ክልሉ ከተደራጀ ወዲህ የአካባቢው ኢኮኖሚ መነቃቃቱን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ
መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች እጥረት እንዳይከሰትና ህገ-ወጥነት እንዳይስፋፋ እየተሰራ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ ተናግረዋል።
ቢሮው የንግዱን ማህበረሰብ ቁጥር የማሳደግና ነባር የንግድ ፈቃድ ዕድሳትን በማከናወን የነጋዴዎችን ቁጥር ከ60 ሺህ በላይ ማድረሱን ተናግረዋል።
ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ወደህጋዊ የንግድ ስርዓት እንዲገቡ ማድረግ እና ኮንትሮባንድን በመከታተል የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ትኩረት የተሰጠባቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።
የፍጆታ ምርቶች ፍላጎት አቅርቦትና ስርጭት በጥንቃቄ እየተመራ ነው ያሉት አቶ ተመስገን ፤ ከተረጂነት መላቀቅና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ትኩረት መደረግ አለበት ብለዋል።
ከባዕድ ነገሮች ጋር የተደባለቁ እንዲሁም የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያበቃና በገበያ ላይ እንዳይውሉ የተከለከሉ ሸቀጦችና ምርቶች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል።
እነዚህ ችግሮች የበዓል ገበያን ተከትሎ በህዝብ ጤና እና ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ሳያደርሱ አስቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ምርትን በመደበቅና በማከማቸት የዋጋ አለመረጋጋት የሚፈጥሩ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል፡፡
ለመንግስት ሠራተኛው የደመወዝ ጭማሪ እንደሚደረግ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሚሳተፉ ግለሰቦችና ድርጅቶች መኖራቸውን የገለጹት የቢሮ ኃላፊው ፤ ለመከላከል ተግባር ቅድሚያ መሰጠቱን አስታውቀዋል።
የደመወዝ ማሻሻያን ተከትሎ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሕብረተሰቡ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉና ምርቶችን የሚያከማቹ ነጋዴዎችን ሲመለከት ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
ህብረት ስራ ማህበራት በተደራጁበት ዓላማ ለአባሎቻቸው የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በጠንካራ አደረጃጀትና ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ሊደገፉ እንደሚገባ ተመላከተ
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን በማሳደግ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ የከተማው ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ገለፁ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር አክልሉ አዳኝ ማህበረሰቡን ከቱርካና ሐይቅና ከኦሞ ወንዝ ሙላት ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በስፍራው በመገኘት ተመለከቱ