የአዲስ ዓመት ተስፋ
“ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት፣ ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት” እንዲሉ፣ እነሆ የክረምቱ ጊዜ ተገባዶ ሰማዩ ብሩህ የሚሆንበት፣ ምድር በአበቦች የምታጌጥበት ወርሀ መስከረም ሊበሰር ነው፡፡
መስከረም የአዲስ ዓመት መጀመሪያ እንደመሆኑ፣ አዲስ እቅድ የሚታቀድበትና ዓመቱን በአዲስ ተስፋ የምንጀምርበት ነው፡፡
“ንብ አበባ አፍቅራ፣ ህይወት ማር ነው ስትል፣
የዘመኑን ተስፋ፣ ቀስማ ስትፈትል፤
የሚጥመኝ የለም እንዳዲስ ፈገግታ፣
መስከረም አንድ ቀን፣ የእንቁጣጣሽ ለታ!”
እንዲል ገጣሚው፡፡
መስከረም ብራ ነው፡፡ ብራነቱ በዝናቡ ማብቃት ብቻም አይደለም የሚገለጸው፤ ከመስከረም ጸሀይ ጋር ተስፋም አብሮ ይፈነጥቃል፡፡ በአዲስ መንፈስ ለስራ የምንነሳሳበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከተፈጥሮ ለውጥ ብሎም ውበት መገለጥ ጋር የሚተሳሰርና የሚገለጽ ጭምር ነው፡-
“ዓለም ብራ ስትውል፣ ሰማዩ ሲጠራ
የአዲስ ጸሐይ አደይ፣ ነዳ እንደደመራ፣
ፈልቃ እንደጐህ ጮራ፤
ልቤ ክንፍ ሲያበቅል፣ ከመስቀል ወፍ ጋራ፤
ስትዘምርልኝ ያውዳመትን ቅኔ
ይጠፋል ኩነኔ
ጽድቅስ ምኔ ለኔ
ነፍስና ስጋዬ፣ አንድ ናቸው ያኔ!
መስከረም እንዲህ የሚቀኙለት ነው፡፡ ከምድር አበቦች ጋር ልብ በተስፋ የሚሞላበት፣ ተናፋቂዋ ጀንበር ልብን የምታሞቅበት፣ ተፈጥሮ ከስሜት ተዋዳ የህይወት ጉዞ በአዲስ መንፈስ የሚቀጥልበት፡፡ እነኚህን የገጣሚውን ስንኞች ልብ ይሏል፡-
“እንደ ዕውነት የሚሞቅ፣ ክረምት የሚረታ
ስጡኝ አዳዲስ ሳቅ
አዳዲስ ፈገግታ፡፡”
ሌላው በአዲስ ዓመት የሚነሳው ነገር ይቅርታ ነው፡፡ ይህ እንደባህልም በብዙ ማህበረሰቦች ዘንድ የሚታወቅ ነው፤ አዲሱን ዓመት ተመራርቆና ታርቆ መጀመር፡፡ አብሮ በመኖር ሂደት መጋጨት ይኖራል፡፡ ይህ ግጭት ግን በረጅም ጊዜ ሂደት የተገነባ አብሮነትንና ወዳጅነትን ሊያስቀር አይገባም፡፡ ይህ ይሆን ዘንድም ይቅር መባባል ያሻል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለይቅርታ የሚሆን ልብ ያስፈልጋል፡፡ ራስን ለማየት፣ ስህተትን ለማረም፣ ያለፈውን በይቅርታ አልፎ ወዳጅነትን ለማጽናት፡፡
“ብንጣላ መታረቂያ፣
ብንታረቅ ለመጣያ፣
ትንሽ ቦታ መጠለያ፣
ትንሽ ብቻ መሰደጃ፡፡
ምናለበት፤
ለምናልባት ብንተውለት!”
ማንም ስህተት የማይሰራ የለም፡፡ ይህን መረዳት ለይቅርታ የልብን በር ለመክፈት አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ሰውነትን በመገንዘብ ውስጥ ሰው ሆኖ መገኘት ይኖራል፡፡ ይቅርታ መጠየቅና ይቅርታ ማድረግ የዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡-
“ፍጹም መሆን ስለማንችል፣
ትንሽ ባዶ እንዋዋል፣ በልባችን ደግ በኩል፡፡
ለአንጎላችን መላወሻ፣
ትንሽ ቦታ እንተውለት፣
“ምናልባት” የምንልበት፡፡”
ፍጹምነት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ እንዳልሆነ በማስተዋል ውስጥ ከሚመነጨው ከዚህ መልካም አስተሳሰብ ውስጥ፣ ፍቅር የአብሮነት መሸመኛ ድር ይሆናል፡፡ ከዚህ የሚቀዳው ጥበብም የህይወትን የተለያየ ገጽታ እንድንመለከት የሚያስችለን ብቻም ሳይሆን፣ ውሳኔያችን በማስተዋል እንዲሆን የሚረዳን ነው፡-
“ልክ እንዳምና ለዚህ ዓመት፣
ብንጣላ መታረቂያ፣
ብንታረቅ ለመጣያ፣
ብንታሰር ይቅር ማያ፣
ይቅር ብንል መታሰሪያ፣”
ትንሽ እንተው ባዶ ቦታ፡፡”
ማንም ህይወትን በሙላት የኖረ የለም፡፡ ይህ በራሱ አንዱ የሰው ልጆችን የሚያመሳስላቸው ብቻም ሳይሆን አብሮ በመኖር ሂደት ለመደጋገፍና ለመቀራረብ የሚያስችላቸው ነገር ነው። ለዚህ ደግሞ፥ ከመረዳዳት ባሻገር፥ አንዳችን ያንዳችንን ሃሳብና ነገር መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ከመልካም አስተሳሰብና ቅንነት የሚመነጭ ነው፡፡
“ጥግ ድረስ የለም ስራ፣
ጥግ ድረስ የለም ፋታ፣
በልባችን ደግ በኩል፣
እንፈልግ ባዶ ቦታ፣
የጳጉሜ ዓይነት ትንሽ ቦታ፡፡”

More Stories
“ጠንክረን ከሰራን ሰዎችን መሳብ እንችላለን” – መምህር ቃልኪዳን መንክር
የቱሪስት መዳረሻዎች – በሲዳማ ክልል
የጉዞ ጅማሮ