“ተማሪዎቼ የሚፈልጉበት ደረጃ እንዲደርሱ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ” – መምህርት ዋጋዬ ደግፌ

“ተማሪዎቼ የሚፈልጉበት ደረጃ እንዲደርሱ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ” – መምህርት ዋጋዬ ደግፌ

በአለምሸት ግርማ

ሰዎች በተፈጥሮ አልያም በአጋጣሚ በሚያገኙት ክህሎት በህይወታቸው ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን በማንኛውም መንገድ ያገኙትን ክህሎት አዳብሮ እና ውጤታማ ሆኖ ለመገኘት የግለሰቦቹ አስተዋፅኦ የጎላ ነው። የዛሬዋ እቱ መለኛችን ወጣት መምህርትና ጊዜዋን በአግባቡ የምትጠቀም፣ በስራ ላይ ጠንካራ አቋም ያላት ብልህ ሴት ናት። ወጣትነቷ ሳይዛት ጊዜዋን በስራ ብቻ ታሳልፋለች። ያካፈለችንን ልምዷን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፦

መምህርት ዋጋዬ ደግፌ ትባላለች። ከሃዋሳ ከተማ ፒያሳ ሰፈር ነው የተገኘችው። ለቤተሰቧ የመጀመሪያ ልጅ ስትሆን፤ በልጅነቷ ትምህርቷን የምትወድ ጎበዝ ተማሪ ነበረች። ተወልዳ ባደገችበት ሰፈርም ተግባቢና ሰዎችን አክባሪም ነበረች።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ “በሃይቅ ዳር ቃለ ህይወት ትምህርት ቤት” የተከታተለች ሲሆን፤ በመቀጠል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ አቶቴ መካነ ኢየሱስ ትምህርት ቤት ነው የተማረችው። የ11ኛና የ12ኛ ክፍልን አላሙራ ትምህርት ቤት ተምራ አጠናቃለች። ለትምህርቷ ድጋፍ ያደረገላት ኮምፓሽን መሆኑንም ደጋግማ ታነሳለች። “ድርጅቱ ትምህርቴን እስከ ከፍተኛ ደረጃ ድረስ እንድማር ከማድረጉም በላይ የተለያዩ ክህሎቶችን እንዳዳብር ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል“ ስትልም ከምስጋና ጋር ተናግራለች።

በልጅነቷ የህግ ባለሙያ(ጠበቃ) የመሆን ፅኑ ፍላጎት ነበራት። ሆኖም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ስትገባ የህግ ትምህርት የመማር ፍላጎቷን እውን ማድረግ አልቻለችም። የተማረችው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አፕላይድ ጂኦግራፊ ዘርፍ ሲሆን፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋም የተለያዩ የህይወት ልምዶችን እንዳገኘች አጫውታናለች።

የከፍተኛ ትምህርቷን አጠናቃ ከተመረቀች በኋላ ጊዜ ሳታባከን ወደ ስራ ፍለጋ ተሰማራች። ባደረገችው ጥረትም በተማረችበት ሙያ ቀጥተኛ ስራ ባታገኝም ተዛማጅ ስለሆነ በመምህርነት ሙያ የምትሰማራበት ሁኔታ አጋጠማት። ዛሬ በተሰማራችበት ሙያ በቱላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማህበራዊ ሳይንስ መምህርነት ማገልገል ከጀመረች አራት አመታት ተቆጥረዋል። መምህርነት በስራ ህይወት ራስ እያስተማሩ መኖር ስለሆነ ሙያውን እንደወደደችው ትናገራለች። “መሆን የምፈልገውን ባልሆንም ተማሪዎቼ መድረስ የሚፈልጉበት ደረጃ እንዲደርሱ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ” ብላለች፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች በቂ እውቀት እንዲያገኙ እና ትምህርታቸውን እንዲወዱ ለማድረግ የተለያዩ ስልቶችን ትጠቀማለች። በስራዋ ደስተኛ እንደሆነች ያጫወተችን መምህርት ዋጋዬ ከስራዋ ጎን ለጎን የተለያዩ ስራዎችን ታከናውናለች። ለዚህ የተለየ ምክንያት ይኖራት እንደሆነ ጠይቀናት የሚከተለውን ምላሽ ሰጥታናለች፦

“ታታሪነትን የተማርኩት ከእናቴ ነው። ልጅ ሆኜ እናቴ የተለያዩ ስራዎችን ስትሰራ አግዛት ነበር። ጥንካሬንና ስራን ማክበርን በተግባር ያስተማረችኝ እሷ ናት። እኔም ተማሪ ሆኜ የተለያዩ ስራዎችን ሰርቻለሁ። ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ የክረምት እረፍቴን በስራ ነበር የማሳልፈው። ከሰራኋቸው ስራዎች መካከል ጋራጅ፣ የባንክ ፅዳትና ፍተሻ ይጠቀሳሉ። እንዲሁም ዩኒቨርሲቲ እያለሁ ደግሞ ቅዳሜና እሁድ የሴቶችን ጸጉር እሰራ ነበር። ያም የሚያስፈልገኝን ወጪዎች በራሴ ለመሸፈን ከማስቻሉም በላይ ጊዜዬን በአልባሌ ቦታ እንዳላባክን እረድቶኛል።

