በዶሮ እርባታ ስራ በመሰማራታቸው የገቢ ምንጫቸውን ከማሳደግ ባሻገር ለሌሎችም የሥራ እድል መፍጠር መቻላቸውን በአርባምንጭ ከተማ የሚገኙ ማህበራት ገለጹ
በከተማው ከ1 ሺ በላይ ስራ አጦች የዘርፉ ተጠቃሚ መሆናቸውን የከተማው ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
”የዶሮ መንደር” መበራከትን ተከትሎ ለማህበራት የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆኑ መስራቱንም የከተማው ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
በእርባታ ዘርፍ ተሰማርቶ ለአካባቢው አርቢዎች በማሰራጨት ላይ የሚገኘው “ኢያኤል” የዶሮ እርባታ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ሳሙኤል ሳታ፤ ማህበሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ከራስ አልፎ ለሌሎችም የስራ እድል እንደፈጠረ ተናግረዋል፡፡
እንደ ሀገር ለእርባታው ዘርፍ እንደ ችግር የሚስተዋለውን የዶሮ መኖ አቅርቦት እና የዋጋ መናር ችግር ለመቅረፍ የመኖ ማቀነባበሪያ ለመገንባት መታቀዱንም ገልፀዋል፡፡
ሌላይኛዋ የዋንዛ ዶሮ እርባታ ማህበር ሰብሳቢ ወ/ሮ ዘቢደር ከበደ፤ የዶሮ እርባታ ስራ አድካሚ ቢሆንም ከዶሮ እርባታው ስራ ጎን ለጎን ንብ ማነብና ከብት ድለባ የወተት አቅርቦት ስራ መጀመራቸውን ገልፀዋል።
በተመጣጣኝ ዋጋ ዶሮ እና እንቁላል በመሸጥም ህብረተሰቡን እየጠቀሙ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
የአርባምንጭ ከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት የእንስሳት ጤና እና በሽታ ቁጥጥርና ክትትል ስፔሻሊስት አቶ ደስታ ዳና፤ በከተማው በእርባታ ዘርፍ ለተሰማሩ ማህበራት የእንስሳት ህክምና እና ክትትል እንደሚደረግ ገልፀው ክትባት ያልወሰዱ እና ጊዜያቸው ያልደረሱ የዶሮ ጫጩቶችን ሳያረጋግጡ በመግዛት ለኪሳራ የሚዳርጉ በመሆኑ ባለሙያ በማማከር ወደ ስራ መግባት ይገባል ብለዋል፡፡
የአርባምንጭ ከተማ ግብርና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ መተኪያ አበበ፤ በከተማው በርካታ ወጣቶች በእርባታ ዘርፍ ተሰማርተው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙና የዶሮ መንደር በመመስረት ማህበራቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መስራቱን ገልፀዋል፡፡
የከተማው ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በሀይሉ ካፒቴን በ2017 ዓ.ም 1 ሺ 125 ስራ አጦች ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የመስሪያ እና የመሸጫ ቦታ በማመቻቸት ረገድ ሰፊ ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ገነት መኮንን – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
በዶሮ እርባታ ስራ በመሰማራታቸው የገቢ ምንጫቸውን ከማሳደግ ባሻገር ለሌሎችም የሥራ እድል መፍጠር መቻላቸውን በአርባምንጭ ከተማ የሚገኙ ማህበራት ገለጹ

More Stories
የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ያሳኩት የጋራ ድል መሆኑን የጨታ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ
የክረምት ዝናብን ተከትሎ ጎርፍ እና መሰል አደጋዎች በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ
ሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በ192 ሚሊዮን ብር ወጪ አዲስ የተቀናጀ የገጠር ልማት ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በሳውላ ከተማ አካሄደ