ሰልጣኞችን ከስራ ጋር ለማስተሳሰር የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ
ኮሌጁ “ትምህርትና ስልጠና ለስራ” በሚል መሪ ሀሳብ በ“EASE” ፕሮጀክት ድጋፍ ከኢንዱስትሪ አማካሪ ቦርድ አባላት ጋር የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል።
የመድረኩ ዓላማ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም መገምገምና በቀጣይ ዓመት ሰልጣኞችን ከስራ ጋር ለማገናኘት ከኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መወያየት መሆኑ ተገልጿል።
በመድረኩ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮሌጁ ዲን አቶ አንዱዓለም ገብረመድህን፤ በፕሮጀክቱ ድጋፍ ሰልጣኞችን ከስራ ጋር ማስተሳሰር መቻሉን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በኮሌጁ ስራ ከጀመረ ወዲህ 88 ሰልጣኞችን ከስራ ጋር ማገናኘት ተችሏል ብለዋል።
ሰልጣኞች ከስራ ጠባቂነት በመላቀቅ ስራ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ የሚያስችሉ የክህሎት ስልጠና በፕሮጀክቱ ታግዞ ሲሰጥ እንደነበርም አንስተዋል።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ብሩክ ዓለማየሁ፤ በፕሮጀክቱ በጀት ድጋፍ አጫጭር ስልጠናዎች ለአሰልጣኝ ኢንስትራክተሮች መሰጠቱን ተናግረዋል።
በፕሮጀክቱ በጀት የተጀመሩ ተግባራት በቀጣይ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ በኮሌጁ በፕሮጀክቱ ድጋፍ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የኢንዱስትሪ አማካሪ ቦርድ አባላት፣ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች እና የኮሌጁ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ: ሀብታሙ ኃይሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ በመንገድ መሠረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሰኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አሰታወቀ
ሳውላ ከተማን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ የማድረግ የ5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እየተካሄደ ነው
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማትና ሰላምን በማጽናት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል