በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሣ ወረዳ የሚገኙ አመራሮች ደም በመለገሳቸው በደም እጦት ምክንያት የሚሞቱ ወገኖችን ህይወት በማትረፋቸው መደሰታቸውን አስታወቁ

በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሣ ወረዳ የሚገኙ አመራሮች ደም በመለገሳቸው በደም እጦት ምክንያት የሚሞቱ ወገኖችን ህይወት በማትረፋቸው መደሰታቸውን አስታወቁ

‎በ2017 የክረምት ወቅት ከዳውሮ ዞንና ከኮንታ ዞን 3 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ የደም ባንኩ አስታውቋል፡፡

‎የሎማ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ሀብታሙ ክፍሌን ጨምሮ በወረዳው የሚገኙ አመራሮች ደም በመለገሳቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

‎ደም መለገስ በቅድሚያ ጥቅሙ ለራስ፥ ቀጥሎ በደም እጦት የሚሞቱ ወገኖችን ህይወት መታደግ በመሆኑ ደስታውን እጥፍ ያደርግልናል ሲሉም ተናግረዋል።

‎በወሊድ ወቅት በደም እጦት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ ደም መለገስ የሚችል ሁሉ ደም እንዲለግስ የሎማ ወረዳ አመራሮች አብክረው አሳስበዋል።

‎ደም በመለገስ ከጤና እክል ጋር ተያይዞ የሚነገሩትን የተሳሳተ ግንዛቤዎች በመተው የጤና ባለሙያዎች ሙሉ ምርመራ በማድረግ መለገስ ያለበትንና የሌለበትን ለይቶ ስለሚወሰድ ያለ አንዳች ስጋት ደማቸውን ለወገኖቻቸው መለግስ እንዳለባቸው አመራሮቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በዞኑ የደም ባንክ አስተባባሪና የጤና ባለሙያ ‎አቶ አማኑኤል አበራ ፤ ደም መለገስ የወገንን ህይወት ከማትረፍ ባለፈ ለጋሹ ከልብ ህመም፣ ከካንሰር፣ ከጭንቀትና መሰል በሽታዎች ነፃ የማድረግ ጥቅም እንዳለው ጠቅሰው ከሚለግሰው ደም ናሙና ተወስዶ በውስጡ ኤች አይ ቪ፣ ጉበት ሌላም በግብረ-ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉትን በሽታዎች በነፃ ምርመራ ተደርጎ ለለጋሾች ውጤቱ ይሰጣል ብለዋል።

‎በመሆኑም ሙሉ ጤንነታቸው ተመርምሮ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 65 የሆኑትና ክብደታቸው ከ45 ኪሎ ግራም በላይ የሆኑት ግለሰቦች ደም በመለገስ ውድ የሆነውን የወገኖቻቸውን ህይወት እንዲያተርፉ አቶ አማኑኤል ጥሪ አቅርበዋል።

‎በ2017 የክረምት ወቅት ከዳውሮ ዞንና ከኮንታ ዞን 3 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ተግባር የተገባ ሲሆን ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ሁለት መቶ ዩኒት ደም ብቻ መለገሱን አስተባባሪው ገልጸዋል።
ዘጋቢ: አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ጣቢያችን