‎ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የብልጽግና ችቧችን ነው – አቶ እንዳሻው ሽብሩ

‎ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የብልጽግና ችቧችን ነው – አቶ እንዳሻው ሽብሩ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የብልጽግና ችቧችን መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ ገለጹ።

በመሪዎች ቅብብሎሽና በሳል አመራር ሰጭነት በመላው ኢትዮጵያዊያን በይቻላል መንፈስ እውን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፤ የትኛውንም ግዙፍ ልማት በራሳችን አቅም መፈፀም እንደምንችል ያረጋገጥንበት፣ በእኛው ለእኛውና ለአፍሪካውያን ትልቅ ዕድልን ይዞ የመጣ ልዩ አሻራችን መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ ተናግረዋል።

ምንም ያህል በግራና በቀኝ ግድቡ ተገንብቶ እንዳይጠናቀቅ የሚጎትቱ አካላት ቢኖሩም ከማጠናቀቅ ማስቆም እንደሚይችሉ ኢትዮጵያዊያን አረጋግጠዋል ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ ለመላው ኢትዮጵያዊያን እንኳን ደስ አለን ብለዋል።

የጂኦ ፖለቲካ ሥርዓት በመላው ዓለም በእጅጉ ተቀባይነት እንዲያገኝ በሳል አመራር የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ ግድቡ ካለበት ችግር ወጥቶ ዛሬ ላይ እንዲደርስ ከፍተኛ ሀላፊነት ተወጥተዋል ሲሉም አቶ እንዳሻው ጠቅሰዋል።

የገደብነው ኢትዮጵያዊያን ካለብን የኢኮኖሚ ችግር ለመላቀቅ እንጂ ማንንም ለመጉዳት ባለመሆኑ የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት የግድቡ መጠናቀቅ ተጨማሪ የትስስርና በጋራ የመበልፀግን መርህን ከያዘው ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጎን መቆም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ኃላፊው።

ለበርካታ ዓመታት ቦንድ በመግዛት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የገለፁት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ነቢዩ ቤዛ ናቸው።

ከተባበርንና ከተደማመጥን የማናሳካው ተአምር የለም ያሉት አቶ ነቢዩ፤ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠናቀን ሌላ ግዙፍ ጀምረን እንደምንጨርስ ምንም ጥርጥር የለውም ብለዋል።

በአንድ በኩል ለግድቡ ገንዘብ በማዋጣት ቦንድ በመግዛት፤ በሌላ በኩል የቁጠባ አቅማችንን ከፍ ለማድረግ ግድቡ አስተማሪ የሆኑ ቁም ነገሮችን እንድንጨብጥ አስተምሮናል ሲሉም ኃላፊው ገልፀዋል።

መላው ኢትዮጵያዊያን ከፊታችን የሚታይ ትልቅ ተስፋና ብሩህ ራዕይ ያለን በመሆኑ ለልዩነት ከሚጋብዙ ሐሳቦች ወጥተን ይበልጥ አንድነታችንን አጠናክረን ብልጽግናችንን ለዓለም ህዝብ ልናረጋግጥ ይጠበቅብናል ብለዋል።

የህዳሴ ግድቡን እንዳሳካን ሁሉ ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት እንድትሆን ሁላችንም ድጋፋችንን እንሰጣለን ሲሉ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን