የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓትን በማዘመን የመረጃ ታማኝነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓትን በማዘመን የመረጃ ታማኝነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ታኅሣሥ 05/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓትን በማዘመን የመረጃ ታማኝነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤ ዞን የአልቾ ውሪሮ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የውሳኔ ኩነት ምዝገባ ሥርዓትን በማከናወን ህጋዊ ሰነድ ከማግኘታቸው በተጨማሪ ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት እንዳስቻላቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል።

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስራ በአንድ ሀገር ዜጎች ላይ ከልደት እስከ ህልፈታ ህይወት የሚከሰቱ ወሳኝ ኩነቶችን የልደት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ፣ የሞት እንዲሁም የጉዲፈቻ ክስተቶችን የመመዝገብ እና የማከማቸት ተግባር ነው።

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግስትና በሌሎች ሕጎች እውቅና የተሰጣቸውን የግለሰቦች መሠረታዊና ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ወሣኝ የመረጃ ምንጭ በመሆናቸው ኩነቶቹ ሲከሰቱ ማለትም አንድ ሰው ሲወለድ፣ ሲያገባ፣ ሲፋታ ወይም ሲሞት የሚመዘገብበት ሥርዓት የወሳኝነት ምዝገባ በመባል ይታወቃል፡፡

በስልጤ ዞን የአልቾ ውሪሮ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መሀመድ አህመድ እንደገለፁት በወረዳው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኮምፒውተራይዝድ በማድረግ በበይነ- መረብ ስርዓት ምዝገባ በመካሄድ የተገልጋዩን ማህበረሰብ የኩነት መረጃ ተአማኒነትና ህጋዊነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓት ያለውን ፈይዳ ከክልሉ የወሳኝ ኩነት ኤጃንሲ ጋር በመተባበር ለህብረተሰቡ የተለያዩ የግንዛቤ ስልጠናዎችን ከመስጠት ጎን-ለጎን የምዝገባው ስርዓት በማዘመን ከዚ ቀደም ይስተዋል የነበረውን የሰነድ ጥራት መቅረፍ መቻሉን የገለፁት አቶ መሀመድ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎችን ለመፍታት ከቀበሌ አስተዳዳሮችና ከክብር የመዝገብ ሹሞችና ባለሙያዎች የመነጋገር እንዲሁም በብልሹ አሰራር የተሳተፉ አካላት ሲያገጥሙ የማረም ተግባር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ።

በስልጤ ማህበረሰብ ዘንድ ከጥንት ጀምሮ ወላጆቻቸው በሕይወት የሌሉና፣ የአቅማ ደካማ ልጆችን ወስዶና ተንከባክቦ የማሳደግ ባህል ያለ ቢሆንም ከዚህ ቀደም በወረዳው ጉዲፈቻን የወሳኝ ኩነት አካል አድርጎ ከመመዝገብ ጋር ተያይዞ የነበረውን ውስንነት ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የሰው ልጅ ህይወት የሚጀምርባቸውንና የሚጠናቀቅባቸውን እንዲሁም የሚያልፋቸውን የህይወት ውህደቶች በህጋዊ መልኩ ተሰንደው የግለሰቦችን ሰብዓዊና ማህበራዊ መብቶችን ተፈጻሚ ለማድረግ እና ለመጠበቅ የመረጃ ምንጭ በመሆን እንደሚያገለግል የሚገልፁ ደግሞ በአልቾ ውሪሮ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አስተባባሪ የሆኑት ወይዘሮ ሙሉካ ሸሚል ናቸው ።

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ለአንድ ሀገር ቀጣይነት ላለው እድገት አቅጣጫ ለመንደፍ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ በመሆን እንደሚያገለግል የሚያነሱት ወይዘሮ ሙሉካ በወረዳው ከሚገኙ 29 ቀበሌ ውስጥ በ15ቱ የምዝገባ ስርዓቱን ዲጂታለይዝድ በማድረግ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ግለሰቦች የወሳኝ ኩነት ሰነዶችን ለህክምና፣ ለውጭ ሀገራት ጉዞ፣ ለህግ ጉዳዮች በሚፈልጉበት ወቅት ታማኝነት ያለው መረጃ ለማቅረብ ከልደት አንስቶ ሞት ያሉ ኩነቶችን በሳምንት ሁለት ቀናት ቤት ለቤት በመዞር ፣በህክምና ተቋማት በመገኘት ፣በትምህርት ቤቶች የወሳኝ ኩነት ክበባትን በሟቋቋም የምዝገባ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

በስልጤ ዞን በአልቾ ዉሪሮ ወረዳ የቃውቀቶ ከተማ 01 ቀበሌ የክብር መዝገብ ሹም ባለሙያ የሆኑት አቶ ነስሬ ፊጣሞ በበኩላቸው ህብረተሰቡ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መከናወን ቀልጣፋ አገለግሎት ለመግኘት ያለውን ፋይዳ እየተገነዘበው መምጣቱን ተከትሎ በርካታ የአገልግሎቱ ፈላጊዎች የተለያዩ ኩነቶችን በመመዝገብና በማስመዝገብ ሰርተፍኬት እየወሰዱ እንደሚገኙ ገልፀዋል ።

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በማካሄድ በያዙት ሰርተፍኬት የተለያዩ አገልግሎቶችን ከማግኘታቸው በተጨማሪ ህጋዊና ዘለቄታዊ የማንነት ሰነድ ማግኘት መቻላቸውን በወረዳው በተለያዩ ቀበሌያት ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ሙጂብ ጁሃር – ከሆሳዕና ጣቢያችን