“አካል ጉዳተኛ መሆኔ ከቀጣይ የህይወት ጎዳና አላስተጓጎለኝም” – አቶ አማን ቃዊቲ
በገነት ደጉ
ሰዎች የአካል ጉዳት አለባቸው ሊባል የሚችለው ሰዎቹ ራሳቸውን ለመንከባከብ፣ በእግር ለመጓዝ፣ ባሉበት አካባቢ ለመንቀሳቀስ፣ ለመስማት፣ ለማየት፣ በግልጽ ለማሰብ ወይም ለመማር ከባድ ሆኖ ሲገኝ ነው።
በአንድ ሰው ህይወት አካል ጉዳተኝነት ሊከሰት የሚችለው በአደጋ፣ እጅግ አሳዛኝ በሆነ ገጠመኝ፣ በበሽታ ወይም በተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ አካል ጉዳተኝነት አብዛኛውን ጊዜ ለረጅም ጊዜ የሚቆይና ቀጣይነት ያለው እስከ ህይወት መጨረሻ አብሮ የሚቆይ ነው። ስለዚህ አካል ጉዳተኝነት ለተወሰነ ወራት የሚቆይ የህመም ዓይነት አይደለም።
የሰው ልጆች በህይወት እስካለን ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች የአካል ጉዳት ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ትልቁ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ የሚደርስባቸውን የአካል ጉዳት ተቀብሎ ለውጤት የማብቃት ጉዳይ ነው፡፡
የዛሬው የችያለሁ ዓምድ ባለታሪካችን የአካል ጉዳት ካደረሰባቸው ድባቴ ራሳቸውን አሳምነው ወደ ወትሮ ስራቸው ለመግባትና ውጤታማ ለመሆን ጊዜ እንደወሰደባቸው ነው የሚናገሩት፡፡
አቶ አማን ቃዌቲ ይባላሉ፡፡ ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ልዩ ስሙ ሻላ ተብሎ በሚጠራው ቆቦ ሌማን ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡
ባልታወቀ ምክንያት ከዛሬ ስድስት ወር በእግራቸው ላይ ህመም ሲደርስባቸው ቆይተው በህክምና ቢረዱም መፍትሔ በማጣት የግራ እግራቸውን በአጋጣሚ መቆረጣቸውን ነው የሚናገሩት፡፡
ከስድስት ወር በፊት ታመው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በህክምናው ሲረዱ ቆይተው ካንሰር ሊሆንና ወደ ሌላው ሊሰራጭ ስለሚችል ተስፋ የለውም ተብሎ የግራ እግራቸውን እንደተቆረጡ ነው አቶ አማን የሚናገሩት፡፡
ባለትዳር እና የስምንት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አማን በግብርናው ስራ ይተዳደሩ እንደነበር ነው ያጫወቱን፡፡ በወቅቱ ሁኔታዎች ከባድ በመሆኑም የማይቻል ነገር የለምና ቀስ በቀስ ራሳቸውን በማሳመን ልጆቻቸውን እንዴት ማሳደግ እንዳለባቸው አስበውና አሳምነውን ወደ ቀድሞው ስራቸው መግባታቸውን ነው የገለፁት፡፡
“ስረዳው እና ወደ ቀልቤ ስመለስ አካል ጉዳተኛ ማለት ምንም ማለት እንዳልሆነና ከአላህ የተሰጠ ነው ብዬ ነው የተቀበልኩት” ያሉት አቶ አማን ከአካል ጉዳት ጋር አብሮ ህይወትን መቀጠል እንደሚቻል ነው የሚናገሩት፡፡
አካል ጉዳተኛ መሆን ህይወት እንዳትቀጥል አያደርግም የሚሉት አቶ አማን ያጣሁት እግሬን እንጂ አዕምሮዬን ወይንም ሙሉ አካላቴን አይደለም በማለት በብርታትና በጽናት ተናግረዋል፡፡
አካባቢው ኦሮሚያ ክልል ይሁን እንጂ ለሀላባ ዞን ቅርብ በመሆኑ በበቆሎ እና በበርበሬ የሚታወቅ ሲሆን የተፈጥሮ ፀጋውን በመጠቀም በስፋት እያመረቱ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት፡፡
ከጉዳት በፊት ከልጆቻቸው ጋር አብረው በጋራ እንደሚያርሱ የሚናገሩት አቶ አማን አሁንም በአርባ ምንጭ ተሀድሶ ማዕከል የሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ ለማሰራት የመጡት እንደ ቀድሞው በሙሉ አቅማቸው የግብርናውን ስራ ለመስራት እንዲያስችላቸው በማሰብ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ይህ ይደርስብኛል ብዬ አስቤም አላውቅም የሚሉት አቶ አማን አሁን ላይ ተበሳጭተው ምንም ሊያመጡና ሊጨምሩ የሚችሉት ነገር እንደሌለ በማስተዋል ከስድስት ወራት በኋላ ወደ ራሳቸው ቀልብ መመለሳቸውን ነው የገለፁልን፡፡
