“ግድቡም አለቀ ÷ መስከረምም ጠባ…”

“ግድቡም አለቀ ÷ መስከረምም ጠባ…”

በአንዱዓለም ሰለሞን

“ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አሉ” አለ፤ ከተገናኘን ብዙ ወራት ካስቆጠርነው አንድ ወዳጄ ጋር ሰሞኑን ድንገት መንገድ ላይ ተገናኝተን፡፡

“ስለምን ጉድ ነው ‘ምታወራው?” አልኩት ለነገሩ ብዙም ግድ ሳይሰጠኝ፡፡ እውነቱን ለመናገር ቸኩዬ ነበር፡፡

“እሱንማ እንዲህ መንገድ ላይ አይደለም የማወራህ፡፡ በስነ ስርዓት ተቀምጠን ነው የምነግርህ” አለና ምን ቢለኝ ጥሩ ነው፡-

“ድራፍት እየጋበዝከኝ!”

እንዲህ ነው ድራፍት ማለቴ ድፍረት! በዚህ ኑሮ፣ ያውም በእኔ ስፖንሰርነት የእሱን “ጉድ” ተጎልቼ ልሰማ!

“እኔም ቸኩያለሁ” አልኩና ነገሩን ሳላስረዝም ተሰናበትኩት፡፡ ሌላውን ምላሽ ወይም ሰበብ ደግሞ ያው ሲደውልልኝ አስብበታለሁ፡፡

እኔ ‘ምለው፤ የአንዳንድ ሰው የወሬ ፍቅር ግን እንዴት ያለ ነው ጎበዝ!? ከባህሪው አንጻር እንደገመትኩት፣ ይኼኔ “ጉድ” ምናምን እያለ ያካበደልኝ እኮ የሆነ ከቲክቶክ ተራ አሉባልታ ያልዘለለ ወሬ ሊነግረኝ ነው፡፡

ለማንኛውም ቸኩዬ ነበር፣ ባልቸኩልም ስራ አለብኝ፣ ስራ ባይኖርብኝም፣ የጀመርኩት መጽሀፍ አለ፣ የጀመርኩት መጽሀፍ ባይኖርም፣ ቢያንስ የጀመርኩት ሀሳብ አላጣም፣ ያም ባይሆን፣ ቢያንስ እቤት ገብቼ ከልጄ ጋር አልጫወትም እንዴ የእሱን “ጉድ” እያዳነቅሁ ከምሰማ! …

ለማንኛውም የዘንድሮ መስከረም እንደሀገር ታላቅ ጉድ (የእንግሊዘኛውን ማለቴ ነው) ሰምተን ነው የጠባውና ደስ ብሎናል። እነሆ ታላቁ ግድባችን አለቀ፤ እንኳን ደስ አለን፣ እንኳን ደስ አላችሁ! …

የመስከረምን ነገር ካነሳን ዘንዳ ግን፤ በቀደምለት ባለቤቴ፡-

“ዓመቱ እንዴት ነው የሚሮጠው!? ሳናውቀው ይኸው መስከረም ጠባ!” ስትል፣ ልጄ (ይቅርታ ልጃችን) ምን ቢል ጥሩ ነው፡-

“መስከረም ግን ምንድነው ‘ሚጠባው!?”

ከዚያ እኔ ጣልቃ ገብቼ፡-

“መስከረምማ የእኔን ኪስና የእናትህን ቦርሳ ነው የሚጠባው” አልኩት፡፡

እና ታዲያ መስከረም ሌላ ምን ይጠባል? ጥቅምትን አይጠባ? ቢሆንማ ጥሩ ነበር፡፡

ከሁለቱ በዓላት ባሻገር ብዙ ጣጣ አለው መስከረም፡፡ ለዚያ ይሆን እንዴ አንደኛው በዓል “እንቁ ጣጣሽ” የተባለው? …

ከዓመት በዓል ወጪው ሌላ፤ የልጆች የትምህርት ቤት ወጪ ከጣጣዎቹ መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ትምህርት ቤት የደንብ ልብስ፣ ደብተር፣ መጽሀፍ፣ ምሳ ዕቃ…፡፡ ያም ሆኖ፤ መስከረም ደስ ይላል፡፡ አለ አይደል፣ የልጅነት ትዝታችንን ይበልጥ የሚያስታውሰን ወር ነው፡፡

