“ጥጃን በጆሮው የምትጎትተው ቀንድ ከማብቀሉ በፊት ነው” – የሀገር ሽማግሌ አቶ ሁዱጋ ሰዲቃ

“ጥጃን በጆሮው የምትጎትተው ቀንድ ከማብቀሉ በፊት ነው” – የሀገር ሽማግሌ አቶ ሁዱጋ ሰዲቃ

በደረሰ አስፋው

የሣምንቱ የንጋት እንግዳችን የጋሞ የባህል መሪ ናቸው፡፡ በመምህርነት ከ30 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ በሌሎች የስራ ዘርፎችም ከባለሙያነት እስከ ኃላፊነት ተመድበው ህዝብን አገልግለዋል፡፡ ዛሬ ከስራቸው በጡረታ ቢሰናበቱም በሀገር ሽማግሌነት ህዝብን እና ሀገርን እያገለገሉ ነው፡፡ የንጋት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ከእኚህ የሀገር ሽማግሌ ጋር ቆይታ አድርጋ ተከታዩን ጥንቅር አቅርባለች፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ንጋት፡በመጀመሪያ እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍላችን ስም ላመሰግን እወዳለሁ፡፡

አቶ ሁዱጋ፡ እኔም አመሰግናለሁ ጎንበስ በማለት፡፡

ንጋት፡በመተዋወቅ እንጀምር፤ ስምዎትን ማን ልበል?

አቶ ሁዱጋ፡ አቶ ሁዱጋ ሰዲቃ እባላለሁ፡፡ የጋሞ የሀገር ሽማግሌ ነኝ፡፡

ንጋት፡ትውልድና እድገትዎን አያይዘው ቢገልጹልኝ?

አቶ ሁዱጋ፡ የተወለድኩት በቀድሞው የጋሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት በጋርዱላ አውራጃ ቦንኬ ወረዳ ነው፡፡ ዕድገቴም ሆነ የ1ኛ ደረጃ ትምህርቴን በቦንኬ ወረዳ ቦንኬ በዛ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 6ኛ ክፍል ተከታትያለሁ፡፡ በዘመኑ ትምህርት ቤት በየአካባቢው ባለመኖሩ የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ከጊዶሌ ይልቅ ከምባ ይቀርበኝ ስለነበረ ወደ ከምባ በመሄድ ነው የተማርኩት፡፡

ንጋት፡ከምባ ዘመድ ነበር ማለት ነው?

አቶ ሁዱጋ፡ አይደለም፡፡ ቤት ተከራይቼ ነው። በወቅቱ በተማሪዎች መካከል ከፍተኛ የትምህርት ውድድር ነበር፡፡ እኔም ተወዳዳሪ ለመሆን ከጓደኞቼ ጋር ለማጥናት እንዲመቸኝ መከራየት ነበረብኝ። ለዚህም ከአካባቢያቸው ርቀው ሄደው ከሚማሩ ጋር በጋራ ቤት ተከራይተን ነው የተማርነው፡፡ ችግር እንኳ ቢኖር የትምህርቱን ጥቅም እናስቀድም ነበር። በአንድ ክፍል ውስጥ 6 ተማሪዎች አብረን ነበር የምንኖረው፡፡ የቤት ኪራይም በእያንዳንዳችን አንድ ብርና ከዚያ በታች ነበር የሚደርስብን። በሠላም አብሮ መኖር፣ ማጥናቱ፣ በጋራ መውጣት መግባቱ እና ሌሎችም ጥቅሞች አሉት፡፡ ለዚህ ነው ዘመድ ቢኖርም ተከራይቼ ለመኖር የመረጥኩት፡፡ ይህም ለጋራ አላማ በጋራ እንድንተጋ ይረዳን ነበር፡፡

ንጋት፡የቀለብስ ነገር እንዴት ነበር? ማንስ ነበር የሚያዘጋጀው?

