“በቅኝ ግዛት አለመያዟ ነው የራሷ የዘመን አቆጣጠር እንዲኖራት ያደረገው” – መምህር ዕንባቆም ብርሃኔ
በካሡ ብርሃኑ
የሳምንቱ እንግዳችን መምህር ዕንባቆም ብርሃኔ ይባላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ሲዳማ ሀገረ ስብከት የሐዋሳ ሳህሊተ ምህረት ቅድስት ማሪያም ቤተ-ክርስቲያን የብሉይ እና ሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ መጽሐፍት መምህር እና የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ናቸው፡፡ በቆይታችን የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከሌላው ዓለም ስለተለየበት ምክንያት፣ አዲስ ዓመት እና ወጣትነት እንዲሁም በዓል እንዴት መከበር አለበት በሚሉ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፋ ያሉ ሃሳቦችን አንስተናል፡፡ እናንተም ከቆይታችን ጠቃሚ ቁም ነገሮችን እንደምታገኙ ተስፋ እያደረግን እንድታነቡ ጋብዘናችኋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ንጋት፡- በቅድሚያ እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ሥም አመሰግናለሁ፡፡
መምህር ዕንባቆም፡- እኔም እንግዳ እንድሆን ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፡- የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከሌላው ዓለም እንዴት ተለየ ከሚለው እንጀምር?
መምህር ዕንባቆም፡- የዘመን አቆጣጠር መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 1፥1 ጀምሮ ስንመለከት አግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰማይንና ምድርን ፈጠረ ብሎ ይጀምራል፡፡ ከዛ የተወሰነ ነገር ከተናገረ በኋላ፤ ማታም ሆነ ጠዋትም ሆነ ይልና አንድ ቀን ይላል። በዚህ መንገድ ሰባት ቀናትን ያመጣል፡፡ ረቡዕ ላይ ሄደን ስንመለከት ደግሞ የዘመን መቁጠሪያ የሚሆኑ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብትን ፈጥሮ እነዚህን ለወሮች፣ ለዓመታትና ለሌሎች ጊዜ መለኪያ እንደፈጠራቸው ይናገራል፡፡
ወደ ጥያቄህ በቀጥታ ስመጣ፤ ሀገራችን የራሷ የሆነ ፊደል፣ ቋንቋ እና የዘመን መቁጠሪያ አላት፡፡ በዋናነት ከሌለች ዓለም የምትለይበት ምክንያቱ ምንድን ነው? ከተባለ እንደሌሎች ሀገራት በቅኝ ግዛት አለመያዟ ነው መልሱ። ለምሳሌ ሌሎች ሀገራትን ስንመለከት በቅኝ ግዛት ስለተያዙ በያዟቸው ሀገራት ካላንደር እንጂ በራሳቸው ዘመን አይደለም የሚቆጥሩት።
እንደ ትልቅ የዘመን መቁጠሪያ ተደርጎ የሚታየው የጎርጎሮሲያዊያኑ የቀን አቆጣጠርን ስንመለከት በ1582 ዓ.ም ጎርጎሪዎስ በተባለ የሮም ካቶሊክ ጳጳስ የተሰየመ ነው፡፡ ጳጳሱ ያለውን ሥልጣን ተጠቅሞ (ከእግዚአብሔር ተልኮ ነው ሁሉንም ነገር የሚያደርገው ተብሎ ስለሚታመን) በነበረው የዘመን አቆጣጠር ላይ ቀናት በመጨመር አዲስ አቆጣጠር መጀመሩን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
ንጋት፡- ለአንባቢያ ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ ይህን ሃሳብ ዘርዘር አድርገን ብንመለከተው?
