“ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል” – አቶ አስፋው ጎኔሶ   

                                                                                                

በመሐሪ አድነው

መንግስት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እና የሀገር ውስጥ ምርትን በበቂ ሁኔታ ለማሳደግ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

በዚህም ባለፈው ዓመት ከአራት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል፡፡

የሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገት ዋና ማሳያ የምርት እድገት በመሆኑ፣ መንግስት በሂደት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር አንዱ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ እየሰራበት ነው። ለአብነትም በመጪዎቹ አምስት አመታት ውስጥ በሁሉም የሀገሪቱ ወረዳዎች ውስጥ አንድ ኢንተርፕራይዝ ለማቋቋም በእቅድ ተይዟል፡፡

የሀገሪቱን ምርት በማሳደግና ገቢዉ እንዲጨምር በማድረግ አዳዲስ የሥራ እድል እንዲፈጠር፣ የዜጎች ፍላጎት የሚያሟሉ ሸቀጦችና አገልግሎቶችን ማቅረብ ያስችላል፡፡ ይህ ሲሆን የዜጎች ኑሮ እየተሻሻለ፣ ድህነትም እየቀነሰ ይመጣል ማለት ነዉ፡፡

ኢትዮጵያም ሁሉንም ነገር አምርታ በራሷ መሸፈን የምትችልበት ሁኔታ አዳጋች ስለሆነ ምግብና ምግብ ነክ በተለይ ስንዴና ገብስ፣ መድሃኒት፣ የዘይት ምርቶችና የመሳሰሉ ዋነኛ ምርቶች ላይ ራሷን ለመቻል በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡

በተለይ እንደ ሀገር ያለንን አቅም መለየትና ገቢ ምርቶችን ለመተካት እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ምርቶቻችንን ለመሸጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ፣ ሰፊ የስራ እድል መፍጠርና ዜጎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዲችሉ እያደረገ ይገኛል።

ሀገሪቱ ለገቢ ምርቶች የምታወጣውን ወጪ ለመቀነስ ተኪ ምርቶችን በብዛት፣ በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡ ይህም በሀገሪቱ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑ ይታመናል፡፡

የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የ2017 ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት አመት መሪ ዕቅድ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

በዚህ ወቅት በብልጽግና ፓርቲ ሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ፓለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስፋው ጎኔሶ በመድረኩ መክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ የክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በ2017 በጀት አመት ጨምሮ ባለፉት አራት አመታት በአፈጻጸም በሀገር ደረጃ ግንባር ቀደም መሆኑን ጠቁመው፣ በዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰሩ ስራዎችን ጠንክሮ በመስራት ረገድ በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ባለሙያዎች በቀጣይም በጋራ ተቀናጅተው ለተሻለ አፈጻጸም መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

አቶ አስፋው አያይዘውም በሚቀጥለው ጊዜ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን በማምረት የውጪ ምንዛሬ በማስገኘት፣ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር በቀል ምርቶች በመተካት እንዲሁም ዘርፉ ከሌሎች ከግብርና፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ጋር ጠንካራ ትስስር ፈጥሮ በመስራት የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግብ የዘርፉ አመራርና ባለሙያዎች በጥንካሬ እንዲፈጽሙ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና በ2017 በጀት አመት ተቋሙን ለመገንባትና በዘርፉ አምስት ስትራቴጂክ ግቦች ልዩ ትኩረት ሰጥተን በሂደቱም በኢንዱስትሪ ዘርፍና የኢኮኖሚ ሽግግር ለማረጋገጥ እንዲሁ ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር በተሰሩ ስራዎች የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ከአምናው አፈጻጸም የተሻለ ውጤት አስመዝግበን ለእውቅናና ሽልማት በቅተናል ብለዋል።

