“በሀገር ሠርቶ መለወጥ ይቻላል” – ወ/ሮ መህቡባ ሁሴን

“በሀገር ሠርቶ መለወጥ ይቻላል” – ወ/ሮ መህቡባ ሁሴን

በሙናጃ ጃቢር

የሰው ልጅ ለመኖር መብላት አለበት፤ ለመብላት ደግሞ ሠርቶ መኖር ግድ ይላል። በስራው በሚያገኘው ገቢ ፍላጎቱን ለማሟላት ይፈልጋል፡፡ ያንን ደግሞ በአንድ ጀንበር ማምጣት አይቻልም። በዚህም ምክንያት ቀዳዳው አልሞላ ሲላቸው አንዳንዶች ስደትን አማራጭ ያደርጋሉ፡፡ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ትዳራቸውን እና ልጅ ጥለው የተሰደዱ እናቶች በርካቶች ናቸው።

አንዳንዴ ስደቱም እንዳሰቡት አይሆንም፤ ለዘመናት ሠርተው ለውጥ ሳያመጡ ይቀራሉ። የራሳቸውን ተስፋ ጥለው የቤተሰባቸውን ተስፋ ለማለምለም ቆመው እያንቀላፉ ቀኑ መሽቶ ይነገባቸዋል፡፡ ከሞት መልስ ያሉ ጠባሳዎችን ተቋቁመው ዳግም በሀገራቸው ሠርቶ መለወጥ እንደሚቻል በተግባር ያሳዩ እንስቶች ደግሞ አልጠፉም።

የዛሬ የእቱ መለኛ አምድ ባለታሪካችን ከስደት እንግልት ወደ ሀገሯ ተመልሳ ታሪክ የሠራች ስልጢ ወረዳ የፈራቻት ጀግና ሴት አርሶ አደር ናት፡፡ ቀን ከለሊት ሳትል በመስራት ከራሷ አልፋ ለህዝብ በመትረፍ ለሴት ስደተኞች ተምሳሌት መሆን ችላለች፡፡

ወ/ሮ መህቡባ ሁሴን ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው በስልጤ ዞን ምስራቅ ወረዳ ሰዳ ጎራ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ ባለትዳር እና የአምስት ልጆች እናት ናት፡፡

እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ በሰዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 3ኛ ክፍል ተምራለች፡፡ ከዚያም በኋላ ትምህርቷን አቋርጣ ትዳር መሰረተች፡፡

የምትተዳደረው በግብርና ነበር፤ ይሁን እንጂ በኑሮዋ ደስተኛ አልነበረችም፡፡ አረብ ሀገር ሄደው የመጡ ጓደኞች ስለነበሯት የእነሱን ጥሩ ኑሮ መኖር ትመኝ ነበር፡፡ ምኞቷን እውን ለማድረግም ከባለቤቷ ጋር ተማክራ ባለቤቷ ሳውዲ አረብያ እንዲሄድ ተስማሙ፡፡

ባለቤቷም ሳውዲ ሄዶ መስራት ጀመረ። እንዳሰቡት ግን አልሆነም። ባለቤቷ ሥራው ከበደው፡፡ እኔ ማገዝ አለብኝ ብላ ተከትላው እሷም ሄደች፡፡ በአረብ ሀገር ባለቤቷ እረኝነት እየሠራ እሷ ደግሞ የቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ትሠራ ነበር፡፡

በስደት እንግልት ተስፋ ሳይቆርጡ ጀግነው ነገ የተሻለ ኑሮ ለመኖር መስዕዋትነት ከፍለዋል፡፡ አንዴ ተሰደናል ሰው ምን ይለናል መመለስ የለብንም ብለው ከሞት ጋር ትግል ገብተው ድፍን 10 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ የሳውዲ አረብያ የመኖሪያ ፈቃድ አግኝተው ኑሮዋቸውን እዚያው አድርገው ልጅ ወልደው ይኖሩ ነበር፡፡

“ስደት ለቀናው ብቻ ነው፡፡ የተሰደደ ሁሉ ያልፍለታል ማለት ሞኝነት ነው፡፡ ’እንደ ቤት እንጂ እንደ ጎረቤት አይኖርም’ ይላል ያገሬ ሰው፡፡ ከለምለሚቷ ምድር ወጥቼ ወደ በረሀ ሀገር መሰደድ የቀን ቅዠት ነው፡፡ በእጅ የያዙት ወርቅ ሆኖ ነው እንጂ ነገሩ። አረብ ሀገር ምንም አይነት ሽርፍራፊ ሰዓት አልነበረኝም 24 ሰዓት ነበር የምሠራው፡፡ ሰውነቴ ዝሎ ነበር ወደ መኝታዬ የምሄደው። በዛ ላይ ነፃነት የለም፡፡ የስደት ህይወት ቀዳዳው ብዙ ነው፤ መቼም አይሞላም። እንግልቱ ከባድ ነበር። ሥራ መሥራት በሀገር ሲሆን ያኮራል፤ ተሰዶ መስራት ግን ያዋርዳል፡፡ ክፍያው ጥሩ ሊሆን ይችላል ግን አመለካከታቸው ጥሩ አይደለም። እንደ ባሪያ ነው የሚያዩን የምንራብ፣ የምንጠማ፣ የሚደክመን እና የሚከፋን አይመስላቸውም። ግዑዝ አድረገው ነው የሚቆጥሩን” ስትል የስደትን አስከፊነት በምሬት ትናገራለች፡፡

