“እንችላለን ብለን ውስጣችንን ማሳመን አለብን” – ወጣት ነፊሳ ሲራጅ
በሙናጃ ጃቢር
እችላለሁ የሚለውን አስተሳሰብ ያንፀባረቀች እንስት አካል ጉዳተኛ ናት። ቤተሰቦቿ ትችያለሽ የሚለውን አስተሳሰብ ውስጧ እንዲኖር አድርገው ነው ያሳደጓት። ለአካል ጉዳተኞች ወሳኙ ነገር የቤተሰብ እገዛ ነው፡፡ የቤተሰብ ልዩ ትኩረት ያላቸው አካል ጉዳተኞች ያሰቡበት ይደርሳሉ፤ ምንም አይገድባቸውም የሚል እምነት አላት፡፡
“የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም” እንዲሉ አንዴ የሆነ ነገር ስላማይመለስ ከሆነ በኋላ መፀፀት አያስፈልግም፡፡ በደረሰባት ጉዳት ዕድሜ ልክ ከማዘን ይልቅ ቤተሰቦቿ ትልቅ ደረጃ እንድትደርስ ይጥሩ ስለነበር አንድም ቀን እንክብካቤያቸው ተለይቷት እንደማያውቅ በኩራት ትናገራለች፡፡
የዚህ ሳምንት ችያለሁ አምድ ባለታሪካችን ነፊሳ ሲራጅ ትባላለች፡፡ ትውልዷ ምስራቅ ኦሮሚያ መተሀራ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ ሲሆን እድገቷ ደግሞ ወራቤ ከተማ ነው፡፡ ትምህርቷን ከመዋዕለ ህፃናት ጀምራ እስከ 2ኛ ክፍል መተሀራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራለች፡፡
ከዚያም ቤተሰቦቿ በሥራ ምክንያት ተቀይረው ወደ ወራቤ ከተማ ሲገቡ ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ ወራቤ አንደኛ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት እስከ 8ኛ ክፍል ተከታትላለች፡፡ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በወራቤ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተምራ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚያስገባ ውጤት ማምጣት ችላለች፡፡
ከ2007 ዓ.ም እስከ 2009 ዓ.ም በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በሶሾሎጂ ትምህርት ክፍል ለ3 ዓመታት ተከታትላ መመረቅ ችላለች፡፡ ሁለተኛ ድግሪዋን ከ2015 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም በአርባን ፕላኒንግ ትምህርት ክፍል በወራቤ ዩኒቨርስቲ ለ2 ዓመታት ተከታትላ ተመርቃለች፡፡
“ለትምህርቴ ስኬት ትልቁን ሚና የተጫወቱት ሳይማሩ ያስተማሩኝ ቤተሰቦቼ ናቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሳላመሰግናችው አላልፍም” ብላለች፡፡
አካል ጉዳት እንዴት እንደገጠማት እንደሚከተለው አብራርታልናለች፡-
“ማንኛውም ልጅ እንደሚታመመው የ8 ወር ህፃን እያለሁ ታምሜ ቤተሰቦቼ ለህክምና ወስደውኝ ነበር፡፡ መርፌ ስወጋ ድንገት መርፌው አምልጦ ወደ ውስጥ እንደገባ ቤተሰብ ሲያወራ ሰምቻለሁ፡፡ በወቅቱ መርፌው ወደ ውስጥ መግባቱን ስላልተረዱ ለማስወጣት አልሞከሩም ነበር፡፡
“ድክ ድክ የምልበት እድሜ ላይ ስደርስ ግድግዳ ይዤ ከመቆም ውጭ መራመድ አልችልም ነበር፡፡ ቤተሰቦቼም ግራ ገብቷቸው የተለያዩ ሰዎችን ያማክሩ ነበር፡፡ ቀስ እያለች ትሄዳለች አንዳንድ ልጆች ይዘገያሉ ሲሏቸው ችላ ብለው ሁለት ዓመት እስኪሞላኝ ድረስ ችግሩን አላወቁም ነበር፡፡