መምህር ዕንባቆም፡- ጳጳሱ አንድ ዓመት የሚባለውን 365 ቀን ከስድስት ሰዓት ከሁለት ደቂቃ ከሃያ አራት ሰከንድ፤ በአዋጅ ነው የቀየሩት፡፡ ይህም ማለት በወቅቱ ሐሙስ ጥቅምት አራት የነበረውን ሐሙስ ጥቅምት 15 አድርጎታል፡፡ ሀሳቡን ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ፤ በእኛ የዘመን አቆጣጠር አንድ ዓመት 365 ቀን ከ15 ኪክሮስ ወይም ከስድስት ሰዓት ነው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ካሊት የሚባሉ ሽርፍራፊ ነገሮች ቢኖሩም የእኛ ዘመን አቆጣጠር ይህ ነበር፡፡ በ325 ዓ.ም የኒቂያ ጉባኤ ላይ የተሳተፉ ሊቃውንትም በዚህ እንድንጠቀም ማዘዛቸውን በፍትሃ-ነገሥት መጽሐፍ ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡
ከላይ በጠቀስኩት ጳጳስ አማካኝነት ግን በ1582 ዓ.ም 365 ቀን ከስድስት ሰዓት የነበረውን ወደ 365 ቀን ከአምስት ሰዓት አደረገው፡፡ ከዛም በራሱ 2 ደቂቃ ከ24 ሰከንድ ጨመረና ጥቅምት አራትን ወደ ጥቅምት 15 ቀይሮ ዛሬ ጥቅምት 15 ቀን ነው ብሎ በአዋጅ አስነገረ፡፡
ስለዚህ እነሱ በዚህ መንገድ እየቆጠሩ ሄደው በኋላም ሌሎችን ሀገራትን በቅኝ ግዛት ሲይዙ ለጊዜው አንቀበልም የሚል ተቃውሞ ከእነ ሶቪየት ሕብረትና የመሳሰሉ ሀገራት ቢገጥማቸውም በጊዜ ሂደት ተቀብለው የጎርጎሮሳዊያኑን አቆጣጠር መጠቀም ጀመሩ፡፡
የእኛ እና የጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን አቆጣጠር መሠረታዊ ልዩነቱ የሚጀምረውም እዚህ ላይ ነው፡፡ እነሱ ቀን ሲቆጥሩ ከእኛ ይበልጣሉ፤ ይሄም የሆነው ቅድም በዘረዘርኩት ጳጳሱ ካሳወጁት አዲስ አቆጣጠር የሚመነጭ ነው፡፡ እኛ ደግሞ በቅኝ ግዛት አለመያዛችን የራሳችንን አቆጣጠር ይዘን እንድንዘልቅ እና ከሌላው ዓለም እንድንለይ አድርጓል፡፡
ሌላው የዘመን አቆጣጠራችን እንዲለይ ያደረገው ሀገራችን ባህረ-ሃሳብን በመጠቀም የምትከተለው የራሷ አቆጣጠር መኖሩ ነው። ይህም ማለት ከመጨረሻዋ ትንሿ ሽርፍራፊ ሳድሲት ጀምሮ ነው የሚቆጠረው፡፡ ሳድሲቱ 60 ሲሞላ አንድ ሐሙሲት ይባላል፡፡ ሐሙሲቱ 60 ሲሞላ ራብዒት ይባላል፡፡ ራብዒቱ 60 ሲሞላ ሳልሲት ይሆናል፡፡ ይህም ስልሳ ሲሞላ ካልሂት፤ ካልሂቷ 60 ስትሞላ ኪክሮስ፣ ኪክሮስ 60 ሲሞላ አንድ ዕለት/ቀን ይሆናል። ከዛ ነው ሣምንት፣ ወር እና ዓመት እያልን የምንቆጥረው፡፡ ይህ ማለት ሰዓት፣ ደቂቃ፣ ሰከንድ እንደሚባለው ማይክሮ ሰከንድ ጭምር የምንቆጥርበት አቆጣጠር ነው፡፡
ከዚህም ባለፈ ለምሳሌ ሳምንቱን የምንቆጥርበት አውደ ዕለት፤ ወራቱን ደግሞ አውደ ወር እያልን ከጳጉሜን በስተቀር እኩል 30 ቀናት ኖሯቸው የሚሽከረከሩበት ነው፡፡ በሌሎች ዓለም ቀናቶቹ አንዴ 28፣ አንዴ 29 እና አንዳንዴ ደግሞ 30 እና 31 የሚሆኑበት ጊዜ አለ፡፡
እኛ በራሳችን መንገድ እየቆጠርን 365 ቀን ከ15 ኪክሮስ ሲሞላ አውደ ዓመት የምንለውን በማስገኘት ዘመናችንን እንቆጥራለን፡፡ ዘመናችንንም በአራቱ ወንጌላዊያን በማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ እና ዮሐንስ በመሰየም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዓቱን ተጠብቆ እንዲቆይ እያደረግን ነው፡፡
ንጋት፡- ከሌሎች ዓለም በተለየ የአስራ ሦስት ወር ባለቤት ስላስኘችን ጳጉሜን እናንሳ። ጳጉሜን ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን በማንሳት እንዴት እንደተገኘች ቢያስረዱን?
