“ሴትነት የጾታ እንጂ ያለመቻል መገለጫ አይደለም” – ወይዘሮ መኪያ እንድሪስ

“ሴትነት የጾታ እንጂ ያለመቻል መገለጫ አይደለም” – ወይዘሮ መኪያ እንድሪስ

በደረሰ አስፋው

“ሴት በመሆኔ ልኮራ፣ ከፍ ብዬ ልታይ እንጅ ላፍርና ዝቅ ብዬ ልታይ አይገባም:: ሴትነት የጾታ መገለጫ እንጂ ያለመቻል ማሳያ አድርጎ መመልከት አይገባም” ሲሉ ነው ሀሳባቸውን የጀመሩት፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሴቶች ተሳትፎ በጣም ውስን እንደሆነ ይገነዘባሉ። ሴቶች በሁሉም ማህበረሰብ ሊባል በሚችል ደረጃ ለዘመናት አድሏዊ ልዩነት ተደርጎባቸው መቆየቱን በመግለጽ፡፡

ምንም እንኳ የሴቶችን እኩልነት እና ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ሀገራዊ እና ዓለም ዐቀፋዊ ሕጎች ሀገራችን ቢኖራትም፣ የሴቶች ተሳትፎ ግን አሁንም ውስን ነው። ሴቶች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካ ተሳትፎ ማህበረሰብ ሠራሽ ተግዳሮቶች ተጭኗቸው ቆይቷል፡፡ ይህ ለዘመናት የቆየ የአመለካከት ችግር ደግሞ እንዲቀረፍ ይፈልጋሉ፡፡

ለዚህ ደግሞ ሴቷ ግንባር ቀደም ልትሆን እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡ አልችልም የሚለውን ተስፋ መቁረጥ አሸንፎ የመውጣት ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባ ገልጸው የሚገጥሙ ፈተናዎችም ቢሆን ለቀጣይ መንገድ መደላደልን የሚፈጥሩ በመሆናቸው ለጀመሩት ስራ ቁርጠኛ ሆነው መቀጠል አለባቸው ነው ያሉት፡፡

እንደመታደል ሆኖ ከመምህር አባታቸው የተወለዱት የዛሬው የእቱ መለኛ ባለታሪካችን ግን ተጽእኖዎች አልደረሰባቸውም፡፡ ይሁን እንጂ “አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል” እንደሚባለው በሌሎች ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ተጽእኖ እየተመለከቱ ነው ያደጉት፡፡ የሌሎች ህመም የእሳቸውም ህመም እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ለምን የሚለው ጥያቄም በአእምሯቸው ይብሰለሰል ነበር፡፡ ሴት ከወንድ በምን ታንሳለች? የሚለው ጥያቄም በሳቸው ዘንድ መልስ ያጣ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ዛሬ ላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የክልል ምክር ቤት አባል ሆነው እያገለገሉ ነው፤ የኡባ ደብረጸሀይ የምርጫ ክልል ህዝብን በመወከል ተወዳደርው፡፡ የሴቶች ተሳትፎ እያደገ መጥቷል የሚል ሀሳብ ቢኖራቸውም ዛሬም የገጠሯ ሴት የመማር ዕድል ተነፍጓት እራሷን ሙሉ አድርጋ ለራሷም ሆነ ለሀገር ማበርከት ያለባትን አስተዋጽኦ እያደረገች አይደለም ነው ያሉት፡፡ ታዲያ ይህን ችግር ለመቅረፍ ሁሉም ሊረባረብ የሚገባ ቢሆንም፤ ሴቶች ግን ግንባር ቀደም ሊሆኑ ይገባል የሚልን ሀሳብ ነው የሰነዘሩት፡፡

ወ/ሮ መኪያ እንድሪስ ይባላሉ፡፡ የተወለዱት በጎፋ ዞን ኡባ ደብረጸሀይ ወረዳ ነው፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም በአካባቢያቸው በሚገኙ የመጀመሪያና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነው ያጠናቀቁት፡፡ ከዚያም የትምህርት ዕድል አግኝተው በዲላ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ፣ በመቀጠልም በአርባ ምንጭ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በህክምናው ዘርፍ ተምረው በሙያቸው አገልግለዋል፡፡

