“ሀገር በቀል ምርቶችን በብዛት ማምረትና መሸመት ለብልጽግና ጉዞ ቁልፍ ሚና አለው” – ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ
በመሐሪ አድነው
“የኢትዮጵያን ይግዙ” ኤግዚቢሽንና ባዛር በሲዳማ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ከንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር በሀዋሳ የንግድ ሳምንት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ተገኝተው በይፋ ከፍተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት በመላቀቅ ዘርፈ ብዙ እና ተከታታይነት ያለው ዕድገት እያስመዘገበች በማንሰራራት ላይ ትገኛለች፡፡
በአጠቃላይ በኢኮኖሚ ሪፎርም የእድገት ሞተሮች በውስን ዘርፍ ላይ ተንጠልጥሎ ከነበረበት ዘርፈ ብዙ እንዲሆን ተደርጓል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ይባክኑ የነበሩ ዕድሎችን አሟጦ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል ቀጣይነት ያለው እድገት በማስመዝገብ ሀገራችንን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ጠንካራ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
መንግስት የተሳለጠ ተወዳዳሪ እና ፍትሀዊ የንግድ ስርዐት ዘርግቷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በዚህም የሁሉንም ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ የተጀመረውን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል የንግድ ስርዐቱን ማነቆ በመፈተሽ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በክልላችን “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ኤግዚብሽንና ባዛር ህብረተሰቡ የሀገራችንን ምርት መጠቀምን ለማበረታታት፣ እንዲሁም የክልሉን የወጪ ምርቶችን እምቅ ሃብት ለማስተዋወቅና ዘላቂ የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚካሄድ ኩነት ነው ብለዋል።
የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶች ኤግዚብሽንና ባዛር ማካሄድ በሀገር አቀፍ ተቋማትና በክልሉ ውስጥ የወጪ ምርት አምራቾች፣ አቅራቢዎችና ኢንተርፕራይዞች መካከል የንግድ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ጠቀሜታ ከማበርከቱም ባሻገር ለክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢን እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
ለሚቀጥሉት 5 አመታት የንግዱን ዘርፍ በክልሉ ከፍ ለማድረግ ትኩረት በመስጠት እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረው በሀገር ውስጥ የሚገኙ ምርቶችን በመግዛት የሀገር ውስጥ ጥራት ያለው ምርት እንዲስፋፋ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ቁጥር እንዲጨመር ህብረተሰቡ ሚናውን መወጣት አለበት ብለዋል።
ከውጭ የሚገባውን ብቻ የሚገዙ ዜጎች የበዙበት ሀገር ከድህነት አረንቋ ለመውጣት አስቸጋሪ ይሆናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያም ይሁን ክልሉ በማምረት ላይ ስለሚገኙ የክልሉ ማህበረሰብ የሀገር ምርቶችን መግዛትና በንግድ ሥራ ላይ በመሰማራት በሀገር ደረጃ ተወዳዳሪ እና እኩል የሀብት ተጠቃሚ ለመሆን ራስን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
በክልሉ በንግድ ላይ የተጀመሩት የዕድገት ሪፎርሞች እና የልማት ትሩፋት ውጥኖች ወደ ብልጽግና የሚመሩ በመሆናቸው ክልላዊ ጥረቶችን እና ጥበቦችን በመጠቀም እጅ ለእጅ ተያይዞ በመስራት የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን የብልጽግና ከፍታ ለማረጋገጥ የንግዱ ማህበረሰብ ለህግ ተገዥ በመሆን የጋራ ሀገሩን መገንባት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
“የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል ንቅናቄ መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ባዛርና ኤግዚቢሽን ሸማች እና አምራችን በቀጥታ ከማገናኘቱ ባሻገር የሀገራችንን ይሁን የክልላችንን እምቅ አቅም ለአለም በማስተዋወቅ ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሠላማዊት መኩሪያ ናቸው።
በሀገራችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የንግዱ ዘርፍ ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ እያጋጠመን ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ፣ አምራቾችንና ሸማቾችን በቀጥታ በማናኘት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገበያዩ ለማድረግ በሃዋሳ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የንግድ ሳምንት ኤግዚብሽንና ባዛር ዓላማ ንግድን ለማዘመን፣ ምርትና አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማስፋትና ንግድ በውድድር እንዲመራ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሀገራችንን ምርትና አገልግሎቶች ለማስተዋወቅ፣ በሀገር ምርት መጠቀምን ባህል ለማድረግ፣ የንግድ ዘርፍ ስብራቶችን ለመጠገን፣ ህገ ወጥነትን ለመከላከልና የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን እና የአሰራር ስርዐት ማሻሻያ በማድረግ በሀገራችን ለሁሉም አካል ምቹ የንግድ ከባቢ ለመፍጠር ያግዛልም ብለዋል፡፡
ከነሐሴ 15 እስከ ጳጉሜ 05/ 2017 ዓ.ም በሚካሄደው ባዛርና ኤግዚብሽን በአምራች፣ በጅምላ አከፋፋይ ነጋዴዎች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት አምራቾችና አቅራቢዎች፣ የማኑፋክቸሪንግና የእንስሳት ተዋጽኦ ውጤቶች እንዲሁም ኤክስፖርት የሚደረጉ የግብርና ምርቶች ቡና፣ ቦሎቄ የቆዳ ውጤቶች በተጨማሪም የዕለት ተዕለት የፍጆታ ምርቶች በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ማህበረሰብ ለእይታና ለግብይት ቀርበዋል፡፡
በተለይም የአካባቢውን ህብረተሰብ በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የሰንበት ገበያዎች ዩኒዬኖች በኤግዚብሽኑ ተሳታፊ ስለሆኑ ሸማቹ ማህበረሰብ በዝቅተኛ ዋጋ የሚፈልገውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ በአንድ ማዕከል እንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል ሲሉም ወይዘሮ ሰላማዊት አስረድተዋል፡፡
ኃላፊዋ አክለውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገር አቀፍ እና በሲዳማ ክልል የተጀመረው የሀገር ውስጥ ምርት አምራቾችን ከማነቃቃት አንፃር ሰፊ ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን ህብረተሰቡ የሀገርን ምርት የመጠቀም ባህልን እንዲያዳብር በማድረግ ረገድ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የንግድ ሳምንት አምራቾች፣ አስመጪና ላኪዎች እንዲሁም የህብረት ሥራ ማህበራትን ጨምሮ የንግዱ ዘርፍና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ መሆናቸውም ተጠቁሟል።
በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ የክልሉ ዋና አፈጉባኤ ወ/ሮ ፋንታዬ ከበደን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ ከዞኖች፣ ከወረዳዎችና ከከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት መሳተፋቸውን ለማወቅ ተችሏል።
More Stories
“አካል ጉዳተኛ መሆኔ ከቀጣይ የህይወት ጎዳና አላስተጓጎለኝም” – አቶ አማን ቃዊቲ
“በሀገር ሠርቶ መለወጥ ይቻላል” – ወ/ሮ መህቡባ ሁሴን
“ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል” – አቶ አስፋው ጎኔሶ