መምህር ዕንባቆም፡- ሰው በተለምዶ ጳጉሜ፣ ቋጉሜ እና የመሳሰሉትን በመጠቀም ቢጠራትም ትክክለኛ ስያሜዋ ጳጉሜን ነው። ጳጉሜን የሚለው ቃል ‹‹ኤጳጉሜን›› ከተሰኘ የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም በቀጥታ ትርፍ ማለት ነው፡፡ የምን ትርፍ ከተባለ የወር ትርፍ ነው፡፡
በእኛ አንድ ወር የሚባለው በፀሐይ አቆጣጠር 30 ቀን ነው፡፡ ይህም መነሻው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ መጽሐፈ ሄኖክ ምዕራፍ 21 ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በሌላ በኩል በጨረቃ አቆጣጠር ወራቱ አንድ ጊዜ 30፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ 29 ቀን ይሆናል፡፡ ይህም ጉድለት በቤተ-ክርስቲያን ህፀፅ ይባላል፡፡ በአጠቃላይ በፀሐይ 30 በጨረቃ 29 እያለ ይዞራል፡፡ በዚህ መልኩ የምንቆጥረው 12 ወራት በዓመት 360 ቀናት ይኖሩታል (12 ሲባዛ 30 እኩል ይሆናል 360)፡፡ ከዚህ ውጭ የምናገኛት ጳጉሜ አንድ ጊዜ አምስት፣ አንድ ጊዜ ደግሞ ስድስት አና ሰባት የምትሆንበት ጊዜ አለ፡፡
ይህቺ አምስት ቀን ፀሐይ ዙረቷን የምትጨርስበት 365 ቀን በመሆኑ ለወራቱ ከሰጠናቸው 30 ቀናት ውስጥ አምስት ቀን በቋሚነት ይተርፋል ማለት ነው፡፡ ይህችን አምስት ቀን ነው እንግዲህ ጳጉሜን በሚል ስያሜ የምንጠራት፡፡ ምክንያቱም ከወር የተረፈች ስለሆነች ነው፡፡
በሌላ በኩል 360 ቀን ብለን ባስቀመጥነው ውስጥ የሚገኙ ሽርፍራፊዎች ደግሞ አሉ፡፡ ፀሐይ ዑደቷን ለመጨረስ በሚፈጀው 365 ቀን ከአስራ አምስት ኪክሮስ ሲሆን ይህ ወደ ሰዓት ሲቀየር ስድስት ሰዓት ይሆናል፡፡
ስለዚህ በአንድ ዓመት አንድ ቀን ያልሞላች ስድስት ሰዓት ትርፍ አለች ማለት ነው፡፡ ይህን በአራት ዓመት ስናባዛው 24 ይሆናል (4 ሲባዛ 6 እኩል ይሆናል 24) ማለት ነው፡፡ 24 ሞላ ማለት ደግሞ አንድ ዕለት/ቀን ይፈጥራል፡፡ በዚህ መልክ ስናሰላው ጳጉሜን በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ስድስት ትሆናለች የሚባለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ የሚገኙ ካልዒት የሚባሉ ሽርፍራፊዎች አሉ፡፡ እነዚህም ተሰብስበው በ600 ዓመት አንዴ ጳጉሜን ሰባት እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ በአጠቃላይ የጳጉሜን አመጣጥና አቆጣጠር ይህን ይመስላል፡፡
ንጋት፡- ከእኛ ሀገር ጋር ተመሳሳይ ካላንደር የሚጠቀሙ አሉ?
መምህር ዕንባቆም፡- ኢትዮጵያና ግብፅ በሃይማኖት ተመሳሳይ ናቸው፡፡ አኃት ከሚባሉ ቤተ-ክርስቲያናት መካከል በመሆናቸው ባህረ-ሃሳብን ነው የሚጠቀሙት፡፡ ባህረ-ሃሳብ ደግሞ ቅድም እንዳልኩት መነሻው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡
እያንዳንዱን በዝርዝር ለመመልከት ሰፊ ቢሆንም የዕለታት ስያሜን ብቻ ብናይ በእኛ አንድ ማለት እሁድ ነው፡፡ ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ረቡዕ፣ ሐሙስ፣ አርብ እያልን እስከ ቅዳሜ እንቀጥላለን፡፡ እነዚህ የራሳቸው የሆነ ትርጉም አላቸው፡፡ እሁድ ማለት አንደኛ ቀን ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ ሰኞ ማለት ሰኑይ ከሚለው የመጣና ሁለተኛ ቀን ማለት ነው፡፡ ማክሰኞ የምንለው ደግሞ ሰሉስ ነው ሦስተኛ ቀን እንደማለት ነው፡፡ ረቡዕ፤ ረብ አደረገ ረባ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን አራተኛ ቀን ማለት ነው፡፡ ሐሙስ አምስተኛ ቀን፣ አርብ የምንለው ደግሞ መካተቻ ይባላል ስድስተኛ ቀን ነው፡፡ የምን መካተቻ ከተባለ ፍጥረት የተካተተበት፣ ተፈጥሮ ያለቀበት እና አግዚአብሔር ፍጥረትን እሁድ ጀምሮ አርብ ጨርሶ ቅዳሜ ያረፈበት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ቅዳሜ ቀዳሜ ሰንበት ትባላለች፤ ከእሁድ ቀድማ ስለምትገኝ፡፡
በአጠቃላይ የእኛን ስንመለከት ሃይማኖታዊ እና መፅሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ የሌሎችን ስንመለከት ሰንዴይ ነው የሚሉት፤ የፀሐይ ቀን ማለት ነው፡፡ መንዴይ የሚለው የጨረቃ ቀን ማለት ነው፡፡ እነዚህ ከአምልኮታቸው ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ፀሐይን ጨረቃንና ከዋክብትን ያመልኩ ስለነበር ዕለታትንም በዛ ሰይመዋል፡፡ ወራቶቻቸውንም ስንመለከት ተመሳሳይ ነገር አለ፡፡ የእኛ ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡
ንጋት፡- አሁን ላይ የእኛን የዘመን አቆጣጠር በመተው የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን ቀመር የመጠቀም ዝንባሌ በስፋት ይታያል፡፡ ይህ በራሱ የሚያስከትለው ችግር የለም?