ባለሙያ ሆነው ለ13 ዓመታት በኃላፊነት ደግሞ ለ4 ዓመታት ማገልገላቸውን የገለጹልን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የክልል ምክር ቤት አባሏ ወ/ሮ መኪያ የወረዳው ሴቶች ሊግ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ በቶ ከተማ ላይ የፓርቲ ርዕዮተ አለም ረዳት የመንግስት ተጠሪና የኡባ ደብረጸሃይ ሴቶችና ህጻናት ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን ያገለገሉባቸው የኃላፊነት ቦታዎች እንደሆኑ ነው የገለጹልን፡፡

ሴት ልጅ በቤት ውስጥ ካላት ከፍተኛ የትዳርና የልጆች እንዲሁም ቤት የመምራት ኃላፊነት ባሻገር በውጪ ወጥታ ሕልሟን ለመኖር የምታደርገው ትግል ፈታኝ እንደሚሆንባት ያነሳሉ። ይሁን እንጂ እሳቸው ችግሩን በርትተው በማለፍ እራሳቸውን ያበቁ ስለመሆናቸው ገልጸው ሌሎችም ይህን አርአያ ሊከተሉ እንደሚገባ ነው የሚመክሩት፡፡

ለዚህ ደግሞ የቤተሰብ፣ የማህበረሰብ እንዲሁም መንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልጋታል ባይ ናቸው። የማንኛውም ሰው የመጀመሪያ ትምህርት ቤቱ ቤተሰብ በመሆኑ የወ/ሮ መኪያ እዚህ ለመድረስ መምህር የሆኑት ወላጅ አባታቸው ጠንካራ ስብዕና እና መልካም አስተዳደግ ለሳቸው ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳደረገላቸው ነው የሚገልጹት፡፡

“ትውልድ መቀረፅ የሚጀምረው በቤተሰብ ውስጥ ነው። ቤተሰብ ልጆቹን በፆታ ሳይለይ ማሳደግ አለበት። እኔ ጠንካራ ማንነት ያለኝ ሰው መሆኔን እየነገሩኝ ያሳደጉኝ ወላጆቼ ዛሬ ትልቅ አቅም ሆነውኛል። በተለይ የአባቴ ድጋፍ እና እገዛ ለጥንካሬዬና ስኬቴ መነሻ ሆኖኛል። በሴትነቴ እንድኮራ፣ ካሰብኩት እንድደርስ፤ መሰናክልና ተግዳሮቶቼን እንዳልፋቸው አድርጎኛል” ነው ያሉት።

ወ/ሮ መኪያ ከመምህር አባት መወለዳቸውን እንደ እድል ነው የሚቆጥሩት፡፡ ይሁን እንጂ እሳቸው ስለተሳካላቸው በሴቶች ላይ ተጽእኖ አልነበረም ለማለት እንደማይደፍሩ ነው የተናገሩት፡፡ በወረዳቸው ባሉ የገጠር ቀበሌያት በሴቶች ላይ ሰፊ ተጽእኖ እንደነበር ያነሳሉ፡፡ ሴት ልጅ ተምራ የት ትደርሳለች፣ ሴት ልጅ በግዜ አግብታ መውለድ አለባት በማለት ካለ ጊዜዋ ባል እንድታገባ ትገደድ እንደነበር በሙያቸውም ሆነ በአመራርነት ባገለገሉበት ወቅት ተመልክተዋል፡፡

ወንዶች ቢማሩ የተሻለ ይሆናል የሚል አስተሳሰቦች ይንጸባረቁ እንደነበር አስታውሰው ይህም ሴቶች አይችሉም የሚል አስተሳሰብ ነጸብራቅ ነው፡፡ አሁን ላይ ይህ አስተሳሰብ እንደቀረፉ መንግስትም ሆነ ማህበረሰቡ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ሲሆን በዋናነት ግን ሴቶች እችላለሁ የሚለውን አስተሳሰብ ሊያሳድጉ ይገባል ነው ያሉት፡፡ በተለያዩ ተቋማት በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ አብዛኛው ወላጅ ሴት ልጆችን ማስተማር ጀምሯል፡፡ በቂ ነው ባይባልም ለውጦች አሉ ነው ያሉት፡፡

ሴቶች እየተማሩ በፖለቲካ አመራሩም ጭምር ተሳትፏቸው እድገት እያሳየ ነው፡፡ በርካታ ሴቶች የህዝብ ውክልናን አግኝተው በፌደራል እና ክልል ምክር ቤት አባል በመሆን የወከላቸውን ማህበረሰብ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ እኔም የዚሁ አካል በመሆኔ ደስተኛ ነኝ፡፡ በሙያዬም ሆነ በኃላፊነት ቦታዎች ሳገለግል በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የከፋ ተጽእኖ ስለተመለከትኩት፤ ለሴቶች ተሳትፎ ማደግ ልዩ አድናቆት ነው ያለኝ፡፡

