ህብረት ስራ ማህበራት በተደራጁበት ዓላማ ለአባሎቻቸው የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በጠንካራ አደረጃጀትና ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ሊደገፉ እንደሚገባ ተመላከተ

ህብረት ስራ ማህበራት በተደራጁበት ዓላማ ለአባሎቻቸው የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በጠንካራ አደረጃጀትና ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ሊደገፉ እንደሚገባ ተመላከተ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 27/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ህብረት ስራ ማህበራት በተደራጁበት ዓላማ ለአባሎቻቸው የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በጠንካራ አደረጃጀትና ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ሊደገፉ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ አሳሰቡ።

በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የሚገኘው አግኖት ኃላፊነቱ የተወሰነ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ዩኒየን 10ኛ ዙር ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሔደ ይገኛል።

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ አግኖት ኃላፊነቱ የተወሰነ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ዩኒየን ቁጠባን በማሰባሰብና ብድርን በማሰራጨት የአባላቱን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱም 28 ሚሊዮን ብር ቁጠባ በማሰባሰብ አዋጭ በሆኑ በግብርና፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ቢዝነስ ፕላኖች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር በማሰራጨት ለአባላቱ የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ህብረት ስራ ማህበራት በተደራጁበት ዓላማ ለአባሎቻቸው የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በጠንካራ አደረጃጀትና ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ሊደገፉ ይገባል ሲሉም አቶ አበራ አሳስበዋል።

አግኖት ኃላፊነቱ የተወሰነ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ዩኒየን በ2005 ዓ.ም በአዲስ መልክ ሲደራጅ የሥራ ክልሉን ወልቂጤ ከተማ አስተዳደርና በጉራጌ ዞን ውስጥ የሚገኙ 10 ወረዳዎችን በማድረግ በ120 ሺህ ብር መኘሻ ሀብት እና በ22 ህብረት ስራ ማህበራትን በማቀፍ ነበር።

አሁን ላይ የሥራ ክልሉን ጉራጌ ዞን እና ቀቤና ልዩ ወረዳን በማድረግ 312 ህብረት ስራ ማህበራትና 105 ሺህ 841 የተናጥል አባላትን በማቀፍ ካፒታሉንም 100 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር አድርሷል።

ለአባላቱ የተሟላ የፋይናንስ አገልግሎት በመስጠት ቀጣይነት ያለው፣ ተደራሽ፣ ተመራጭና ተወዳጅ ህብረት ስራ ባንክ ሆኖ የማየት ርዕይ አንግቦ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ዩኒየኑ አባላቱን በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትራንስፖርት፣ በእደ ጥበብ እና በሌሎችም አዋጭ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው የገቢ ምንጫቸውን እንዲያሳድጉ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ እንደሚገኝ የዩኒየኑ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ እንዳለ ዓለሙ ጠቁመዋል።

በጉባኤው የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ኸይሩ መሀመድ፣ የዞኑ የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የዩኒየኑ አባላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

ዘጋቢ፡ ተረፈ ሀብቴ – ከወልቂጤ ጣቢያችን