አቶ ሁዱጋ፡ (ሳቅ በማለት) የምንጋግረው እኛው ነበርን፡፡ እንጨት እንለቅማለን፡፡ ምግባችንን በሚመቸን መልኩ እናዘጋጃለን። ከሰኞ እስከ አርብ ከተማርን በኋላ ቀለብ ካለቀ ወደ ቤተሰብ በመመለስ ቀለባችንን እናመጣለን፡፡ በወቅቱ ተሽከርካሪ ስላልነበረ የ6 ሰአት የእግር መንገድ ተጉዘን ነበር ቤተሰብ ጋር የምንደርሰው። የጉዞውን ጫና ለመቀነስ አንዳንድ ጊዜ የወር ቀለብ በአህያ ወይም በፈረስ ጭነን እናመጣለን፡፡ ያልተፈጨ እህል ካመጣንም እኛው እናስፈጫለን፡፡ ጊዜው እንዳሁኑ ባለመሆኑ ለመበያ የሚሆን ጎመን የሰው ጓሮ ተገብቶ ቢቆረጥ ለምን የሚል አልነበረም፡፡ በዚህ መልኩ ከምባ እስከ 8ኛ ክፍል ተምሬያለሁ። ግጭት የሚባል አልነበረም፤ ፍቅርና እርስ በእርስ መተሳሰብ እንጂ ጠብ ስላልነበር በጣም ደስተኞች ነበርን፡፡ 

ንጋት፡8 ክፍል በኋላ የነበረው ትምህርትዎን ቀጠሉ ወይስ አቋረጡ?

አቶ ሁዱጋ፡ የሚኒስትሪ ውጤቴን አይቼ ማለፌን ካረጋገጥኩ በኋላ ወደ አርባ ምንጭ ከተማ ነው የሄድኩት፡፡ ይሁን እንጂ ትምህርቴ እንቅፋት አጋጠመው፡፡ ወቅቱ በሀገራችን የነበረውን የፊውዳሉን ስርአት በመጣል ወታደራዊ መንግስት ስልጣኑን የያዘበት ጊዜ ነበር፡፡

እንደማንኛውም የዘመኑ ወጣት የፊውዳሉን ስርአት በመቃወም ተሳትፎ ነበረኝ፡፡ ለውጡ ግን እንዳሰብነው ሳይሆን አቅጣጫውን ቀየረ። በዚህም ምክንያት በወታደራዊ መንግስት ላይ ተቃውሟችንን ማሰማት ጀመርን፡፡ በዚህም ለእስራትና ግርፋት ተዳረኩ፡፡

እኔና መሰሎቼም ከግድያው ብንተርፍም ለ3 ዓመት ታሰርን፡፡ ምሁሩ፣ ሰራዊቱና መላው ወጣት በዚህ ሂደት ተሳትፏል፡፡ ብዙ የህይወት ዋጋም እንደተከፈለበት አስታውሳለሁ፡፡ ነገር ግን ስልጣኑ በደርግ እጅ ላይ ከወደቀ በኋላ የአጼውን ስርአት ታግለው በጣሉት ምሁራንና ወጣቶች ዘንድ እንደታሰበው አልሆነም፡፡ በዚህም ወጣቱና ምሁራን ሌላ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ደርግን መቃወም ጀመርን፡፡ በዚህም ቀይ ሽብር የሚባል ነገር ተፈጠረና ደርግን የሚቃወሙ ሀይሎችን ማሰር ብሎም መግደል በስፋት ይፈጸም ጀመር፡፡ የበርካታ ወጣቶችና ምሁራንም ደም በከንቱ ፈሰሰ፡፡ እኔ በፈጣሪ ፈቃድ ከግድያ ብተርፉም ከእስር ግን አላማለጥኩም፡፡

ንጋት፡እርስዎ ከግድያ መትረፈዎ ሌላ እንድምታ ነበረው?

