በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ዙሪያ የሚደረገው ጥንቃቄ በመቀዛቀዙ አሁንም የቫይረሱ ስርጭት እየተስተዋለ መሆኑን ተገለጸ

በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ዙሪያ የሚደረገው ጥንቃቄ በመቀዛቀዙ አሁንም የቫይረሱ ስርጭት እየተስተዋለ መሆኑን ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኤችአይቪ ኤድስ ዙሪያ የሚደረገው ጥንቃቄ በመቀዛቀዙ አሁንም የቫይረሱ ስርጭት እየተስተዋለ መሆኑን በጋሞ ዞን የቦረዳ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

‎ቀደም ሲል በመንግሥት በኩል ይደረግ የነበረው ግንዛቤ የማስጨበጥ ዘመቻ መቀዝቀዙን ተከትሎ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚታይ መዘናጋት መኖሩን የወረዳው ነዋሪዎች ገልፀዋል።

‎አቶ ማናዬ ማርካ የኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ መኖሩን ገልፀው፥ ሰው ራሱን ከቫይረሱ እንዲጠብቅና እንዲከላከል በየአደባባዩ እናስተምራለን ነው ያሉት።

‎ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መገኘቱን ካረጋገጡ በኋላ የፀረ ኤች.አይ. ቪ/ ኤድስ መከላከያ መድሐኒት መጠቀም በመቻላቸው በ20 ዓመት ግዜ ውስጥ 3 ጤነኛ ልጆችን ወልደው እያሳደጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

‎ሌላኛው ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝባቸው አቶ ወንድይፍራው ሃብቴ አሁን ላይ በሽታው ትኩረት አለማግኘቱን ተከትሎ የሚታዩ መዘናጋትን ለመቀረፍ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

‎ወ/ሮ መስታወት ማርካ ባለድርሻ አካላት ሳይቀሩ በቫይረሱ ዙሪያ የሚያደርጉትን የግንዛቤ ትምህርት በማቆማቸው ጥንቃቄ ማድረግ ላይ ሰው ተዘንግቷል ነው ያሉት ።

‎በዘፍኔ ጤና ጣቢያ የጤና ባለሙያ የሆኑት አቶ አብርሃም ማንደቦ ሰው ሳይመረመር ጤነኛ ነኝ ማለት ስለማይችል መመርመርና ራሱን ማወቅ አለበት ይላሉ።

‎አክለውም ስርጭቱን መከላከል እንዲቻል የኮንዶም ስርጭት ብናደርግም ሰው ግን እየተዘናጋ ነው ብለዋል።

‎የቦረዳ ወረዳ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና የበሽታ መከላከል ዳይሬክቶረት ቡድን መሪ አቶ ሽመልስ አገኘው እንደ ወረዳ 4 ጤና ጣቢያ 2 ታዳጊ ጤና ጣቢያ እንዲሁም 28 ጤና ኬላዎች እንዳሉ ገልፀው፥ የጤና ተቋማት ከዚህ ቀደም በተካሄደው ምርመራ 42 ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ተገኝቶ የፀረ ኤች.አይ.ቪ መድሐኒት እንዲጠቀሙ መደረጉን አመላክተዋል።

አሁን ላይ ተጋላጭ በሚባሉ ስፍራዎች ላይ በተደረገ ምርመራ አራት ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱን አቶ ሽመልስ ጠቁመው፥ ይህም ስርጭቱ እንዳለ አመላካች ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው ኮንዶም መጠቀም ላይ ችላ ባይባልና ተመርምሮ ቫይረሱ የተገኘበት ሰው የፀረ ኤች አይ ኤድስ መድሐኒት መጠቀም እንደሚገባው ጭምር አሳስበዋል።

‎ዘጋቢ፡ ታምሩ በልሁ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን