የአፍሪካ ኩራቶች

የአፍሪካ ኩራቶች

በአንዱዓለም ሰለሞን

ዓለም አቀፍ ተወዳጅነትን ባተረፈው የአትሌቲክስ ስፖርት በርካታ አፍሪካዊያን አትሌቶች ውጤታማ ለመሆን ችለዋል፡፡ እነዚህ አትሌቶች፣ በስፖርቱ ስኬታማ ለመሆን፣ ብዙ መሰረተ ልማት በሚፈልገው ስፖርት ያን ያህል የተሟላ ነገር በሌለበት በጥረታቸው ለዚህ መብቃታቸው አድናቆትን የሚያስችራቸው ነው፡፡

በዚህ ረገድ ለዛሬ በስፖርቱ በተለይም እ.ኤ.አ በ2024 ባካሄዷቸው ውድድሮች ጥሩ ጊዜን ካሳለፉ አትሌቶች ሁለቱን ለአብነት እንመለከታለን፡፡

ቦትስዋናዊው ሌትስሌ ቶቤጎ በዚህ ረገድ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል ይገኛል፡፡ በወርሀ ሰኔ 2003 የተወለደው ይህ አትሌት፣ የመጀመሪያ ውድድሩን በ17 ዓመቱ በፖላንድ ያደረገ ቢሆንም፣ ስኬታማ የአትሌቲክስ የውድድር ጅማሮው የሚጀምረው በ2021 በተካሄደው በዓለም ከ20 ዓመት በታች ውድድር ነበር፡፡

በኬንያ በተካሄደው በዚህ ዓለም አቀፍ ውድድር በ100 እና በ200 ሜትር የሩጫ ውድድር የወርቅ እና የብር ሜዳሊያዎችን ለማግኘት ችሏል፡፡

በዚያው ዓመት አትሌቱ መቶ ሜትርን ከ10 ደቂቃ በታች ለመሮጥ የበቃ የመጀመሪያው ቦትስዋናዊ የሆነበትን ውጤት ለማስመዝገብ ችሏል፤ ርቀቱን 9.96 በመሮጥ፡፡ ከዚህ አስቀድሞ በ18 ዓመቱ 10.8 በመግባት የሀገሩን የ100 ሜትር ክብረ ወሰን ለማሻሻል በመቻሉ ይህ ውጤት በእርግጥም የሚጠበቅ ነበር፡፡

ይህን በጋቦሮኒ ያስመዘገበውን ሰዓት በኢውጅን ኦሪገን በተካፈለበት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሻሻለው፤ 9.94 በመግባት፡፡

በመቀጠለም ይህን የራሱን ክብረ ወሰን በኮለምቢያ ካሊ ላይ ባደረገው ውድድር አሻሽሎታል፤ 9.91 በመግባት።

ነሀሴ 8፣ 2024 ለአትሌቱ የተለየ ቀን ነበር፡፡ በፓሪስ ኦሎምፒክ በ200 ሜትር የሩጫ ውድድር በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆኗል፡፡ ይህም በኦሎምፒክ መድረክ ያሸነፈ የመጀመሪያው ቦትስዋናዊ ያደረገው ሲሆን ከመንግስትም ሁለት የመኖሪያ ቤቶች ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡

በወርሀ መስከረም፣ 2004 በብራሰልስ በተካሄደ የዳይመንድ ሊግ ውድድር አሸናፊ ሆነ፡፡ ምንም እንኳ በአጠቃላይ ውጤት የውድድሩ አሸናፊ ባይሆንም፣ በ200 ሜትር የገባበት ሰዓት (19.80) በጥሩ አቋም ላይ እንደሚገኝ ያስመሰከረበት ሆኗል፡፡

በወርሀ ጥቅምት፣ በፓሪስ ኦሎምፒክ ባስመዘገበው ታሪካዊ ድሉ ምክንያት፣ ከዓለም አቀፉ ኦሎምፕክ ኮሚቴ የውድድሩ ምርጥ ወንድ አትሌት በሚል ሽልማት አግኝቷል፡፡ በወርሀ ህዳር ደግሞ የዓመቱ ምርጥ አትሌት በሚል ተሸልሟል፡፡