አቶ ሁዱጋ፡ አጋጣሚው ነው እንጂ እኔ ከሌላው የተለየሁ ሁኜ አይደለም፡፡ በወቅቱ የክፍለ ሀገሩ የደርግ ከፍተኛ አመራር አቶ አሰፋ ጫቦ ይባሉ ነበር፡፡ እኚህ ከፍተኛ የክፍለ ሀገሩ ባለስልጣን በግድያ እምነት አልነበራቸውም። ስለተቃወመ ብቻ ሰው መገደል የለበትም፤ እንዲያውም ተቃውሞ ለውጥን ያመጣል የሚል አስተሳሰብን የሚያራምዱ አመራር ነበሩ፡፡ ለተቃውሞው ምላሽ መስጠት ነው እንጂ በመግደል ሀገር አይገነባም የሚል አቋም ነበራቸው፡፡ ከግድያ ይልቅ ማረሚያ ውስጥ አስገብቶ እንዲታረሙ ማድረግ ይሻላል የሚል አስተሳሰብ የነበራቸው ናቸው፡፡ በዚህም ወደ ጨንቻ ማረሚያ ቤት እንድንዛወር ተደረገ። በወቅቱ የነበሩ አንድ የደርግ አመራር እኛን ለመግደል በሚመጡበት ዕለት እንዳጋጣሚ ከአርባ ምንጭ ማረሚያ አውጥተው ወደ ጨንቻ ማረሚያ ቤት አዛወሩን፡፡ እንዲያውም እርምጃ ተወስዶባቸዋል በሚል ምላሽ ተሰጠ፡፡ በዚህ ልክ ከተረፉት ጥቂት ሰዎች መካከል ነኝ፡፡

ንጋት፡ከእስር ከተፈቱ በኋላስ የነበረዎ ህይወት ምን ይመስላል?

አቶ ሁዱጋ፡ ከማረሚያ ከወጣሁ በኋላ ያቋረጥኩትን ትምህርት ነው የቀጠልኩት፡፡ ከ9ኛ ክፍል ጀምሬ 12ኛ ክፍልን አጠናቅቄ ወደ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በመግባት በቋንቋና ስነ ጽሁፍ የትምህርት ዘርፍ በ1973 ዓ.ም ተመረቅኩ፡፡ ከተመረቅኩ በኋላም በእጣ ወደ ጎንደር ክፍል ሀገር ተመድቤ ስማዳ፣ ጋይንት፣ ደባርቅና ደብረታቦር አካባቢዎች በመዘዋወር ለ12 ዓመታት አገልግያለሁ። በዲፕሎማ የጀመርኩት የመምህርነት ሙያዬንም በስራ ላይ ስልጠና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመግባት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቅኩ፡፡ ትዳር መስርቼም ሁለት ልጆችን ያፈራሁት እዚሁ ጎንደር በነበርኩበት ጊዜ ነው፡፡ ከዛም ወደ ኦሮሚያ ክልል አዳማ (ናዝሬት) ተዛውሬ ለ14 ዓመታት በመምህርነት አገልግያለሁ፡፡ ወደ ትውልድ አካባቢዬ በመዘዋወርም በመምህርነትና በሌሎች የኃላፊነት ቦታዎች ለ20 ዓመታት አገልግያለሁ፡፡

ንጋት፡ጡረታ ከመውጣትዎ በፊት በኃላፊነት የሰሩባቸው ተቋማት አሉ?

አቶ ሁዱጋ፡ አዎ፡፡ ከማስተማር ባሻገር በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተመድቤ ህዝብንና ሀገርን አገልግያለሁ፡፡ የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ፣ የትምህርት መምሪያ ኃላፊ፣ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ሆኜ ሰርቻለሁ። ባለህ አቅምና ዕውቀት ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል የአዕምሮ እርካታ ለመንፈስም ደስታ ይሰጣል፡፡ የጡረታ ጊዜዬ ከመድረሱ ቀድሜ ነው ጡረታ የወጣሁት፡፡ ከጡረታ በኋላም ቢሆን መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ (ናይስ ኢንሹራንስ) የተቋሙ አስተዳዳሪ ሆኜ ለ5 ዓመታት አገልግያለሁ፡፡

ንጋት፡የጋሞ የባህል አባት ሆነው በሽምግልና እያገለገሉ ነው፡፡ ወደዚህ እንዴት ሊገቡ ቻሉ?

