“መምህርነት የትውልድን አደራ የምትሸከምበት ክቡር ሙያ ነው” – መምህር ተስፋዬ ገብረእስጢፋኖስ

“መምህርነት የትውልድን አደራ የምትሸከምበት ክቡር ሙያ ነው” – መምህር ተስፋዬ ገብረእስጢፋኖስ

በመሐሪ አድነው

መምህር የሰውን ልጅ አእምሮ እንደ ጥሩ አናጺ የጎበጠውን ጠርቦ የሚያቀና፣ ብሩህ ተስፋ በሚፈነጥቁ ቃላቶች አእምሮን በመገንባት የሰዎችን የህይወት ሚዛን ያስተካክላል፡፡

መምህር የጥሩ ስነ-ምግባር ምሣሌ፣ የነገ ብሩህ ተስፋ አብሣሪ፣ የተጐላደፈን አስተሳሰብ በተስተካከለ አመለካከት በመተካት የቀና ጐዳና ጠራጊ የህይወት አባት ነው፡፡ የሰው ልጅን አእምሮ ከፈጣሪ በታች ማስተካከልና እንደገና መፍጠር የሚችለው መምህር ነው፡፡

ዛሬ በእድገት ማማ ላይ ያሉ ምዕራባውያን ሃገሮች የትናንት ድህነታቸው ተወግዶ በዛሬ ልዕልናቸውና ክብራቸው የተተካው ያለመሰልቸት ያላቸውን እውቀት ለትውልዳቸው በማካፈላቸውና ለዕለት እንጀራቸው ሣይሆን ለትውልዳቸው በመኖራቸው ነው፡፡

ከአነስተኛ ፈጠራ እስከ ከፍተኛ የጠፈር ምርምር ድረስ እየተከናወኑ ያሉ የወቅቱ የአለማችን ክስተቶች መሰረታቸው መምህር ነው፡፡ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ህዝቦች የሚመሩ የሃገራት መሪዎች ከጀርባቸው መምህራን አሉ፡፡

የዛሬው ባለታሪካችን አቶ ተስፋዬ ገብረእስጢፋኖስ ይባላሉ፡፡ ትውልዳቸው በ1946 ዓ.ም በቀድሞ አጠራሩ በጀምጀም አውራጃ ሶላሞ ወረዳ ነው፡፡ በወቅቱ እዚያ አካባቢ መደበኛ ትምህርት ቤት ስላልነበረ ትህርታቸውን በቄስ ትምህርት ቤት ነበር የገቡት ፡፡እዚያም እስከ ወንጌል ድረስ ተምረዋል፡፡

ሶላሞ ወረዳ መደበኛ ትምህርት ቤት የተከፈተው በ1957 ዓ.ም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የቄስ ትምህርት ተምረው ለመጡት ለእነ አቶ ተስፋዬ ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረላቸው፡፡

የተመዘገቡት ቁጥራቸው ጥቂት የሆኑ ተማሪዎች ሲሆኑ እነርሱም የቄስ ፊደል የቆጠሩ በመሆናቸው ከአንደኛ ክፍል በአንድ ዓመት ደብል መትተው ወደ ሁለተኛ ክፍል፤ በቀጣይም አመት እንደዚሁ ደብል መትተው ከሶስተኛ ክፍል ወደ አራተኛ ክፍል እያሉ በ1959 ዓ.ም በሁለት አመት አራተኛ ክፍል ደረሱ፡፡

ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ትምህርት በወቅቱ የነበረው ትምህርት ቤት ክብረመንግስት፣ ሀገረሰላም፣ ይርጋዓለም እና ወላይታ ስለሆነ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በሀገረሰላም ወረዳ ደጃዝማች ባልቻ ትምህርት ቤት ነው የተከታተሉት፡፡

እዚያም የደረጃ ተማሪነታቸውን ሳይለቁ ቀጥለው የስምንተኛንም ክፍል ሚኒስትሪ በጥሩ ውጤት አለፉ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በይርጋዓለም የእርሻ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡

በተማሪዎች እንቅስቃሴ በ1966 ዓ.ም የንጉሡ ስርዓት ተገረሰሰ፡፡ ወታደራዊው የደርግ መንግስት ስልጣን ላይ እንደወጣ የእድገትና የስራ ዘመቻ ሲታወጅ ከተማሪዎች ጋር እርሳቸውም ቦረና ያቬሎ ለሁለት አመታት ዘምተዋል፡፡

ከዘመቻ መልስ በሀገሪቱ የተለያዩ የአመጽ እንቅስቃሴዎች ስለነበሩ የደህንነት ስጋት በሀገሪቱ ሰፍኖ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ተሰፋዬ፣ ይህን ክፉ ጊዜ ለማለፍ በ1972 ዓ.ም በድጎማ ተቀጥረው በአለታ ወንዶ ለሁለት አመታት በመምህርነት አገልግለዋል፡፡