አሁን በምሰራበት የመምህርነት ሙያ ግማሽ ቀን ያህል የማሳልፍ ሲሆን፤ ቀሪውን ግማሹን ቀን ተጨማሪ ስራ መስራት እንዳለብኝ ወሰንኩ። በዚህ ሃሳብ መሰረት የሰው ልብስ ቤት ተቀጠርኩ። ከቆይታ በኋላ ለራሴ ልብስ ለመነገድ አሰብኩ። በመቀጠልም ለመኖሪያና ለስራ ሁለት ቦታ ቤት መከራየት ስለሚከብደኝ መኖሪያዬንም ሱቄን በአንድ ስፍራ አደረኩ። ከልብሱ ስራ ጋር አብሮ ይሔዳል ብዬ ስላመንኩ ማስታወቂያ /ታፔላ/ በማሰራት የሴቶችን ጸጉር መስራት ጀመርኩ“

የክረምት ወቅት ተማሪ እና አስተማሪ የሚያርፍበት፤ ብሎም ዘመድ የሚጠይቅበት ጊዜ እንደሆነ ይታወቃል። መምህርት ዋጋዬ ግን ከዚህ በተለየ መልኩ ነው ክረምትን የምታሳልፈው። ከመደበኛ ስራዋ መምህርነት ውጪ ያለውን ስራዋን በማከናወን ነው ቀኗን የምታሳልፈው። ጊዜዋን በአግባቡ የመጠቀም ልምድ አዳብራለች። ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ከወትሮው ይልቅ ሴቶች ሹሩባ የሚያዘወትሩበት ነው። ለመሰራት የሚመጡ ደንበኞቿን እንደሚፈልጉት ስለምታስውብና በአክብሮት ስለምታስተናግድ በርካታ ደንበኞችን ማፍራት ችላለች። ከበርካታ ደንበኞቿም በርቺ የሚል አስተያየት ይጎርፍላታል።

መምህርት ዋጋዬ በቀጣይ ትምህርቷን የመቀጠል ዕቅድ ያላት ሲሆን፤ ለዚያ የሚያስችላትን ቅድመ ዝግጅት ከወዲሁ እያደረገች ትገኛለች። ከተቻለ ደግሞ በፍላጎቷ በህግ ሙያ የመስራት ፍላጎትም አላት። የህግ ሙያን በጣም ስለምወድ ብሰማራበት ከአሁኑ የበለጠ ውጤታማ እንደምሆን እርግጠኛ ነኝ ትላለች።

ለወጣት ሴቶች ከተሞክሮዋ በመነሳት እንዲህ በማለት ትመክራለች፦
“በማንኛውም ሙያ ያሉ ወጣት ሴቶች ጊዜያቸውን በአግባቡ ቢጠቀሙ መልካም ነው። እንዲሁም የሚኖራቸውን ትርፍ ሰዓት በጠቃሚ ተግባር ቢያሳልፉ ተጠቃሚ ይሆናሉ። እኔ በምሰራው ስራ ከማገኘው ትርፍ ይልቅ የውስጥ እርካታዬ ይበልጣል። ስለዚህ ጊዜያቸውን በስራ ሲያሳልፉ ከሚያገኙት ጥቅም በላይ የውስጥ እርካታቸው እንደሚበልጥ በማወቅ ቢሰሩ በርካታ ጠቀሜታ ያገኛሉ።”

በህይወቷ ያጋጠማት ፈተና ካለ እንድታጋራን ጠይቀናት ስታጫውተን፦
“የተለየ ከባድ ነገር ገጥሞኝ አያውቅም። ነገር ግን በአካል ልጅ በመሆኔ ብዙ ሰዎች አትችልም ብለው ይገምታሉ። እኔ ግን ሰርቼ እንደምችል በተግባር ማሳየት ነው የምፈልገው፤ ያንንም እያደረኩት ነው” ብላለች፡፡

ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ልብወለድን ጨምሮ የተለያየ ይዘት ያላቸውን መፅሐፍት ታነብ እንደነበር ያጫወተችን መምህርት ዋጋዬ፤ ያኔ የጀመረው የንባብ ፍላጎት በትምህርቴ ውጤታማ እንድሆን አግዞኛል ትላለች። “በትንሽነቴ የጀመርኩት ንባብ እዚህ አድርሶኛል። በቀጣይ ማሳካት ለምፈልገው ዕቅድ እንዲሁም ለህይወቴ በርካታ ክህሎት ለማግኘት ረድቶኛል። እና ሌሎችም በተለይም ተማሪዎች የንባብ ልምዳቸውን ቢያዳብሩ መልካም ነው” ስትል ከንባብ ጋር ያላትን ቁርኝትና ያገኘችውን ጠቀሜታ አስረድታናለች።

ከመምህርት ዋጋዬ የህይወት ተሞክሮ ሴቶች በተለይም ወጣት ሴቶች የተለያየ ስራን መስራት እንደሚችሉ ያሳያል። ይህም የገቢ ምንጭን ከመጨመሩም ባሻገር ጠንካራ የስራ ባህልን በመፍጠር የተሻለ ኢኮኖሚ ለመገንባት አበርክቶው የጎላ ነው።