መምህር ዕንባቆም፡- አለ እንጂ፡፡ ከላይ እንዳነሳነው ከሌሎች ሀገራት በተለየ የራሳችን የቀን አቆጣጠር እንዲኖረን ያደረገው በቅኝ ግዛት አለመያዛችን ነው፡፡ አሁን ግን ትውልዱ ወዶና ፈቅዶ በቅኝ ግዛት ያዙን የሚያስመስል አካሄድ ሲከተል እያየን ነው፡፡
ይህ ደግሞ ትልልቅ የመንግስት መስሪያ ቤቶችንም ይመለከታል፡፡ በጀት መዝጊያቸውን ጨምሮ በሚያከናውኑት ሥራ የሚጠቀሙት የጎርጎሮሳዊያኑን የጊዜ አቆጣጠር/ካላንደር ነው፡፡
ይህ ደግሞ አባትና እናቶቻችን ዋጋ ከፍለው ያቆዩልንን ነፃ ሀገር እና በውስጡ የሚገኙ የቀን መቁጠሪያ፣ ፊደል፣ ቋንቋ፣ ባህልና እሴቶቻችንን በአግባቡ ካለማወቅ የሚመነጭ ነው፡፡ ያለጦርነት ወደን እጅ ለመሥጠት እየተንደረደርን ነውና ቆም ብሎ ማስብ ያስፈልጋል፡፡ የእኛ የዘመን አቆጣጠር ምን ጎድሎት ነው የምዕራባዊያኑን የምንኮርጀው? ይህን በመፈተሽ ለመፍትሄው መሥራት ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ ለማስተካከል ደግሞ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ለማወቅ ደግሞ መማር ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም ካላወከው አትወደውም፤ ካልወደድከው ደግሞ አታከብረውም፤ አጠብቀውም፡፡ ስለዚህ የዘመን አቆጣጠሩን ጨምሮ ፊደል እና ቋንቋችንን በማወቅ በውስጡ የሚገኙ ምስጢራትን ለመረዳት መማር ያስፈልጋል፡፡
የውጭው ዓለም የእኛን ቋንቋና ፊደል እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ በማስተማር ልጆቻቸው ምስጢራቱን አውቀው ትልልቅ ፈጠራዎችንና ግኝቶችን ሲሰሩ፤ እኛ ግን እያጣጣልነው ለባዕድ አሳልፈን መሥጠትን ሥራችን አድርገነዋል፡፡ በዚህም በየገዳማቱና ቤተክርስቲያናቱ የሚገኙ ትላልቅ ምስጢር የያዙ ጥበብና እውቀት የሚሰጡ መጽሐፍትን መረዳት አቅቶን ለባዕዳን አሳልፈን እየሰጠን ነው፡፡ የዘመን አቆጣጠሩን እና ግዕዝን በማንቋሸሽና የቤተ-ክርስቲያንና የቄስ ብቻ አድርጎ የመመልከት ሁኔታ በመብዛቱ ለመማር ያለው ፍላጎት ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት በመሆኑ መስተካከል አለበት፡፡ የኢትዮጵያ አብዛኛው ታሪክ ተፅፎ የሚገኘው በግዕዝ ነው፡፡ ስለዚህ ግዕዝን ማወቅ ማለት ኢትዮጵያን ማወቅ ጭምር በመሆኑ መስተካከል አለበት፡፡
እነዚህ የኢትዮጵያ ብቻ የሆኑ ቋንቋና ፊደላት ጨምሮ የዘመን አቆጣጠሩን የመጠበቅ ሥራ ከባህልና ቱሪዝም፣ ከቅርስ ባለሥልጣን እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ይጠበቃል፡፡ መንግስት የትምህርት ፖሊሲውን በማሻሻል ጭምር በትምህርት ሥርዓቱ እንዲካተት በማድረግ ትውልዱን ማስተማር ይጠበቅበታል፡፡ የግዕዝ ቋንቋና ፊደላት የቤተክርስቲያን ብቻ አድርጎ መመልከት ተገቢ ባለመሆኑ መንግስት እንደ መንግስት ኃላፊነት በመውሰድ በማስተማር እንዳይጠፋ ከማድረግ ጎን ለጎን በውስጡ ያሉ ጠቃሚ መረጃዎችና እውቀቶችን ለሀገር ጥቅም እንዲውሉ በቅንጅት መሥራት አለበት፡፡ አንዳንድ ሀገራት የእብራይስጥ ቋንቋን በማጥናት የዓለም ጥንታዊ ታሪክን ለማወቅ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የእኛ አብዛኛው ታሪክ በግዕዝ ውስጥ እንደመገኘቱ ቋንቋውን በማሳደግ ታሪካችንን ይበልጥ ለማወቅ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ቋንቋን ከዘር፣ ከሃይማኖት እና ከሌላ ነገር ጋር ሳናያይዝ በቋንቋነቱ ብቻ በመረዳት እንዳይጠፋ ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡
ንጋት፡- ሀገር እና ሃይማኖት ከቤተ-ክርስቲያን አስተምሮ አንፃር እንዴት ነው የሚገለፀው?