አቶ ሁዱጋ፡ ወላጅ አባቴ የባህል አባት በመሆን ለአመታት ህዝብን አገልግለዋል። የተጣላን በማስታረቅ በሰዎች መካከል እርቅን ያወርዳሉ። ለተገፋውም እውነትን በመፍረድ እንባ ያብሳሉ። ይህን ጠቃሚ እሴት እያየሁ አድጌያለሁ፡፡ ዛሬም ይህን ከቤተሰብ በመውረስ እኔም የበኩሌን ድርሻ ለመወጣት እየሰራሁ ነው፡፡ በባህላችን መሰረት እናትና አባትን ባለን አቅም መደገፍ የተለመደ ነው። ሲታመሙ ማስታመምና ተንከባክቦ የአባትን ምርቃት መቀበል በጋሞ ባህል የግድ ይላል። ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት በነበርኩበት ቦታ ምቾት ቢኖረኝም እንኳ የባህሉን ወግና ስርአት በማክበር ቤተሰቦቼን ለመንከባከብ ስል ነው ወደ ትውልድ አካባቢዬ የመጣሁት፡፡

ወደ ትውልድ አካባቢዬ ከመጣሁ በኋላ የመምህርነት ስራዬን እየሰራሁ ቤተሰቦቼንም እደግፋለሁ፡፡ ሲያማቸው አስታምማለሁ፡፡ ሲቸግራቸው ከጎናቸው አልተለየሁም፡፡ ከዚህ የበጎነት ስራ ከአባቴ የወረስኩት ስራ ዛሬም ይህን ሀላፊነት በመረከብ የጋሞ የባህል አባት ሆኜ በማገልገል ላይ እገኛለሁ፡፡

ንጋት፡አሁን በሽምግልና እየሰሩ ያለውን ስራ ቢገልጹልኝ?

አቶ ሁዱጋ፡ አሁን ባለኝ ዕድሜ ከአባቴ በወረስኩት የሽምግልና ባህልና ወግ እንዲሁም ያለኝን የህይወት ተሞክሮ በመጠቀም ትውልዱን በመምከርና በማስተማር ሰላምንና ፍቅርን ለትውልዱ በማስተማር እያገለገልኩ እገኛለሁ። በሀገር ሽማግሌነት በአካባቢዬ ብሎም በሀገር ሰላምና መረጋጋት እንዲጸና የድርሻዬን እየተወጣሁ ነው። በዚህም በጋሞ ዞን አንጻራዊ ሠላም ተፈጥሯል፡፡ ይህ ለማንም የተሰወረ አይደለም። በመገናኛ ብዙሃን ጭምር እንደ አብነት የሚገለጽ ነው፡፡ በሰላም እጦት ወይም በዘር ልዩነት ችግር ያልተከሰተበት፣ ንብረት ያልወደመበት፣ የሰዎች ሞትና መፈናቀል ያልተከሰተበት አካባቢ ቢፈለግ በግንባር ቀደምትነት የጋሞ አካባቢ የሚጠቀስ ነው። ይህን በጎና በፈጣሪም ዘንድ የተወደደ ተግባርን ነው እያከናወንኩ ያለሁት፡፡

ንጋት፡በዚህ አኩሪ ባህል ላይ የመደብዘዝ አደጋ ገጥሞት ነበር ይባላል? ይህን ጊዜስ ያስታውሳሉ?

አቶ ሁዱጋ፡ በኢትዮጵያ የመንግስታት ታሪክ በተለይ ባህል እንዲጠፋ፣ እንዲደበዝዝ የተደረገበት ጊዜ ይኖራል፡፡ አሁን ትውልዱ ረስቶት የነበረውንም ወደ ኋላ መለስ ብለን የቀደሙ አባቶቻችን ባህል በመያዝ ትውልዱ በባህል እንዲመራ እያደረግን ነው።

ሰው መግደል፣ ሀብት ማውደም መቀጠል የለበትም የሚል የጸና አቋም ተይዞ ነው በትውልዱ ላይ እየተሰራ ያለው፡፡ ችግሮች ሲከሰቱም ወጣቶች ፊት ቆመን መክረንና ገስፀን ከጥፋታቸው እንዲታቀቡ እናደርጋለን። በዚህም ወጣቶች የሽማግሌዎችን ምክርና ተግሳጽ ሰምተው ለባህላቸው ታዛዥ በመሆናቸው እደሰታለሁ፡፡