የዘመን መለወጫ፣ የተስፋ ተምሳሌት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ እናም እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን ማለትን ወደድኩ፡፡ እርግጥ ነው፤ ሰላምና ጤና መሆን ዋጋው በገንዘብ አይተመንም፡፡ እና ደግሞ ሁሉም ከመኖር በኋላ የሚሆንና የሚታሰብ አይደል!…

ለማንኛውም አዲሱ ዓመት ሌላ አዲስ ነገር የምንገነባበት፣ ከምንም በላይ ደግሞ እኛ የምንግባባበት ይሁንልን! ይህን ስል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ፤ አንድ ጓደኛዬ በቅርቡ ያለኝ ነገር፡-

“በአዲሱ ዓመት ከራሴ ጋር መታረቅ ነው ዕቅዴ!”
ነገሩ ገርሞኝ፡-
“እንዴ ተጣልታችሁ ነበር እንዴ!?” ስለው የመለሰለኝ ምላሽ ነው፣ ነገሩ የበለጠ ትኩረቴን እንዲስበኝ ያደረገው፡-

“ቀላል! ራሴን በጣም በድዬው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ በራሴ ላይ አቂሜ ሁሉ ነበር፡፡ አሁን ግን በቃ፤ ራሴን ይቅር ልለውና ከራሴ ጋር ልታረቅ ወስኛለሁ!”

እንግዲህ ጋሽ ያሲን እንደሚሉት “አላህ ያሰብከውን ያሳካልህ!” ከማለት በስተቀር ምን ይባላል!…

አንዳንድ ነገሮች ደግሞ ትንሽ ግራ ያጋባሉ፤ በተለይ ደግሞ ምክር ሲሆኑ፡፡ በቀደምለት አንድ ጓደኛችን ሌላኛውን ምን ብሎ ሲመክረው ሰማሁ መሰላችሁ፡-

“በቃ በአዲሱ ዓመት አዲስ ሰው ሁን!”

እኔ ‘ምለው፤ እንዲህ ዓይነት ምክር ግን ተገቢ ነው ትላላችሁ? ማለቴ አዲስ ሰው ማለት ምን ማለት ነው? ነገሩ “መጽሀፍ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” እንደሚለው አባባል ሆኖብኝ እኮ ነው፡፡ እናም ጠይቃለሁ፤ ሙሉ ሰው መሆን ማለት ምን ማለት ነው? በጎዶሎ መጽሀፍ እንዴት ሙሉ ሰው ይኮናል? ሙሉ መጽሀፍስ አለንዴ? … ብቻ ግን ይህን ማለቴ ማንበብ አያስፈልግም ለማለት እንዳይደለ ልብ በሉልኝማ፡፡

ካላነበብን እንዴት እንጽፋለን፣ ካልጻፍንስ እንዴት እንነበባለን?
“ደፋር እንደጻፈው፣
የጋዜጣ ግጥም፤
ምስጢር አልባ – ተራ፣
ውበትሽ የማይጥም፡፡”
ያለው ገጣሚ ማን ነበር? …

ወደ ቀደመ ነገሬ ስመለስ፤ ጓደኛዬ ጓደኛዬን እንዲህ በማለት ሲመክረው፤ እኔ በበኬሌ እንዲህ እያልኩ በውስጤ አስብ ነበር፤ ‹አዲስ ሰው ሁን ማለት ምን ማለት ነው? የሰውዬው አዲስነት ያለው አሮጌው ማንነቱ ውስጥ ከሆነስ? ማለቴ አንዳንዴ ሙሉ ለሙሉ መፍረስ ማለት መታደስ ላይሆንም እኮ ይችላል፡፡ ነገሩ መቀየር የሚል ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችለው ሁሉ፣ መጥፋት ለሚል ስያሜም ሊዳርግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ሁለቱን ማጣጣም ያስፈልጋል እኮ ጉዳዩ። ዝም ብሎ በአዲስ ሰውነት ስም፣ በስንት የአባት ምክርና ተግሳጽ የተገነባ ማንነትን መደፍጠጥ ተገቢ አይደለም!…› “አንድ አባት ከሺህ የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች ይበልጣል” እንዲል ሳሙኤል ጆንሰን፡፡

ለመካሪው ጓደኛዬ ይህን በውስጤ የሚመላለሰውን ሀሳብ በቅንነት ሳካፍለው፣ እንዲህ ሲል ገሰጸኝ፡-

“አንተ ዝም ብለህ አትፈላሰፍ! እና ደግሞ ጉዳዩ አንተን የሚመለከት አይደለም፡፡ እሱ ግን በአዲሱ ዓመት እንኳ ያግባበት!”

