፡፡

የአቋም ኪሳራው ሌላ ማሳያ ግብጽ ሰሞኑን ስታሰማ የቆየቸው ቅዠት ሲሆን ቀደም ሲል በመሪዋ አማካይነት ”ውኃ አናስነካም” ከሚሉት ዛቻ ለየት ብሎ መምጣቱም ምን ዓይነት ወደ ተዘበራረቀ አስተሳሰብ እንደገባች ያሳያል፡፡

ከንትርኩ ይልቅ ፊት ለፊት ግጥሚያ ይሻላል እስኪባል ድረስ ከሀገራችን ጋር ስታደርግ የነበረው እሰጥ አገባ ለዓመታት ዘልቋል፡፡ ሆኖም ግን ያኔ የተለሳለሰ የነበረው አቋሟ አሁን ለምን ገነፈለ ቢሉ በርካታ ምክንያቶችን ማመልከት ይቻላል፡፡

በጊዜው ኢትዮጵያ ስለ ህዳሴ ግድብ ብቻ እንጂ ስለቀይ ባህር ጥያቄ ያለማቅረቧ አንዱ ነው፤ ምክንያቱም በግትር አቋማቸው ካልተመለከቱት በቀር ሁለቱ የፍላጎት ዘውጎች እርስ በርስ በምንም ስለማይገናኙ፡፡

አሁን ግን ኢትዮጵያ ልማት ብታከናወን ሁለቱ የውኃ አካላትን አጣምራ እንዴት መቆጣጠር ትችላለች የሚል ቅናት ያላቸውም ይመስላል በቅርቡ የሀገሪቱ መሪ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በግልጽ እንደተናገሩት፡፡

ሰሞኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ያወጣችው መግለጫ ይህንን መሥመር የሳተና ሌላ አማራጭ ይዞ ብቅ ያለ፣ በቀጥታ ሳይሆን በጎረቤት ሀገራት በኩል ኢትዮጵያን የማተራመስ ዓላማ ያለው ነው፡፡

እንደ አንዳንድ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ዘገባ ከሆነ ሚኒስትሩ የሀገራችን ጎረቤት ለሆኑት ለሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ እና ለሌሎች ስልክ የደወሉ ሲሆን መልዕክቱም ሀገራችን በመሠረተ-ልማት በምትፈጥረው አካባቢያዊ በረከት እንዳይጠቀሙና አደናቃፊ መንገድ እንዲከተሉ ለመወትወት ነው፡፡

ከድሮ ጀምሮ ሲያቀነቅኑ የነበሩበትን ይህንን ሀሳብ እንደገና ማስተጋባታቸው የሚገርም ባይሆንም ምን ያህል ጥቅም ሊያስገኝላቸው ይችላል የሚለው ግን ጥርጣሬን ይፈጥራል፤ ምክንያቱም ኃይል በአሁኑ ጊዜ የዓለም ህዝብ ፍላጎትና ኢትዮጵያ ዋነኛ አቅራቢም እየሆነች ስለመጣች፡፡

ችግራቸውን ይቀርፋል ብለው የመደቡት የግብጽ የውጭ ተራድኦ የተባለው ገንዘብም ሀገራችን ከምታቀርበው አገልግሎት በምንም ስለማይመጣጠን፡፡

ሀገራት በዚህ ገንዘብ በኢትዮጵያ ጥቅሞች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ ተብሎ ቢታሰብም ሀገራችን ከገነባችው መሠረተ ልማት አንጻር ተነጻጻሪ የሆነ ልማት በቀጠናው እስከሌለ ድረስ ገበያዋን መግታት የሚችል አቅም የሌለና እርካሽ ተወዳጅነቷን ብቻ ይፋ ስለሚያደርግ፡፡

እንዲህ ዓይነት ሤራዎችን ከመጋረጃ ጀርባ ቁጭ ብለው ሊሸርቡ የሚችሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንትንም ክትትል ማድረግና በተለይ ከዚህ ቀደም እንዳደረግነው ከአፋቸው ላወጡት መጥፎ ቃል በሀገራቸው ምክር ቤት ላይ ማመልከት ተገቢ የሚሆንበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