ትውልዱ አምጾ ወደ ክፋትና ጥፋት አለመሰማራቱ ምክርና ተግሳጽን የሚሰሙ በመሆናቸው ስለሆነ ደስተኛ ነኝ፡፡ በዚህም የጋሞ አባቶች የሠላም አምባሳደር ሆነን በተለያዩ መድረኮች በሰራነው አኩሪ ተግባር እየተወደስን ለሽልማትም በቅተናል፡፡ ይህ አኩሪ ተግባርም እንደ ሀገር እንዲቀጥል እንፈልጋለን፡፡ የሀገር ህልውና ከሌለ ሀይማኖት የለም ወልዶ መሳም የለም፤ ሰርቶ ንብረት ማፍራት የለም፡፡

በመሆኑም በአንድ ወቅት ደብዝዞ የነበረው ድንቅ ባህላችን መልሶ ይዘቱን ሳይቀይር እንዲቀጥልና ሀገርም ከዚህ እንድትጠቀም በአዲስ አስተሳሰብ እየሰራን ነው፡፡ ዛሬ መንግስት አልባ የሆኑ ጎረቤት ሀገራትና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ እንደ የመን፣ ሶሪያና መሰል ሀገራት ማንነት የሌላቸው ሆነው አይደለም፤ ሰላም ስላጡ እንጂ፡፡ ስለዚህ እኛም ማንነታችንና ሀብት ንብረታችን የተከበረ እንዲሆን ሠላም ቀድሞ መኖር አለበት የሚል ሀሳብ ይዘን ነው ከባልደረቦቼ ጋር አበክረን እየሰራን ያለነው፡፡

ንጋት፡በስራ አጋጣሚ ብዙ ቦታዎችን የማየት ዕድል ይኖርዎታል፡፡ በሌሎች አካባቢ ያሉ ባህልና እሴቶች ግጭትን እንዴት መግታት አልቻሉም? በዚህ ላይ ያለዎት ሀሳብ ምንድነው?

አቶ ሁዱጋ፡ እርግጥ ነው በስራ አጋጣሚ ብዙ ቦታዎችን ተመልክቻለሁ፡፡ በጎንደርና አካባቢው በደብረታቦር፣ ስማዳና ደባርቅ ሰርቻለሁ። በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል አዳማ ላይ ሰርቻለሁ፡፡ በዚህም በእያንዳንዱ አካባቢ ሰላምን የማይሰብክ ባህልና እምነት የለም፡፡ ይሁን እንጂ ሰላምን ስለሰበክን ብቻ ሰላም አይመጣም፡፡ ለሰላም ሃላፊነት መውሰድ ይገባል፡፡ ሞትም ካለ መጋፈጥ ይገባል፡፡ ህይወት ጠፍቶ፣ ንብረት ወድሞ፣ ሰዎች ከቀያቸው ከተፈናቀሉ በኋላ አይደለም ሽምግልና መሆን ያለበት፡፡ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ተከታትሎ ከምንጩ አስቀድሞ ማድረቅ ነው፡፡

አንድ አባባል አለ “ጥጃን በጆሮው የምትጎትተው ቀንድ ከማብቀሉ በፊት ነው” የሚል፡፡ ቀንድ ካበቀለ በኋላ ጥጃ በጆሮው አይጎተትም፡፡ ችግር ቀንድ ካበቀለ በኋላ አይደለም ወደ እርቅ የሚኬደው፡፡ ሽምግልና ችግርን በእንጭጩ የመቅጨት ባህል ነው መሆን ያለበት፡፡ ችግርን አነፍንፎ መድረስና የችግሩን ባለቤቶች ማስማማት ይገባል፡፡ ለዚህም ነው የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች የፈፀሙት ተግባር ስማቸው ሲወሳ እንዲኖር ያደረገው፡፡ በዚህም እኮራለሁ፡፡

በሌሎች አካባቢዎችም የዳበረ ባህል አላቸው። ይህን አውጥተው መጠቀም አለባቸው፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች ከቀድሞ አባቶቻቸው የወረሱትን ባህል ማስተማር፣ ለትውልዱ ማዝለቅና ማጽናት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወጣቶች ዕድሜና የዘመኑ ቴክኖሎጂ ተጽእኖ ከባህል በተጻራሪ እንዲሄዱ የሚገፋፋቸውን ተግባራት ለመከላከል አባቶች ከፊት መቅደም አለባቸው፡፡ ሃላፊነት ወስዶ መምከርና መገሰጽ ይገባል፡፡ በየአካባቢው ተሰሚነት ያላቸው የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በመላው ሀገሪቱ ግጭቶች እንዲጠፉና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር አበክረው መስራት አለባቸው።

ንጋት፡የሀገር ሽማግሌዎች በትክክል በባህሉ መሰረት ተልኳቸውን እየተወጡ ነው የሚል እምነት አለዎት?