መምህር ዕንባቆም፡- ሀገር በሀይማኖት ውስጥ ትልቅ ቦታ ነው ያላት፡፡ ምክንያቱም ሀገር ሳይኖር ሀይማኖት አይኖርም፡፡ ሀይማኖት የሚኖረው ደግሞ ሀይማኖተኞች ሲኖሩ ነው። ሀይማኖተኞች የሚኖሩት ደግሞ ሀገር ሲኖር ነው፡፡
ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የምናውቀው የእስራኤላዊያን ታሪክ ሰዎቹ በግብፅ ምድር ለዘመናት ኖረዋል፡፡ ነገር ግን ሀገራቸው አልነበረም፡፡ ሀገራቸው እንዲገቡ የእግዚአብሔር እርዳታን ማግኘት ነበረባቸው። እነሱም ወደ ሀገራቸው ለመግባት ይፀልዩ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሰው ሀገር ስለነበሩ አኗኗራቸው በጣም በሚያሳቅቅ ሁኔታ ነበር፡፡ ጡብ/ፒራሚድ እየሰሩ የፀነሱ እናቶች ሳይቀር እረፍት ሲፈልጉ እየተከለከሉ ፅንሳቸውን ከጭቃ ጋር እየቀላቀሉ ያቦኩ ነበር። ወንድ ልጆችም ሲወለዱ ወደፊት ያጠቁናል በሚል በንጉሱ ትዕዛዝ ሲገደሉባቸው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቤን ልቀቅ እያለ ቢናገርም ብዙ መስዋዕትነት ለመክፈል ተገደዋል፡፡
ምንም እንኳን መጨረሻ ላይ ጠንካራ መሪ አግኝተው በእግዚአብሔር እርዳታ ነፃ ቢወጡም ብዙ የመከራና ጭንቅ ዘመን አሳልፈዋል፡፡ ሀገራቸው ሲደርሱም ርስታቸው በጠላት ቁጥጥር ሥር ሆኖ ቢያገኙም ተዋግተው ወርሰዋል፡፡
ይህ የሚያሳየን ሀገር ከሌለ ችግር፣ መከራና ስቃይ እንደሚያጋጥም ነው፡፡ ስለዚህ ሀገርን መጠበቅ እና ስለሀገር መዋጋት እንደሚገባ በመጽሐፍ ቅዱስ በግልፅ ተሰንዶ ተቀምጧል። ይህም በሀይማኖት አስተምሮ ውስጥ ሀገር አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
ለዚህም ነው በእኛም ሀገር በአድዋ ጦርነት ወቅት ከመሪዎች ባልተናነስ የሀይማኖት አባቶች ታቦታቱን ይዘው በመምራትና በመባረክ የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉት፡፡ እንደውም በወቅቱ የነበሩ የሀይማኖት አባቶች ‹‹ስብዓተ ፍቁር›› የሚባለውን የሰዓታት ፀሎት በመፀለይ ከፊት ሆነው ከማገዝ ባለፈ፤ አንዳንዶቹ ‹‹ወግድልኝ ድጓ፤ ወግድልኝ ቅኔ፤ ጀግኖች ከዋሉበት እውላለሁ እኔ›› እያሉ በቀጥታ ጦርነቱ ላይ መሳተፋቸው ይነገራል። ለዚህም ምክንያቱ ምንድን ነው ከተባለ ጦርነቱ የሀይማኖት ጉዳይ ጭምር ስለሆነ ነው፡፡ በወቅቱ በቅኝ ግዛት ብንያዝ ኖሮ ዛሬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የሚባል አይኖርም ነበር፡፡ ስለዚህ ሀገርን መጠበቅ ማለት በተዘዋዋሪ ሀይማኖትን መጠበቅ ስለሆነ ቤተ-ክርስቲያናችን ብዙ ዋጋ ከፍላለች፡፡
ከዚህም ባለፈ ዕለት ተዕለት በሚከናወኑ የፀሎት መርሃ-ግብሮች ስለሀገር ይፀለያል። በፀሎቱ ስለ ሀገር ዳር ድንበር፣ ስለህዝቧ፣ ወንዞቿና ተራራዎች፣ ስለምድር ውሃና ዝናብ፣ ስለወታደሮቿ እና በአጠቃላይ ስለሁሉም የሀገሪቱ የልማት ሥራዎችና መከናወኖች ይፀለያል፡፡ ስለዚህ ሁለቱ የማይነጣጠሉ ነገሮች ስለመሆናቸው በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንደውም ሀይማኖት እንደ ነፍስ፤ ሀገር ደግሞ እንደ ሥጋ በመሆን አንድ መሆናቸውን የሚገልፁ አባቶች አሉ፡፡ ይህ ማለት አንዱ ከአንዱ ህልውና ውጪ መኖር የማይችሉ ናቸው፡፡
ለዚህም ነው በሀገር ደረጃ ሀይማኖት የሌለውና እግዚአብሔርን የማይፈራ ትውልድና ሕዝብ በበዛ ቁጥር በዓለም ህግ ብቻ መምራት ከባድ ሆኖ ለቀውስ የሚዳረጉት። ምክንያቱም የሚፈራው ፈጣሪን ሳይሆን ህጉን በመሆኑ ወንጀል ለመሥራት ወደኋላ አይልም፡፡ ሀይማኖት ካለው ግን የሚፈራው እግዚአብሔርን በመሆኑ ማድረግ ያለበት እና የሌለበትን በመለየት ለሰማያዊው ሕይወት የማይበጀውን ነገር ከማድረግ ይቆጠባል። ስለዚህም ነው ሀገር በሃይማኖታችን ዘንድ ሰፊና ትልቅ ቦታ አላት የምንለው፡፡
ንጋት፡- ወጣትነት እና መንፈሳዊነት ከአዲስ ዓመት ጋር አያይዘው እንዴት ባለ መልኩ ነው መቃኘት ያለበት ይላሉ?
መምህር ዕንባቆም፡- በመጀመሪያ ወጣትነት ምንድን ነው? የሚለውን መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡ በቤተክርስቲያናችን አራቱ ባህሪያት የሚባሉ አሉ፡፡ ይህ ማለት የሰው ልጅ የተፈጠረው ከአራቱ ባህሪያተ ሥጋ እና አምስተኛ ከሆነው ባህሪያተ ነፍስ ነው፡፡
የመጀመሪያው ባህሪየ ነፋስ ይባላል፡፡ የነፋስ ወቅት እንደማለት ሲሆን ከተወለድን ጀምሮ እስከ ሃያ ዓመት ያለውን ጊዜ የሚይዝ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ሕፃናት በመሆናቸው በጣም ይፈጥናሉ፤ ልክ እንደ ነፋስ ለመያዝ ያስቸግራሉ፣ እዚህም እዚያም ይገኛሉ ፈጣን ናቸው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ዘመነ እሳት የሚባል ሲሆን ከሃያ ዓመት እስከ አርባ ያለውን የሚይዝ ነው፡፡ ወጣትነትን እዚህ ላይ ነው የምናገኘው፡፡ ወጣቶች አካላዊ ለውጥ፣ ሃሳባዊ ነውጥ የሚገጥማቸው ወቅት ነው፡፡ ይህ ዘመን ለተጠቀመበት ለሥራ ምቹ ነው፡፡ በመንፈሳዊ ዓለም በመልካም ሥራ የተቸገሩትን ረድቶ፣ ፆሞና ፀልዮ መንግስተ ሰማያትን ለመውረስ የሚዘጋጅበት ነው፡፡ በሥጋዊ ዓለም ደግሞ ወጥቶ ወርዶ፣ ተምሮና ሰርቶ የሚበለፅግበትና ባለሃብት የሚሆንበት ነው፡፡
ይህንን ወቅት ያበላሸ ሰው ቀጣይ ያሉት ዘመናት ይበላሹበታል፡፡ በዚህ ወቅት ተምሮ ያልተለወጠ፣ ሰርቶ መለወጥ ካልቻለ ዘመነ ውሃን ያበላሻል፡፡ ይህ ማለት ከአርባ እስከ ስድሳ ባለው የዕድሜ ክልል ሰዎች ቀዝቀዝ የሚሉበት እና ወደራሳቸው የሚመለሱበት በመሆኑ፤ ተገቢ ያልሆነ ሥራ ከሰሩ የሚፀፀቱበት፤ መልካም ሥራ ከሰሩ ደግሞ የሚያርፉበት ነው።
ዕድሜውን በአግባቡ ለተጠቀመበት ከስድሳ እስከ ሰማኒያ ባለው የዘመነ መሬት ወቅት በጥሩ ሁኔታ ማሳለፍ ይችላል፡፡ ይህ ማለት በዘመነ መሬት ሰዎች በእርጅና ዝቅ ብለው የሚሄዱበት እና በኋላም መሬት ነህና ወደ መሬት ትመለሳለህ የሚለውን ትዕዛዝ የሚከተሉበት ነው፡፡
ስለዚህ ዘመነ እሳት/ወጣትነቱ ላይ ዘመኑን ያበላሸ ሰው ቀጣይ ያሉት ዘመናቱ ሁሉ ይበላሹበታል፡፡ ትውልዱ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ቆም ብሎ ማሰብ ያለበት፡፡ እንደሚታወቀው እሳት ጠቃሚም ጎጂም የምናደርገው እኛው ነን፤ እንደአጠቃቀማችን ነው እኛ የምንወስነው። በአግባቡ ከተጠቀምነው ምግብ አብስለን እንበላበታለን፤ ሲበርደን እንሞቀዋለን፤ ለብዙ ነገር እንጠቀመዋለን፡፡ በአንፃሩ በአግባቡ ካልተጠቀምነው ሀብት ንብረት ያወድማል፤ ሀገራት ይቃጠሉበታል ይጠፉበታል፡፡ ወጣትነትም እንደዛ ነው፡፡
ለዚህም ነው መጽሐፈ መክብብ ምዕራፍ 12፥1 ላይ ‹‹በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ›› የሚለው፡፡ በዚህ ዘመን ሰው እግዚአብሔርን ካላሰበ፤ አቅምና ጉልበት ስላለ ማንም የሚችለኝ የለም ቢል፤ ከሰዎች ጋር ይጣላል፤ ለሀጢያት ይጋለጣል፣ ለሱስ ይዳረጋል፡፡ ፈጣሪን ካሰበ ግን እንደነዚህ ያሉ ነገሮች ውስጥ አይገባም፡፡
በቤተክርስቲያናችን በወጣትነት ዘመናቸው እግዚአብሔርን አገልግለው ቅዱሳን ተብለው የሚጠሩ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ወጣቶችም ከእነሱ በመማር በዘመኑ ከሚንፀባረቀው የተሳሳተ አካሄድ መመለስ አለባቸው፡፡ አንዳንድ ወጣቶች እኔ የእንትን ሀይማኖት ተከታይ ብሆንም መቅረብ አልፈልግም ሲሉ ይሰማል፡፡ ይህ ደግሞ ተገቢ ባልመሆኑ ቀረብ ብሎ በመማርና በማወቅ ከዘመኑ መቅሰፍት ጭምር ለማምለጥ መጣር አለባቸው፡፡ ወጣቱ ለሀገሩ እና ሀይማኖቱ ታማኝ በመሆን እስከመጨረሻው መትጋት አለበት፡፡
በተለይ አዲስ ዓመት ሲመጣ ልብስን፣ ቤትን፣ ስልክን እና አንዳንድ ነገሮችን ብቻ መቀየር ሳይሆን አስተሳሰብን በመቀየር ለለውጥ እራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ አዲስ ዘመን የምንለው እኮ እኛን ነው የሚመስለው። መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ዘመኑ አንተ ነህ፡፡ አንተ ስትከፋ ይከፋል፤ አንተ መልካም ስትሆን ደግሞ መልካም ይሆናል›› ይላል፡፡ በሌላ በኩል መልካም ዘመን ልታይ ከወደድክ፤ ከክፉ ነገር ሽሽ፤ ሠላምንም ፈልጋት፤ ተከተላትም ይላል፡፡ እንደዛ ካደረክ መልካም ዘመን ታያለህ፡፡