“አካል ጉዳተኛ መሆኔ ከቀጣይ የህይወት ጎዳና አላስተጓጎለኝም። ከዚህም በኋላ ምንም የሚያግደኝ ነገር የለም” ያሉት አቶ አማን የሰው ሰራሽ አካል ድጋፉን ካገኘሁ ያሰብኩትን ማሳካትም ሆነ ልጆቼን አርሼ በማብላትና ቀሪውን ለገበያ በማቅረብ እቅዶቼን ከግብ ለማድረስ እችላለሁ በማለት ያላቸውን ጥንካሬ ነው ያስረዱን፡፡
ጉዳቴ ሰዎች የደረሱበት መድረስና ያቀድኩትን እቅድ ማሳካት አይከለክለኝም ያሉት አቶ አማን ከዚህም በኋላ ሁሉንም ነገር እሰራለሁ፡፡ የማሳካውም ገና ብዙ ዓላማ አለኝ በማለት ነው የተናገሩት፡፡
“ተቀምጬ መኖርን አልመርጥም። አላህ ያግዘኝ እንጂ የሰውን እገዛ እና ድጋፍን መጠበቅም ሆነ መስማትን ህልሜ አላደርገውም” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
“በእስልምናው እምነት አቅም እያለው ተቀምጦ መለመንን አይደግፍም። መኖርም ሆነ ሁሉንም ለማድረግ የደረሰብኝ ጉዳት አይከለክለኝም። ልመና ውስጥ ከመግባት ሞትን እመርጣለሁ፡፡” ሲሉም አክለዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ተሀድሶ ማዕከል ለሰው ሰራሽ ድጋፍ ቢያንስ ቁስል እስኪደርቅ ስድስት ወራት መቆየት አለብህ የተባሉት አቶ አማን እስከዚያም ድረስ በራሳቸው ክራንች በማሰራት ወደ ስራ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡
ሰው በሰው የአርባ ምንጭ ተሀድሶ ማእከል ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ እንደሚሰጥ በጥየቃ ከደረሱ በኋላ ወረፋ ይዘው መምጣታቸውን ተናግረው ሰው ሰራሽ እግር ከወሰዱ በኋላ ወትሮ ሲሰሩ የነበረውን የእለት ተእለት ተግባራቸውን በማከናወንና ከማንኛውም ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ እንደቻሉ ነው ያስረዱት፡፡
ፈጣሪ እስካኖራቸው ድረስ ምንም ዓይነት ነገሮችን ማሰብ እና ማሰላሰልን እንደማይፈልጉና በተስፋ መኖርን እንደሚመርጡ ተናግረው ከዚህም በላይ ያለውን የበርበሬ ማሳዎችን በሰውም ሳያሰሩ በራሳቸው ጉልበት ለመስራት እንዳዘጋጁ ነው የጠቀሱት።
ከእርሳቸው ይልቅ ባለቤታቸው እና ልጆቻቸው ጉዳቱ ሲደርስባቸው እንደተበሳጩ እና ህይወት እዛው ጋር እንዳበቃ ነበር ያሰቡት። እኔ ግን ራሴን በማረጋጋት እነርሱ በጉዳዩ እንዲያምኑ እና መኖርንና መስራትን ደግሞም እንደ ቀድሞው መሆን እንደምችል ያለመንገር ነው ያበረታታሁት ሲሉም ተናግረዋል፡፡
እራሳቸውን ለማብቃትና ህክምናውን የተሻለ ሊሆን ይችላል በማለት እቤት ያለውን ሀብት ንብረታቸውን ሙሉ እንዳጡና ነገም ሌላ ህይወት እንደሌለ ባለቤታቸው እንዳሰቡና መስራት ሲችሉ ግን ተስፋቸው እንደለመለመ ብሎም አካል ጉዳተኛም መስራት ይችላል የሚለው እሳቤ ላይ መድረሳቸውን ነው ያስረዱት፡፡
አቶ አማን ከጊዜ በኋላ የደረሰባቸውን የአካል ጉዳት ለመቋቋም እጅግ ቢፈትናቸውም እንኳን ህይወት እንደምትቀጥልና ነገም ሌላ ህይወት እንዳለ በማመን በቁርጠኝነት እና በልበ ሙሉነት ወደ ቀድሞ የግብርና ስራ ተሰማርተው ዛሬ ላይ ሙሉ ቤተሰቡም ተጽናንቶ ወደ ስራ እንዲገቡ መንገድ መሆናቸውን አጫውተውናል፡፡
“መኖር ስላለብኝ እንጂ ያ ሁሉ አልፎ ዛሬ ላይ እደርሳለሁ ብዬ አላሰብኩም” ያሉት አቶ አማን ህይወት በዚያ መንገድ እንደማይቀጥል እና ያለፈን መመለስ እንደማይቻል በመረዳት አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር ወስነው መግባታቸው እንደጠቀማቸው ነው ያጫወቱን።
አቶ አማን የአካል ጉዳት ያለበት ሰው መስራት እንደሚችል በጥንካሬ ሰርቶ ማሳየት እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
More Stories
“በሀገር ሠርቶ መለወጥ ይቻላል” – ወ/ሮ መህቡባ ሁሴን
“ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል” – አቶ አስፋው ጎኔሶ
“ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በክልሉ ምቹ የንግድ አካባቢ እንዲፈጠር አስችሏል” – የሲዳማ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