በ1974 ዓ.ም ደግሞ ለቋሚነት ሲወዳደሩ በአጋጣሚ የነበራቸው የእርሻ ትምህርት ሰርተፊኬት ስለነበራቸው አለፉ። የተማርኩበትና የማውቅበት ቦታ ይሻለኛል ብለው ወደ ሀገረሰላም ሄደው ደጃዝማች ባልቻ ትምህርት ቤት የማስተማር ስራ ጀመሩ፡፡

ለስራውም ፍቅርና ክብር ስለነበራቸው ምንጊዜም ከማለዳው 12፡30 ጀምሮ ከትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ አይታጡም፡፡ በመሆኑም የስራ ትጋታቸው ታይቶ በዚያው አመት ዩኒት መሪ ሆነው ተመረጡ፡፡ ብዙም ሳይቆይ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገብተው ሰለጠኑና የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ሆኑ፡፡

አቶ ተስፋዬ በኩራት ከሚናገሩት በተለይ በ1975 እና 1976 ዓ.ም ባልቻ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ የተፈተኑ ተማሪዎች በሙሉ ዘጠና ዘጠኝና መቶ ከመቶ ውጤት አስመዝግበው ወደ ዘጠነኛ ክፍል ያለፉበትን ወቅት ነው፡፡

ውጤቱን የተመለከተው በቀድሞ አጠራሩ የሲዳሞ ክፍለ ሀገር ትምህርት ቢሮም “ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? የባልቻ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ይህን ውጤት ያመጡት ተኮራርጀው ነው ወይስ እንዴት ነው?” የሚለውን ለመገምገም መምጣታቸውንም ያስታውሳሉ፡፡

ቢሮው ግምገማውን ካካሄደ በኋላ በእሳቸው በግል ጥረት የመጣ ውጤት መሆኑን አረጋግጦ ለትምህርት ቤቱ የደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶን ፎቶ በፍሬም ተደርጎ ለእርሳቸው ደግሞ የእውቅና ምስክር ወረቀት አበርክቶላቸዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ የባልቻ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሆነው ካገለገሉበት ከ1974 እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ ሚኒስትሪ የወደቀው አንድ ተማሪ ብቻ ነበር፤ እርሱም ታይፎይድ ታሞ ቆይቶ የመጣ ተማሪ ሲሆን አቶ ተስፋዬ ይቅርብህ እያሉት ሳይዘጋጅ ተፈትኖ የወደቀ ተማሪ ነው፡፡

አቶ ተስፋዬ እንደሚሉት ይህ ውጤት የሚመጣው ዝም ብሎ አይደለም። የትምህርት ቤቱ ጠንካራ መምህራን የሚመደቡት በታችኛው የክፍል ደረጃ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል በመሆኑ ተማሪዎች በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነቡ ናቸው፡፡

አንድ ለአምስት አደረጃጀትም የተጀመረው አሁን አይደለም፤ የትህርት ቤቱ ተማሪዎች በአንድ ለአምስት ማለትም ከፍተኛ ሁለት፣ መካከለኛ ሁለት ዝቅተኛ ደግሞ አንድ ተደርጎ ይደራጁና ከፈረቃቸው ውጭ ቤተ መጻህፍት ገብተው እርስ በርስ እንዲማማሩና እንዲጠያየቁ ይደረጋል፡፡

በዚህ ሂደት ደካማው ወደ መካከለኛ፣ መካከለኛው ወደ ከፍተኛ እንዲመጣና ተያይዘው እንዲሄዱ ይደረጋል። ከዚህም ባሻገር በ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በየአስራ አምስት ቀኑ የቀለም ትምህርት ውድድር ይካሄዳል፡፡ ጥያቄዎች የሚዘጋጁት በመምህራን ሲሆን በትምህርት ቤት ውድድር ከ1ኛ እስከ 3ኛ የወጡ ተማሪዎች ከአካባቢ ትምህርት ቤቶች ጋር ውድድር ይደረጋል፡፡

በዚያን ጊዜ ኩረጃ የሚባል ነገር የለም። የነበረው ተማሪ በራሱ የሚተማመን ነው፤ መምህራንም ኩረጃን የሚፈቅዱ አይደሉም። በፈተና ወቅት የተለየ ክፍል (ስፔሻል ክላስ) የሚባል የፈተና ክፍል በክፍል ደረጃቸው ከ1ኛ እስከ 10ኛ ለወጡት ይዘጋጃል፡፡