አቶ ሁዱጋ፡ እርግጥ ነው ይህ በተግባር ሲፈተሽ ተግባራዊ ሆኗል ለማለት አያስደፍርም። በርካታ የሀገር ሽማግሌዎች መድረክ ላይ ባህላዊ ልብስ ለብሶ ከመቀመጥ ባለፈ በመድረክ ላይ የሚያወሩትን በተግባር መፈጸም ሲሳናቸው ይታያል፡፡ ህዝቡ ተቆጥቶ ሲነሳ እርስ በእርስ ሲገዳደል እየታየ ወደ ኋላ መመለስ፣ አብሮ ማበር አይጠቅምም፡፡ እኛን ቀድማችሁ ግደሉ ብሎ ፊት መውጣት ይገባል፡፡

የሀገር ሽማግሌዎች እና የባህል መሪዎች ይህን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል፡፡ ከመድረክ ባሻገር የባህል ልብስን አውልቆ ጠመንጃ የምንጨብጥ አብረን ቀስት የምንወረውር ከሆነ የሠላሙ መደፍረስ ራሳችንንም ይዞ ይጠፋል፡፡ ጋቢያችንን አውልቀን ጠመንጃ የምንተኩስ ከሆነ የምንፈልገውን ሠላም ማምጣት አንችልም፡፡ ሠላም በመድረክ ላይ ከማውራት ያለፈ የህይወት መርህ አድርጎ መተግበርን ይጠይቃል። እንደ አንድ የጋሞ አባት በመላው ሀገሪቱ ላሉ የባህል መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች የማስተላልፈው መልዕክት በየአካባቢያችን ያሉ በርካታ ጠቃሚና የሚደነቁ ባህሎች አሉ፡፡ እነዚህን ተግባራዊ እናድርጋቸው ነው፡፡ ቅድመ አያቶቻችን፣ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ያለፉበትን የሠላም ተምሳሌትነት ማጽናት ይገባል፡፡ ለልጆቻችንም ይህን ጠቃሚ ባህል ማውረስ ይገባል፡፡

ንጋት፡ከፖለቲካ አመራሩ ጋር ተቀራርባችሁ የምትሰሩበት ሁኔታ አለ?

አቶ ሁዱጋ፡ በሰላምና የጋራ በሚያደርጉን እሴቶች ዙሪያ ከአመራሩ ጋር በጋራ እንሰራለን። አመራሩ የፖለቲካ አመራር በመሆኑ የራሱ ተልዕኮ አለው፡፡ ይህንኑ ለማሳካት ነው የሚሰራው፡፡

እኛ ደግሞ በህዝቦች መካካል በጋራ በሠላም ለመኖር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ነው የምንሰራው። የፖለቲካ አመራሩ የራሱ ተግባር ሳይነካ ባህሉ ሳይረሳ ጎን ለጎን የራሳችንን ስራ እንሰራለን፡፡ የፖለቲካ አመራሩ እነሱ የመረቁትን እንድንመርቅ እና እነሱ የረገሙትን እንድንረግምላቸው ይፈልጉ ይሆናል። እኛ ደግሞ እንደ ሀገር ሽማግሌና እንደ አካባቢው የባህል አባት እውነትና ፈጣሪን ማዕከል አድርገን ነው የምንሰራው፡፡ በእድሜም ሆነ በልምድ የተሻለ ሰው በመሆናችን ጥፋተኛውን በማረም፣ መገሰጽና መመለስ ያስፈልጋል፡፡ አመራሩ የፖለቲካ መስመሩን እንዲስት ሳይሆን ከእኛ ጋር ተቀራርበው በመስራት ሰላም እንዲሰፍን፣ ልማት እንዲፋጠን በጋራ መስራት አለብን፡፡ በዚህም ተቀራርበን እንሰራለን፡፡

ንጋት፡የፖለቲካ አመራሩ ባህሉን ለፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም አያስብም?