ሴቶች ከጓዳ ወጥተው ከወንዶች እኩል ወደ አመራርነት መምጣታቸው የተሰራው ያልተቋረጠ ተግባር ለውጤቱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሴቶች ዕድሉን በማጣት እንጂ ከማንም ያነሰ ስራ እንደማይሰሩ በተግባር እያሳዩ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ ሴቶች ወደ አመራርነት ቢመጡ ለሀገርም ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ የሚሉት ወ/ሮ መኪያ ሴቶች ታማኝ፣ ጥንቁቅ፣ ቁጥብ፣ እና ለብልሹ አሰራር የተጋለጡ ባለመሆናቸው ኃላፊነትን የመወጣት አቅም አላቸው ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡ ለዚህም ሴቶችን ማስተማር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ነው የምክር ቤት አባሏ ወ/ሮ መኪያ የተናገሩት፡፡

ወ/ሮ መኪያ ከተጣለባቸው የኃላፊነት ስራዎች በተጓዳኝ ጓዳቸውን ሙሉ ለማድረግ የሚሰሩትም ለሌሎች አርአያ የሚሆን ተግባር ነው፡፡ ትርፍ ጊዜያቸውን በመጠቀም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ በግል ስራም ላይ ተሳትፏቸው ከፍተኛ ነው፡፡ የመንግስት ሰራተኛ ሆነው ማህበረሰቡን ሲያገለግሉ ጎን ለጎን በእርባታው ዘርፍ የወተት ላሞችን የማርባት ስራ ይሰራሉ፡፡ ይህም ወተትን ለመግዛት የሚያወጡትን ወጪ ከመታደጉም ባሻገር ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ነው የፈጠረላቸው፡፡ እንዲሁም ፍየሎችንም ያረባሉ፡፡ የኑሮ ጫናው የብዙዎችን ጓዳ በፈተነበት በዚህ ወቅት ከመንግስት ስራ ጎን ለጎን እንደዚህ አይነት ተጨማሪ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

ሴቶች የተፈጠረላቸውን የስራ አማራጭ በመጠቀም መስራት ካልቻሉ ከባህላዊ ተጽእኖ በተጨማሪ በኢኮኖሚያዊ ተጽእኖዎችም ስለሚወድቁ ይህን ችግር መጋፈጥ እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡ በገጠር ቢሆን በከተማ ለንግድ፣ ለእርባታ፣ ለግብርናው ሰፊ የመልማት ዕድል እንዳለ ጠቁመው ይህን መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በርካታ ሀብትን በጉያ አቅፎ ይዞ በችግር መኖር ተመራጭ ሊሆን አይገባም ነው ያሉት፡፡

በርካታ የሀገራችን ሴቶች ዛሬም ያልተላቀቁት ዘርፈ ብዙ ችግር እንዳለ የሚገልጹት ወ/ሮ መኪያ ለዚህም መፍትሄው ሴቶች እራስን የመቻል አቅማቸውን ማጎልበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በትምህርት፣ በንግድ እንዲሁም በአመራርነት ደረጃ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ይገባል፡፡ ወንዱ አመራር ሲሆን የሚያምርበት ሴቷ አመራር ስትሆን የማያምርባት አድርጎ መውሰድ ተገቢ አይደለም ነው ያሉት፡፡

“ቤተሰብን የምንመራው በጋራ እስከሆነ ድረስ ሴቷ አመራር ከሆነች ቤተሰብ ይበተናል ከሚል አመለካከት መውጣት ይገባል፡፡ ሴቶች ከወንዶች እኩል ነን የሚባለው በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ማሳየት አለብን፡፡ ስለ ሥርዓተ-ጾታ ስናወራ በሴቶች እና በወንዶች መካከል ያለውን ማህበረሰብ ሰራሽ አስተሳሰብ መቅረፍ ይገባል፡፡ ሴቶች በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚው እና በፖለቲካው ላይ ያላቸው ውስን ተሳትፎ መስተካከል አለበት፡፡ ሴቶች ለሀገራቸው እና ለማህበረሰባቸው ያላቸውን ዕምቅ አቅም ተጠቅመው ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲያመጡ፣ የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ በሴቶች ላይ የሚስተዋለው ፍትሀዊነት የጎደለው አሰራር እንዲስተካከል ሊሰራ ይገባል” ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