“አንድ ቀን ግን የእናቴ የአክስት ልጅ ለጥየቃ እኛ ጋር መጥቶ ነበር፡፡ አለመራመዴ አስጨንቋቸው ሲወያዩ እናቴ ትዝ አላት እና ‘የ8 ወር ህፃን እያለች አኮ ሀኪሞቹ መርፌ አምልጧቸው ነበር ይወጣ አይውጣ ግን በውል አላውቅም’ ስትል የእናቴ የአክስት ልጅ እስቲ ብሎ አገላብጦ ሲያየኝ ድንገት ታፋዬ ሥር ሲጎረብጠው ኧረ ወደ ህክምና መሄድ አለባት ብለው ወደ መተሀራ ሆስፒታል ወሰዱኝ፡፡
“ሀኪሞቹም መርፌ እንደሆነ ነግረዋቸው እዚህ ማውጣት ስለማንችል ብለው ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሪፈር አደረጉኝ። ከዚያም ቀዶ ጥገና አድርገውልኝ መርፌውን አውጥተውልኛል፤ ግን ሥሬን ነክተውኝ ስለነበር ቀኝ እግሬ የባሰ ታጠፈ ስትል” አካል ጉዳት እንዴት እንደገጠማት አውስታናለች፡፡
ጉዳቷ ከምንም ሳይገድባት ከራሷ አልፋ ለሌሎች አካል ጉዳተኞች በርካታ ሥራዎችን እየሠራች ትገኛለች፡፡ የወራቤ ከተማ አስተዳደር ሴት አካል ጉዳተኞች ሰብሳቢ እንዲሁም ደግሞ አጠቃላይ የዞኑ አካል ጉዳተኞች ፀሀፊ እና የሴት አካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን ሰብሳቢ ሆና እየሠራች እንደሆነ አጫውታናለች፡፡
የመንግስት ሥራ የጀመረችው በሁልባረግ ወረዳ ሴቶችና ህጻናት ጽ/ቤት ሲሆን ለ8 ወራት አገልግላለች፡፡ ከጉዳቷ ጋር ስላልተመቻት ወደ ወራቤ ከተማ አስተዳደር ተዘዋውራ ሰራተኛና ማህበራዊ ውስጥ የልማት ዕቅድ ባለሙያ እና የሰው ሀብት ሥራ አመራር ባለሙያ ሆና ለ4 ዓመታት አገልግላለች፡፡
ከዚያም ሁለተኛ ዲግሪዋን ጨርሳ ስትመጣ በስራዋ ታታሪ ሠራተኛ ስለነበረች የደረጃ ዕድገት አግኝታ ወደ ኢንዱስትሪ ግንኙነት አቤቱታና ቅሬታ መፍቻ ሥራ ዘርፍ ላይ ተመድባ እየሠራች ሲሆን በአጠቃላይ መንግስት ቤት ለ8 ዓመታት አገልግላለች፡፡
“ከአመለካከት ጋር ተያይዞ ምንም ነገር ገጥሞኝ አያውቅም፤ ነፍስ እያወኩ ስሄድ ግን አካል ጉዳተኛ ስለሆንኩ ብቻ ብዙ ጊዜ ከሰው ጋር መቀላቀል እፈራ ነበር፡፡ እድሜ ለቤተሰቦቼ የሁልጊዜ ድጋፋቸው ስላልተለየኝ አሁን ላይ በራሴ እንድተማመን አድርጎኛል፡፡
“በተለይ በዩኒቨርስቲ ቆይታዬ ምንም ሳልቸገር እንድማር ጠቅሞኛል፡፡ በርግጥ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ እንደሚታወቀው ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ነው። ከማደሪያ ጀምሮ መወጣጫው፣ በተለይ ለሴት አካል ጉዳተኛ ልዩ ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡ የመማሪያ ክፍሉም ምድር ስለነበር አልተቸገርኩም” ስትል ከአመለካከት ጋር ተያይዞ ምንም ችግር እንዳልገጠማት አጫውታናለች፡፡
“የወደፊት ዕቅዴ ባለሁበት የሥራ መስክ ጠንክሬ በመስራት እና ተወዳደሪ ሠራተኛ መሆን ሲሆን በተጨማሪም የራሴን የግል ሥራ መሥራት እና አንድም ቀን እንዳይከፋኝ አድርገው ያሳደጉኝን ቤተሰቦቼን እስከ እለተ ሞቴ ማገልገል ነው፡፡” ስትል የወደፊት ዕቅዷን ገልጻልናለች፡፡
“ለሌሎች አካል ጉዳተኞች የማስተላልፈው መልከት ቢኖር፡- አልሀምዱሊላህ የኔ ጉዳት ያን ያህል የከፋ አይደለም፡፡ ያለምንም ድጋፍ እያነከስኩ ነው የምራመደው፡፡ ከእኔ የባሱ ጥቂት የማይባሉ ሴት አካል ጉዳተኞች አሉ። ሴትነት በዛላይ አካል ጉዳተኝነት ሲጨመር ጉዳቱ በጣም ከባድ ነው፡፡