አቶ ሁዱጋ፡ ፖለቲካውን ይዘው ባህሉን መጠቀሚያ ለማድረግ የሚደረገውን አሰራር አንደግፍም፡፡ መድረኮችን ተጠቅመው የፖለቲካ አጀንዳን የሚያራምዱ ሽማግሌዎች አይታጡም። ለፖለቲከኞችም ሆነ ከአሰራር ውጭ ላሉ ሽማግሌዎች የምንመክረው ከሰላም እሴቶቻችን ውጭ እንዳይሆኑ እና የጋራ በሆነው የሰላም አጀንዳ ላይ አብረን እንሰራለን፡፡ ሲሳሳቱም እንመክራለን እንገስጻለን፡፡

ፖለቲከኛው በተሰማራበት መስመር ስኬትን ማምጣት ነው፡፡ ሽምግልና ግን እውነት ነው፡፡ እውነት ዛሬ እውነት ሆኖ ነገ ውሸት አይሆንም፡፡ እውነትን መወገን ደግሞ ይገባል። ፖለቲከኛውም ወደ እውነት መጥቶ ሠላምን በየአካባቢያቸው እንዲያጸኑ በመነጋገር መስራት ይገባል፡፡ አሸንፎ ስልጣን የሚይዘውም ሆነ የሚሸነፈው የዚህች ሀገር ዜጋ ነው፡፡ ለዚህች ሀገር በጎ በሆነው ነገር ላይ በጋራ መስራት ይገባል፡፡

በአስተሳሰብ ሁሉም አንድ ላይሆን ይችላል። አሁን ላይ በልዩነታችን ላይ ብቻ በማተኮር ትንሹን ልዩነት ማግነንና ብዙ አንድነታችንን በማንኳሰስ የሚመጣ ችግር ለሠላማችን ጠንቅ እየሆነ ነው፡፡ ስለዚህ የሀይማኖት አባቶች፣ የባህል መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችም ይሁን የፖለቲካ አመራሩ አብዛኛውን ህዝብ ተጠቃሚ በሚያደርጉ የጋራ ጉዳዮቻችን ላይ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ከፖለቲከኛው የማገኘውን ጥቅም አጣለሁ በማለት እውነት ስቶ መሄድ ነውር ነው፡፡ ሀገር በሰላም ስትኖር የወለድኳቸው ልጆችም በሰላም ይኖራሉ፡፡ ከእኔ የተሻለ ዕድሜ ትውልዱ መኖር አለበት። ለትውልዱ የተረጋጋች፣ ያደገች፣ የለማችና በሰለጠነ አእምሮ የሚያስቡባት፤ አንዱ ሌላውን በቋንቋው፣ በዘሩ፣ በሀይማኖቱ የማይገፋባት ሀገር ለመፍጠር የፖለቲካ አመራሩ፣ የሀገር ሽማግሌው፣ የሀይማኖት አባቶችና የባህል አባቶች በሀገር ጉዳይ አንድ በመሆን መስራት ይጠበቅብናል፡፡

ንጋት፡የጋሞ አባቶችን ድንቅ ባህል ለትውልዱ ለማስተላለፍ ምን እየተሰራ ነው?

አቶ ሁዱጋ፡ ይህንን እሴት በጥናት በመደገፍና በመሰነድ ለአዲሱ ትውልድ ለማስተዋወቅ ብሎም ለሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም የእውቀት ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል እየተሰራ ነው፡፡ እሴቱንም ለቱሪዝም የገቢ ምንጭነት ማዋል የሚቻልበትን ሁኔታ ማጥናትም አብሮ የሚሰራ ነው የሚሆነው።

የጋሞ አባቶች በአለም የታወቀ ዝናን ያገኙበት ድንቅ ባህል ባለቤቶች ናቸው፡፡ ይህን እምቅ እና የካበተ ባህል ለትውልድ ለማቆየት መስራትን ይጠይቃል፡፡ ለዚህም የባህል እሴቶችን ሰንዶ ማስቀመጥ ይገባል፡፡ እስካሁን በዚህ ላይ ትኩረት ተደርጎ የተሰራ ባይኖርም የተጀማመረ ነገር ግን አለ። ባህል በአንድ ሀገር ህልውና ውስጥ ሚና አለው። ባህላዊ ስርአቶች፣ ወጎች ጠቃሚውን አጎልብቶ መሄድ ይገባል። ይህ ደግሞ እየተሰነደ ለትውልድ እየተላለፈ መሄድ ይገባል፡፡