አቶ ጎሳዬ አክለውም ከዚህ በፊት በዚያ ደረጃ ትኩረት ያልተሰጠውና እንደ ሀገርም እንደ ክልልም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራው ተኪ ምርቶችን የማምረት ስራ ነው ብለዋል፡፡ ተኪ ምርት ከኤክስፖርት ጋር እኩል ትኩረት አግኝቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ከፋይዳውም አንጻር ሲታይ የውጭ ምንዛሪ ከማዳንም ሆነ ከማግኘት ረገድ በክልል ውስጥ ከአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የተለያዩ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ፣በኬሚካልና ኬሚካል ውጤቶች፤ እንደዚሁም በቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ማምረት የተቻለበት እደሆነ አብራርተዋል፡፡

እስትራተጂክ ግብ ተብሎ የሚታሰበውና በዚያ ዙሪያ እየተሰራ የሚገኘው ደግሞ ከኤክስፖርት ጋር ተያያዥ በሆነው ስራ ወደ ሃምሳ አራት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማስገኘት መቻሉንም የጠቀሱት አቶ ጎሳዬ ከዚህ ውስጥ የይርጋዓለም አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ሲሆን ከፓርክ ውጭ በአጠቃላይ እንደ ክልል ተመርቶ ወደ ውጭ በመላክ ወደ ሃምሳ አራት ሚሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሉንም አስረድተዋል፡፡

ሌላኛው ቁልፍ ስራ ተብሎ የተጠቀሰው የስራ ዕድል ፈጠራ ሲሆን ቋሚና አስተማማኝ የስራ ዕድል እንደ ሀገር እስትራቴጂክ እቅድ ላይ ወደ አምስት ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጠራል ተብሎ የታሰበ መሆኑ ይታወቃል፡፡የሲዳማ ክልልም በ2017 በጀት አመት ላይ ሃያ አንድ ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ18 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡ በዚህም የዕቅዱን 85 በመቶ ተፈጽሟል ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ከተለያዩ ባንኮችና ከማሽን አቅራቢ ተቋማት ለሊዝ ፋይናንስ ማሽነሪ አቅርቦት ወደ ሁለት ቢሊዮን የሚጠጋ ብርም ማቅረብ ተችሏል ሲሉም አቶ ጎሳዬ አክለው ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አመታት ያስመዘገብነው ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ በሚቀጥለው 2018 በጀት አመት በአፈጻጸም ያሳየነውን ጠንካራ ጎናችንን አጠናክረን በማስቀጠል በክልሉ ያለውን ዘርፈ ብዙ ምቹ ሁኔታዎችን በሙሉ አሟጠን በመጠቀም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት መፈጸም ይጠበቅብናልም ብለዋል።

በክልሉ የማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መንግስቱ ማቴዎስ እንዳሉት በዞኑ የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ መገንባትን ተከትሎ በአምራች ዘርፉ ላይ ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጥሯል።

ፓርኩ የአርሶ አደሩን ምርቶች በመቀበል አቀናብሮ ለገበያ በማቅረብ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

ፓርኩ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማድረግ ባለፈ በፈጠረው የገበያ ትስስር አርሶ አደሩ ከ1 ሺህ በሚበልጡ ማህበራት ተደራጅቶ ምርቱን እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ በሀይሉ ጌታቸው በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በከተማው 60 አዳዲስ አነስተኛ እስከ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ተቋቁመው ወደ ሥራ ገብተዋል።

ኢንዱስትሪዎቹ በአልባሳት፣ በግንባታ ምርቶች፣ በምግብ እና በሶላር ምርት ላይ እንደተሰማሩ ጠቅሰው፣ በዋናነት ተኪና ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችን በማምረት ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ ሥራ በገቡ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ኢንዱስትሪዎች ከ18 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩ በጉባኤው ተገልጿል።

ቢሮው ከ2014 በጀት አመት ጀምሮ በተሻለ አፈጻጸም ባስመዘገበው አመርቂ ውጤት ለአራት ተከታታይ አመታት በሀገር ደረጃ ለእውቅናና ሽልማት በቅቷል።

ቢሮው በ2017 በጀት አመት በመደበኛ ስራዎች አፈፃፀም የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ከአንድኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን ለያዙ ዞኖች፣ የክልሉ ቢሮ ዳይሬክተሮችና ባለሙያዎች እውቅናና ሽልማት አበርክቷል።