“እኔ የቤተሰብ ድጋፍ ስላልተለየኝ ለዚህ ደረጃ ልደርስ ችያለሁ፡፡ ምንም እገዛ የሌላቸው አካል ጉዳተኞች አሉ፡፡ በተለይ ሴት አካል ጉዳተኞች ላይ ችግሩ ይበረታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ራሳቸውን ማጠንከር አለባቸው፡፡
“ሴት ልጅ ውጣ ውረዷ ብዙ ነው። መውለድ አለ፤ ልጅ መሳደግ፤ ከዚያም ከፍ እያሉ ሲሄዱ ልጆቿ ተፅዕኖ ይፈጥሩባታል። የአካል ጉዳተኛ ልጆች ነን መባልን አይፈልጉም። ብቻ የሴት ልጅ ጣጣዋ ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ ውጣ ውረዱን ለማለፍ እንችላለን ብለን ውስጣችንን ማሳመን አለብን። አካል ጉዳተኛ መሆኔን አምኜ ከተቀበልኩኝ እችላለሁ የሚለውን አስተሳሰብ ለሌሎች ማንፀባረቅ እችላለሁ፡፡
“መጀመሪያ ራሴን ማሳመን አለብኝ። ከዚያም ቤተሰቦቼን ማመን አለባቸው። በመጨረሻም ማህበረሰቡ ማመን አለበት። ለዚህ ታድያ እኛው ራሳችን ግንዛቤ ማስጨበጥ ይጠበቅብናል” ስትል አፅንኦት በመስጠት ተናግራለች፡፡
“በተለይ የተማረው ማህበረሰብ ለአካል ጉዳተኞች የሚያሳዩት አመለካካት ጥሩ አይደለም። ቅጥር ላይ ብዙ እንግልት ይደርስባቸዋል፡፡ ሴቶች ላይ ደግሞ እንግልቱ ይብሳል፡፡ ለፀሀፊነት እንኳን አይቀጥሯቸውም፡፡ እንደዚህ አይነት አመለካከት ሊቀረፍ ይገባል፡፡ አሁን አሁን ላይ በርግጥ መሻሻሎች ይታያሉ ግን ሙሉ ለሙሉ አመለካከቱ አልተቀረፈም፤ መስተካከል አለበት፡፡” ስትል ኮንናለች፡፡
“በመጀመሪያ ደረጃ ማመስገን የምፈልገው ፈጣሪን ነው፡፡ በመቀጠል ደግሞ ቤተሰቦቼን። እዚህ ለመድረሴ ምክንያት ናቸው፡፡ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ ማስተርስ ተምሬ እስክጨርስ እናቴ ከጎኔ ነበረች፡፡ እናቴን በልዩነት ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ አጠቃላይ ቤተሰቦቼ ያላቸው ድጋፍ የተለየ ነበር፤ በቃላት ለመግለፅ ይከብደኛል፡፡
“በመጨረሻም መሀመድ ሸይቾ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበር ሰብሳቢ ነው፡፡ እሱን ማመስገን ይፈልጋለሁ። ማስተርሴን ለመማር የወጪ መጋራት ክፍያ መክፈል አቅቶኝ አልማርም ብዬ ተስፋ ቆርጬ ነበር፡፡
“መሀመድ ሸይቾ ‘እኔ እያለሁ አታቋርጪም፤ አካል ጉዳተኛ ሆነሽ ያገኘሽውን ዕድል መተው የለብሽም’ ብሎ በራሱ ወጪ ከፍሎልኝ መማር ችያለሁ፡፡ ለእኔ ብቻ አይደለም አካል ጉዳተኛ ለሆነውም፤ ላልሆነውም እንዲሁም ደግሞ በገንዘብም ሆነ በሀሳብ ድጋፍ ከማድረግ ወደ ኋላ ብሎ አያውቅም፡፡ እኛም ካመንንበት እና ከሰራን በትምህርቱም፤ በኢኮኖሚውም ትልቅ ደረጃ መድረስ እንችላለን፡፡ አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም፡፡” ስትል በልበ ሙሉነት ትናገራለች፡፡
More Stories
“መምህርነት የትውልድን አደራ የምትሸከምበት ክቡር ሙያ ነው” – መምህር ተስፋዬ ገብረእስጢፋኖስ
“ጥጃን በጆሮው የምትጎትተው ቀንድ ከማብቀሉ በፊት ነው” – የሀገር ሽማግሌ አቶ ሁዱጋ ሰዲቃ
ኦሾአላ ÷ ከእግር ኳስ ተጫዋችም፣ ባሻገር