የደመወዝ ጭማሪ ምክንያት በማድረግ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ ተገቢነት የሌለው መሆኑ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመንግስት ሠራተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተደረገውን የደመወዝ ጭማሪ ምክንያት በማድረግ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ ተገቢነት የሌለው መሆኑ ተገለፀ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠምባሮ ልዩ ወረዳ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውንና ነጋዴዎቹ በገንዘብ መቀጣታቸውን የልዩ ወረዳዉ ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት አስታውቋል።
በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ካሉ ታዳጊ ከተማዎች መካከል ቀለጣና ሆዶ ከተማዎች በተደረገዉ ድንገተኛ ፍተሻ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ የንግድ ተቋማትን የማሸግና በገንዘብ የመቅጣት ሥራ መሰራቱን የልዩ ወረዳው ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተመስን ዓለማየሁ ተናግረዋል።
ለመንግስት ሠራተኞች ከመስከረም ወር ጀምሮ ደመወዝ እንደሚጨምር መንግስት ማሳወቁን ተካትሎ አንዳንድ ነጋዴዎች ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ እንዳሉ ገልፀዉ፥ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎችን ተከታትሎ የማረም ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል ።
የዋጋ ጭማሪ፣ሚዛን ማጭበርበርና ህጋዊ ፍቃድ ሳይዙ በንግድ ስራ መሰማራት ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ መሆናቸውን ኃላፊው አመላክተዋል።
ምክንያታዊ ያልሆነ ዋጋ በእቃዎች ላይ የሚጨምሩ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ስለሚኖሩ በዘርፉ ግብረ ኃይል በማቋቋም በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ የንግዱ ማህበረሰብ ዋጋ በመጨመር ከሚደርሰው ቅጣት እራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል ።
ይህ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አቶ ተመስገን አመላክተዋል።
በዋጋ ጭማሪ፣ በሚዛን ማጭበርበርና ያለ ንግድ ፍቃድ በሚሠሩ የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ከ10ሺ እስከ 12 ሺህና ከዛ በላይ ህጋዊ የቅጣት እርምጃዎች መወሰዳቸውን ያነሱት አቶ ተመስገን፥ ሸማቹ ማህበረሰብ በግብይት ወቅት በእቃዎችም ሆነ በእህል ላይ ዋጋ ተጨምሮ ሲገኝ ለህጋዊ አካል ጥቆማ ማድረስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
ክልሉ ከተደራጀ ወዲህ የአካባቢው ኢኮኖሚ መነቃቃቱን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ
ህብረት ስራ ማህበራት በተደራጁበት ዓላማ ለአባሎቻቸው የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በጠንካራ አደረጃጀትና ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ሊደገፉ እንደሚገባ ተመላከተ
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን በማሳደግ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ የከተማው ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ገለፁ