ስለዚህ ዘመኑ መልካም የሚሆነው ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያን ሲቀርቡና አስተምህሮቱን በማወቅ መተግበር ሲጀምሩ ነው፡፡ ይህን አደረግን ማለት ደግሞ ከሀጢአትና የተሳሳተ መንገድ በመውጣት መልካም በማድረግ መልካም ዘመን እንድናይ ያግዛል እና ወጣቱ በአዲስ ዓመት መሰል አስተሳሰብ በመያዝ ለመቀየር መትጋት አለባቸው፡፡ እንደዛ ማድረግ ከተቻለ በአዲስ ዘመን ብሩህ ተስፋ ማየት እንችላለን፡፡
ይህን ለማድረግ ደግሞ ተስፋ የምናደርገው እና ለማሳካት የምንተጋለት ግልፅ ዓላማ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ በክርስትና ተስፋ የሌለው ሰው/ተስፋ መቁረጥ ተገቢ እንዳልሆነ ይታመናል፡፡ ለዚህም ማሳያ ብዙ አብነቶችን መጥቀስ ቢቻልም ‹‹ክርስቲያን ተስፋ አይቆርጥም›› የሚለው ብሂል በቂ ነው፡፡ ስለዚህ በምድር ላይ ስንኖር የምንከተለው የሕይወት መርህ ለሰማያዊው ዓለም ጭምር ስንቅ ስለሚሆን አካሄዳችን ትክክለኛውን መንገድ የተከተለ መሆን አለበት፡፡
ንጋት፡- የአባይ ወንዝ/ግዮን እና ኢትዮጵያ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንፃር ቢያብራሩልን?
መምህር ዕንባቆም፡- ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 2፥10 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው፤ ከአራቱም አቅጣጫ ገነትን የሚያጠጡ አራት ትላልቅ ወንዞች እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ከእነዚህ ወንዞች አንዱ ግዮን/አባይ የኢትዮጵያን ምድር እንደሚከብ ያወሳል፡፡
ይህ ታላቅ ወንዝ አባይ የሚለውን ስያሜ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፃድቅ ተብለው በሚጠሩ አቡነ ዘርዓብሩክ የተሰኙ ሰው እንደሰጡት የቤተ-ክርስቲያን ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ አባይ በመጽሐፍ ቅዱስ ካለው ታሪክ ባልተናነሰ በቤተክርስቲያናችንም ትልቅ ቦታ ነው የሚሰጠው፡፡
በዘመናችንም ይህ ታላቅ ወንዝ ለልማት ሥራ ውሎ ህዝብን በሚጠቅም ተግባር ሲውል ማየት የሚያስደስት ነው፡፡ ዘመኑ የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ ለዘመኑ የሚበጅ ሥራ እየተሰራበት መሆኑ ያስደስታል፡፡ ይህም ለብዙሃኑ መብራት ማግኘት ላልቻሉ የሀገራችን ዜጎች የኤሌክትሪክ ብርሃን እንዲያገኙ የሚያደርግ በመሆኑ የሚደነቅ ነው፡፡ መሰል ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግ ሀገርን ከችግር ተምሳሌትነት በማውጣት አዲስ ታሪክ መፃፍ ያስችላል፡፡
መጋቢ ሀዲስ የሚባሉ የቤተ-ክርስቲያናችን መምህር እንዳሉት ‹‹በወጭ ሀገር ውሃ ሲገኝ ተገድቦ ለልማት ይውላል፡፡ በእኛ ሀገር ግን ውሃ ሲኖር ድንበር ሆኖ የልዩነት እና የፀብ ምንጭ ሲሆን ይታያል፡፡ ከእዚህ አስተሳሰብ መውጣት አለብን፡፡ የአባይ ግድብ ይህን ታሪክ የቀየረ በመሆኑ መሰል ወንዞችን በመገደብ ለልማት ማዋል ከችግር ለመውጣት የሚያግዝ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት›› ሲሉ ሰምቻሉ። የእሳቸው መልዕክት የእኔም መልክት ነውና ትንንሽ ወንዞችን ጭምር በመገደብ አርሶ አደሩ በመስኖ ሥራ እንዲሰማራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ንጋት፡- አዲስ ዓመት እንደመሆኑ ቤተ-ክርስቲያን በዓል እንዴት ባለ መልኩ ነው መከበር ያለበት ትላለች?