ከዚያ መካሪው ጓደኛዬ ነገሩን ለማለዘብ አስቦ ይሁን ብቻ፡-
“ካልሆነ እንገጥምብሀለን” አለው፡፡
“ደግሞ የምን ግጥም ነው እሱ፤ ማነው ሚገጥምብኝ!?” ጠየቀ ተመካሪው ጓደኛችን፡፡

“ግድቡም አለቀ መስከረምም ጠባ፣
አማን ብቻ ቀረ ሚስት ሳያገባ!
ብለን ነዋ” አለ መካሪው ጓደኛችን እየሳቀ።

ሲገርም! ለካ “አዲስ ሰው ሁን…” ምናምን ሲለው የነበረው አግባ ለማለት ኖሯል? ለማንኛውም የአዲስ ሰውነቱ ትርጉም አግባና ሚስትህ እንደአዲስ ጠፍጥፋ ትስራህ ለማለት እንዳልሆነ ተስፋ በማድረግ እንለፈው፡፡

ግን ደግሞ፣ አንድ ሰው ለማግባት ምክር ያስፈልገዋል እንዴ? እንጃ ብቻ፤ እንደእኔ፣ ለማግባት ማፍቀር ቀዳሚው መስፈርት ነው ባይ ነኝ፡፡ (ብቸኛው አለማለቴን ልብ በሉልኝማ) በበኩሌ ሌላው፣ ሌላው መስፈርት እንዳለ ሆኖ፤ አንድ ሰው ሚስቱን ካላፈቀራት ለምን ሊያገባት እንደሚወስን አይገባኝም። እናም የጓደኛዬ ምክርም ስላልገባኝ “እዛው ጨርሱ” ብዬ ከጨዋታው ወጣሁ እላችኋለሁ።

ኋላ ላይ ግን፣ ተመካሪው ጓደኛችን ለእኔ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው፡-

“ይሔ ሰው ዝም ብሎ አግባ አግባ እያለ የሚጨቀጭቀኝ ሳገባ እኮ ሁለት ልንሆን ነው፣ ትንሽ ቆይተን ደግሞ ሶስትና ከዚያም በላይ! እና በዚህ ኑሮ ከራሴ አልፌ ለስንቱ ላስብለት ነው!?”

“ ‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሀኒቱ› ማለቱ ይሆናላ ” አልኩት እየሳቅሁ፡፡ ያሳቀኝ ሲያወራ ፊቱ ላይ ያየሁት ነገር ነው፡፡ ፊቱን ጥንስስ እኮ ነው ያስመሰለው ጎበዝ፡፡ (ሲጀመር ፊቱ መጀመሪያውንም የሆነ “ከፊል ደመናማ” ዓይነት ነው፡፡…

እሱ የመለሰለልኝን አልጻፍኩላችሁም። ያው ሁሉ ነገር አይጻፍም፡፡ የምንጽፈውን ሁሉም አንኖረውም እኮ፤ እናነበዋለን እንጂ። ልክ የምንናገረውን ሁሉ እንደማንኖረው ማለት ነው፤ አንዳንዴ ዝምታችንንም ነው የምንኖረው፡፡

ምስጋና ከንግግራችን በሻገር ዝምታችንን ላደመጡ፣ ፊታችንን ብቻ በማየት ስሜታችንን ለተረዱ ምርጥና የልብ ወዳጆቻችን!!! …

ለማንኛውም የዛሬውን እንዲህ ጻፍኩላችሁ፡፡ እናንተም ካነበባችሁልኝ እሰየሁ፤ አንብባችሁ አስተያየት ከሰጣችሁኝ ደግሞ የበለጠ እሰየሁ!

አዲሱን ዓመት ቀና ቀናውን የምናስብበት፣ የምናወራበት፣ የምንጽፍበትና የምናነብበት ያድርግልን! ቸር ይግጠመን፣ ሰላም! …