ወደሀገሩ ሲመለስ የጠበቀውን ደማቅ አቀባበልም እንዲህ በማለት ገልጾታል፡-

“የህዝቡ አቀባበል እጅግ የሚያስደንቅ ነበር፡፡ 80ሺህ ሰው በስታዲየምና በጎዳናዎች ላይ በመገኘት ነበር ደስታቸውን የገለጹልኝ፡፡ አሁን ህይወቴ እንደተቀየረ ይሰማኛል፡፡ እኔም በበርካታ የሀገሬ ዜጎች ላይ ተጽእኖ እንደፈጠርኩና ለአፍሪካ ጭምር አንድ ነገር እንዳደረኩ ይሰማኛል፡፡ በምንም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ያሰቡትን ማሳካት እንደሚቻል አሳይቻለሁ፡፡”

ይህ በእርግጥም ከህይወት ልምዱ የተቀዳ አስተያየት ነው፡፡ ከኦሎምፒክ ውድድሩ አስቀድሞ የሚወዳትን እናቱን በሞት አጥቶ በጥልቅ ሀዘን ውስጥ ነበር፡-

“እናቴን በሞት ካጣሁ በኋላ የነበሩት የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ለእኔ በጣም አስቸጋሪ ነበሩ፡፡ ምክንያቱም ለእኔ የዓለም ፍጻሜ ነበር የመሰለኝ፡፡ የስፖርቱ እና የሁሉም ነገር መጨረሻ እንደሆነ አድርጌ ነበር ያሰብኩት፡፡” በማለት በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ያስታውሳል፡፡

በእርግጥም በአሁኑ ሰዓት በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ይህ አትሌት፣ በአጭር ርቀት ሩጫ ለሀገሩ ብቻም ሳይሆን ለአፍሪካም ጭምር ኩራት መሆን የቻለ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በ200 ሜትር ተቀናቃኙ ከሆነው አሜሪካዊው ኖሀ ላለስ እኩል የዩሴን ቦልትን ክብረወሰን ሊያሻሽል ይችላል ተብሎ ግምት የተሰጠው አትሌት ለመሆን ችሏል፡፡

ይህን አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው አስተያየትም ሊሳካ እንደሚችል ፍንጭ ሰጠበትን ምላሽ ሰጥቷል፡-

“በሂደት የምናየው ይሆናል፤ ነገር ግን አሁን ራሴን ማስጨነቅ አልፈልግም” በማለት፡፡

በሴቶቹ በ2004 ውጤታማ ከሆኑ አትሌቶች መካከል እ.ኤ.አ ሀምሌ 7 ቀን 1997 የተወለደችው ደቡብ አፍሪካዊቷ ዋናተኛ ታቲጃና ሶንሜከር ትጠቀሳለች፡፡

በደረት ቀዘፋ የዋና ውድድር የምትታወቀው አትሌቷ በ2018 በተካሄደው የጋራ ብልጽግና ሀገራት ውድድር ላይ በ100 እና በ200 ሜትር ውድድሮች የበላይነትን በመቀዳጀት በዓለም አቀፍ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመታወቅ ችላለች፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ በ2020 በተካሔደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ፣ በ200 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት አድናቆትን አትርፋለች፡፡ ይህም ከ1996 ወዲህ በዋና ለደቡብ አፍሪካ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘች የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት አድርጓታል፡፡

ከዚህ አንጸባራቂ ድል በኋላ፣ በ2024 በዓለም አቀፍ ውድድር ያሳካቻቸው ሌሎች ሁለት ሜዳሊያዎች አትሌቷን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናዋ የበለጠ ከፍ እንዲል ብሎም በስፖርቱ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ አትሌቶች ተርታ እንድትሰለፍ አስችሏታል፡፡