“ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በክልሉ ምቹ የንግድ አካባቢ እንዲፈጠር አስችሏል” – የሲዳማ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ

በመሐሪ አድነው

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ምቹ የንግድ አካባቢ በመፍጠር ዘርፈ ብዙ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማገዙን የሲዳማ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ።

ከነሐሴ 15 ጀምሮ እስከ ጳጉሜ 5 ድረስ በሚቆየው ”የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን አውደ ርዕይና ባዛር በማስመልከት የክልሉ ገበያ ልማት ቢሮ ከክልሉ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በመሆን ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የቢሮው ሃላፊዋ ሰላማዊት መኩሪያ እንደገለጹት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በክልሉ ምቹ የንግድ አካባቢ በመፍጠር ዘርፈ ብዙ ውጤቶች እንዲመዘገቡ እያገዘ ነው፡፡

በክልሉ ምርታማነትን ለማሳደግ ተኪ ምርቶች ላይ በማተኮር በግብርናው እና በኢንዱስትሪው ዘርፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ለምርቱ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ቢሮው የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው ነሐሴ 15 ቀን 2017 የሚከፈተው ”የኢትዮጵያን ይግዙ” አውደ ርዕይና ባዛር የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

አውደ ርዕይና ባዛሩ በክልሉ የሚመረቱ ወደውጭ የሚላኩ ምርቶችን በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ያለመ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ቡናን ጨምሮ የፍራፍሬ ውጤቶች፣ ማርና የማዕድን ውጤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ በማቅረብ ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ የገበያ ትስስር የመፍጠርና ልምድ የመለዋወጥ ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል።

በአውደ ርዕይና ባዛሩ ከ213 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ህብረት ሥራ ማህበራት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ትላልቅ ድርጅቶችና በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የሚነግዱ አካላት ጭምር ይሳተፋሉ ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዘሪሁን ቃሚሶ በበኩላቸው እንዳሉት ”የኢትዮጵያን ይግዙ” አውደ ርዕይና ባዛር በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምንና በሀገር ምርት የመጠቀም ልምድን ለማሳደግ የሚያግዝ ነው፡፡

በተጨማሪም መጪውን አዲስ ዓመት ታሳቢ ያደረጉ ምርቶች በስፋት እንዲቀርቡ በማድረግ ገበያን ለማረጋጋት ምክር ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ከውጭ የሚገባውን በመተካት ከፍተኛ ወጪን ከመቀነስ ባለፈ የሚፈጥሩት የስራ እድል ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ባዛርና አውደ ርዕዩ በዘርፉ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋትም ያግዛል ብለዋል፡፡

የዘንድሮውን ባዛር ለየት የሚያደርገው የኢትዮጵያን ይግዙ የሚለውን የክልሉ መንግስትና የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጅት በሚያደርግበት ወቅት መሆኑን አቶ ዘሪሁን አንስተዋል፡፡

ከነሃሴ 15 እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በሃዋሳ ሚሊኒየም አደባባይ እየተካሄደ ባለው አውደ ርዕይና ባዛሩ ላይ ሸማቹ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።