በእነዚህ ክፍሎች የሚፈተኑት ሁሉም የደረጃ ተፎካካሪ ስለሆኑ ኩረጃ አይታሰብም። በሌሎቹ ክፍል ተፈታኞች ግን ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ ይህን ብልሃት ያመጡት አቶ ተስፋዬ ሲሆኑ ተሞክሮው ተወስዶ ወደ ሌሎች የአውራጃው ትምህርት ቤቶችም እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡

በትምህርት ጥራቱ የደጃዝማች ባልቻ ትምህርት ቤት ተመራጭነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጣ፡፡ በመሆኑም ተጨማሪ ክፍሎችን መገንባት የግድ ሆነ፡፡

አቶ ተስፋዬ በዚህ ወቅት ለክፍለ ሀገሩ ትምህርት ቢሮ ማመልከቻ በማስገባት የማስፋፊያ ፈቃድ አግኝቶ ህብረተሰቡን በማስተባበር በ1981 ዓ.ም በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ወደ ስምንት የመማሪያ ክፍሎች፣ አንድ ቤተ መጽሀፍት ከመጸዳጃ ቤት ጭምር አስገንብተው ትምህርት ቤቱን በማሳደግና የተማሪዎችን ቁጥር በመጨመር ውጤቱም እያደገ እንዲሄድ በማድረግ እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ ለ16 አመታት በትጋት በማገልገልና የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ምስጉን ርዕሰ መምህር መሆን ችለዋል፡፡

ደጃዝማች ባልቻ ትምህር ቤት ተምረው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሚኖሩትን የቀድሞ ተማሪዎቻቸውን ሲያገኙ ታማኝነታቸውንና ለስራ ያላቸውን ትጋት ሲመለከቱ ከፍተኛ ኩራትና ክብር እንደሚሰማቸው አቶ ተስፋዬ ይናገራሉ፡፡

ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሀዋሳ ተዛወሩ። ሀዋሳም ሲመጡ ስማቸው ተከትሎ በመምጣቱና የስራ ብቃታቸው ስለሚታወቅ በንግስት ፉራ ትምህርት ቤት ዋና ርዕሰ መምህር ቢታጩም ቀድማ የነበረችውን ሴት ርዕሰ መምህርት ላለመጋፋት በምክትልነት ማገልገል እንደሚፈልጉ በመግለጽ በምክትልነት እየሰሩ እዚያም ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡

የትምህርት ደረጃቸውን በማሻሻል በክረምት መርሀ ግብር ዲፕሎማ እና የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ መያዝም ችለዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ ገብረእስጢፋኖስ በእውቀታቸውም በልምዳቸውም ትውልድን በእውቀትና በምግባር በማነጽ አገልግለው ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የጡረታ መብታቸውን አስከብረው አሁን ላይ በጡረታ ላይ ይገኛሉ፡፡

አሁን ላይ ጊዜው ለትምህርት በብዙ ነገር የተሻሻለና ለመማር ማስተማርም በቴክኖሎጂ ጭምር የተደገፈ መሆኑ የሚደነቅ ቢሆንም ከተማሪዎች ስነ-ምግባር አንጻር የሚስተዋለው ሁኔታ ከቀደሙት ተማሪዎች አኳያ ሲነጻጸር ከፍተኛ ችግር ያለበት በመሆኑ የሚያሳዝናቸው ጉዳይ ነው፡፡

በእርሳቸው ጊዜ የነበሩ ተማሪዎች ለመምህራን ያላቸው ክብር የተለየ ከመሆኑ የተነሳ አሁን ድረስ የቀድሞ ተማሪዎቻቸው ሲያገኟቸው የሚያሳያሳዩዋቸውን ክብር ሲመለከቱ ኩራት ይሰማቸዋል፡፡

አሁን ዘመኑ ጥሩም ነው መጥፎም ነውማለት ይቻላል፡፡ ዘመኑ ያመጣውን እድል ለሚጠቀም ተማሪ በርካታ የተመቻቹ ነገሮች አሉት ነገር ግን የአሁን ተማሪ እነዚህን እድሎች በተለይም ከቴክኖሎጂ አንጻር ያለውን ለመልካም ነገር ከመጠቀም ይልቅ ለአልባሌ ነገሮች ሲያውላቸው ይታያል፡፡ በዚህም ያልሰራውን ውጤት ለማግኘት የሚፈልግ ተማሪ የበዛበት ሁኔታ ተፈጠረ።ከዚህ ጋር ተያይዞ ኩረጃ ባህል እስከመሆን ደረሰ፡፡ ትምህርት ቤቶችም ስማቸውን ለማስጠራት ኩረጃን ማበረታታት ጀመሩ። ይህ ነገር በፍጥነት የማስተካከያ እርምጃ ካልተወሰደበት የመጪው ትውልድ ነገር አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል ስጋት አለባቸው፡፡