መምህር ዕንባቆም፡- ቤተ-ክርስቲያናችን በዓላት እንዴት መከበር እንዳለባቸው በመጽሐፍ ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ለምሳሌ ፍትሃ ነገስት አንቀፅ 19፤ ስለሰንበት በማንሳት የበዓላት አከባበርን በዝርዝር ይናገራል፡፡ መጽሐፉ ‹‹በዓላትን ስናከብር እንደ አይሁድም ሆነ፤ እንደ አህዛብም ማክበር የለብንም›› ይላል፡፡ ምን ማለት ነው ከተባለ፤ እስራኤላዊያን በዓል ሲያከብሩ ከተቀመጡ አይነሱም፣ በር ከከፈቱ አይዘጉም፡፡ በዛ ቀን ጦርነት እንኳን ቢከሰት ስለማይዋጉ ያልቃሉ፡፡
ስለዚህ እኛ እንደነሱ ማክበር እንደሌለብን ይነግረናል፡፡ በዓላትን ስናከብር የተቸገሩትን እያበላን፣ የተጠማ እያጠጣን፣ የታመመ እያሳከምንና እየጠየቅን እንጂ ቁጭ ብለን እንድናሳልፍ አይፈቅድም፡፡ በዓል ማለት መንፈሳዊ ሥራ በመሥራት ሰዎችን የምንጠቅምበት እንጂ ቁጭ የምንልበት መሆን የለበትም፡፡
እንደ አህዛብም መሆን የለበትም ሲልም፤ አህዛብ ከመጠን በላይ በመብላትና በመጠጣት ዝሙትና ሀጢአት እየሰሩ ስለሚያሳልፉ እንደነሱ መሆን እንደሌለብን ቤተክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ በአንዳንድ የዓለም ሀገራት እንደምናየው መቅሰፍትና ቁጣ እንዳይመጣብን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
በቤተክርስቲያናችን መጠጥና ስካር በፍፁም የተከለከለ ነው፡፡ ነገር ግን ቤተ-ክርስቲያን እንደዚህ እያስተማረች በከተሞቻችን ጭምር ለሌላ ሀጢአት የሚጋብዝ ከመጠን ያለፈ መብል፣ መጠጥና የጭፈራ ዝግጅቶች ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡
ስለዚህ ምዕመናን ከመሰል ፕሮግራሞች እራስን በማራቅ ከዋዜማ ጀምሮ በቤተ-ክርስቲያን በሚከናወኑ መርሃ-ግብሮች በመሳተፍና ቃለ እግዚአብሔርን በመስማት ማሳለፍ አለብን፡፡ በልተንና ጠጥተን ከምንሰክር፤ የሚበላው ላጣ ወገን በማካፈል እና የበዓሉን ዓላማ ከቤተክርስቲያን በመረዳት ማሳለፍ ያስፈልጋል፡፡ መታወቅ ያለበት በመብላትና መጠጣት የሚገኘው ደስታ ምግብና መጠጡ ሲያልቅ ያበቃል፡፡ ስለዚህ ለተቸገሩ ወገኖች በማካፈል የሚገኘውን ዘላቂ ደስታ በማሰብ በዓልን ማክበር እንደሚገባ በዚህ አጋጣሚ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡
ንጋት፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ እና ጊዜ በድጋሚ በዝግጅት ክፍሉ ሥም አመሰግናለሁ።
መምህር ዕንባቆም፡- እኔም አመሠግናለሁ። መልካም በዓል!
More Stories
የአፍሪካ ኩራቶች
“ሀገር በቀል ምርቶችን በብዛት ማምረትና መሸመት ለብልጽግና ጉዞ ቁልፍ ሚና አለው” – ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ
“አካል ጉዳተኛ መሆኔ ከቀጣይ የህይወት ጎዳና አላስተጓጎለኝም” – አቶ አማን ቃዊቲ