“ከስደት የተማርኩት ችግርን ብቻ ሳይሆን÷ ልምድ ቀስሜበታለሁ፡፡ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ምንም አይነት ወንዝ የለም፤ ትልቁ በረሀማ አሸዋ መገኛ ነው። ለእጽዋት እንኳን አፈር የሚያመጡት ከሌላ ሀገር ገዝተው ነው። በዚያ በበረሃ እንዴት እንደሚያለሙ ሳይ ህልሜ ሁሉ ወደ ሀገሬ መመለስ ነበር” ስትል በቁጭት ትናገራለች፡፡

ህልሟ በሀገር ሰርቶ መለወጥ ስለነበር ከባለቤቷ ጋር በገዛ ፍቃዳቸው የመኖሪያ ፈቃዳቸውን ቀደው ወደ ሀገራቸው ነበር የተመለሱት፡፡

“ከአረብ ሀገር ስመለስ ምንም ገንዘብ አልነበረኝም፡፡ የነበረኝ ንቄው የሄድኩት መሬት ብቻ ነበር፡፡ ከሰው ላይ 5 ሺህ ብር ተበድሬ አትክልትና ፍራፍሬ ማልማት ጀመርኩኝ” ስትል ሥራ እንዴት እንደ ጀመረች አጫውታናለች፡፡

“የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ለስደት ተመላሾች የስልጠና መርሀ ግብር አዘጋጅቶ ተሳትፌያለሁ፡፡ ስልጠናው በጣም ጠቅሞኛል። የግብርና ግብዓቶችንና ቴክኖሎጂዎችን እንድንጠቀም በማድረጉ የተለያዩ ምርቶችን የበለጠ እንዳለማ አግዞኛል፡፡

“በአሁኑ ወቅት እኔ ጓሮ ምንም ነገር የለም አይባልም፡- የዶሮ እርባታ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የወተት ተዋጽኦ፣ የቡና ተክል፣ እንሰት እና ከብት ድለባ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ እያለማሁ እገኛለሁ፡፡ ከራሴ ከመጠቀም አልፎ ለሌሎች የሥራ እድል መፍጠር ችያለሁ” ስትል በደስታ ስሜት ውስጥ ሆና በኩራት ትናገራለች፡፡

በየቀኑ የወተት ተዋጽኦ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ ለገበያ ታቀርባለች። የቁጠባ ባህል ለማዳበር ከሰፈር የተውጣጡ 35 ሴቶች ጋር የወተት እቁብ ትጥላለች፡፡

ወ/ሮ መህቡባ በምግብ ራሷን ከመቻል ባለፈ ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገበች ትገኛለች፡፡ ዛሬ ላይ በየቀኑ ከምታገኘው ገቢ ቆጥባ ልጆቿ የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ የግል ትምሀርት ቤት ታስተምራለች፡፡ በተጨማሪም ገጠር ላይ ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት የገነባች ሲሆን ከተማ ላይ ደግሞ ቤት መግዛቷንም ጭምር ገልጻልናለች፡፡

“ስራዬ ላይ ውጤታማ እንድሆን የረዳኝ የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ነው። በዚህ አጋጣሚ ሳላመሰግን አላልፍም ምክንያቱም የተለያዩ የዘር ብዜቶችን እና የሙያ ድጋፍ አድርገውልኛል” ብላለች፡፡

“የስደትን ህይወት የቀመሰ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ከስደት መልስ የብዙ ሰው አዕምሮ ይጎዳል፤ የማይሽር ጠባሳ ጥሎ ያልፋል፡፡ ስለዚህ ስደት ላይ ላለሽ እህቴ በሀገር ሠርቶ መለወጥ ይቻላል፡፡ የስደት ኑሮ ካልተመቸሽ ሰው ምን ይለኛልን ትተሽ ወደ ሀገርሽ ተመለሺ አትርፍ ባይ አጉዳይ እንዳትሆኚ” በማለት ነበር ከተሞክርዋ በመነሳት ለሴቶች ምክሯን የለገሰችው፡፡

“በዙሪያችን ያሉ ሀብቶችን እንመልከት። ውስጣችን የሚያስበው በስደት ብቻ የምንለወጥ ይመስለናል፡፡ በተለይ ሴቶች እንንቃ፤ ከሌሎች እንማር። የግድ የስደት ሰቆቃ ሲደርስብን ብቻ መማር የለብንም” ስትል ስደትን ላሰቡ እህቶች አፅኖት በመስጠት መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