በተለያዩ ዘመናት ባህላዊ ስርአቶችን የሚያስፈጽሙ አባቶች ኋላ ቀሮች እየተባሉ የተገፉበት ጊዜ ነበር፡፡ ባህሉን የሚፈጽም እንደ ጥፋተኛ ተቆጥሮ የሚገፋበት ጊዜ ነበር። በዚህም ንጹህ ባህሎቻችን ጠፍተዋል፡፡ አልፎ አልፎ ከቱሪዝም ጋር የሚገናኙት ባህልና ቱሪዝም በሚል በማዋሃድ መዋቅሩ ቢኖርም ባህላዊ እሴቱ የት ነው ያለው በሚል በምርምር ተደግፎ የተሰነደ ሰነድ የለም፡፡

አሁን ላይ ተሰርቶ ጥሩ ደረጃ ላይ ተደርሷል ባይባልም ጅምሮች አሉ፡፡ የሀገር ሽማግሌዎችም በተደራጀ መልኩ እንዲሰራ አመራሩን እየጠየቅን ነው፡፡ እኛ እናልፋለን ትውልድ ሊወርስ የሚገባው ባህል ሊኖር ይገባል፡፡ ጋሞ ከ42 በላይ ደሬዎች አሉት፡፡ ደሬ ባህላዊ አባቶች የሚሰባሰቡበት ባህላዊ መማክርት ነው፡፡ በራሱ አስፈጻሚ የሚመራ አደረጃጀት ቢኖረው ትውልዱ ከዚህ ምን መማር አለበት፣ በአካባቢ በባህሉ መሰረት ችግርን እንዴት ነው የሚፈታው፣ የሚለው ተሰንደው እንዲቀመጡ በማድረግ አስፈላጊ በሆኑ ጊዜ ይህን ለማከናወን ከአመራሮች ጋር እየሰራን ነው፡፡ በዚህም አመራሩ ፈቃደኛ ነው፡፡

ንጋት፡የጋሞ አባቶች የግጭት አፈታት ስርአት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት ምን እየተሰራ ነው?

አቶ ሁዱጋ፡ የጋሞ አባቶች በ2011 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ ሊከሰት የነበረውን ግጭት እርጥብ ሳር በመያዝና በመንበርከክ ማስቀረት የቻሉ ሲሆን ለዚህም በተለያዩ መድረኮች እውቅና ተሰጥቷቸዋል። የጋሞ አባቶች ግጭትን ለማብረድ እየተጠቀሙበት ያለውን ባህላዊ ስርዓት ለትውልድ ለማስተላለፍና በመላው ሀገሪቱ ለማስፋፋት ዝግጅት እየተደረገ ነው። የጋሞ አባቶች የሰላም ተምሳሌት ናቸው። እርጥብ ሳር በመያዝ ጸብንና ቁጣን የማብረድ ባህል ለዘመናት የኖረ እሴት ባለቤት ናቸው። 

የጋሞ አባቶች ችግር በመጣ ጊዜ ጉልበት ሳይሆን ትህትናን በማስቀደም ተንበርክከው ፀብን ያረግባሉ። ይህን ትልቅ ዋጋ ያለው እሴት መጠበቅና ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል። ይህንን ባህል በቋሚነት የሚጎበኝበትና ለመላው ኢትዮጵያዊያን የእውቀቱ ምንጭነት እንዲውል ለማድረግ ራሱን የቻለ አንድ ማዕከል መገንባት እንዲቻልም ከፖለቲካ አመራሩ ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡

ንጋት፡ወጣቱ ትውልድ ከጋሞ አባቶች ባህላዊ የግጭት አፈታት ምን ሊማሩ ይገባል ይላሉ?

አቶ ሁዱጋ፡ ትውልዱ ታሪኩን በአግባቡ ማወቅና ቀደምት እናትና አባቶቻችን ለሀገራቸው ምን ሠርተው አለፉ? አሁን ሀገራችን ለገባችበት ችግር መንስዔው ምንድነው? ብሎ መመርመር አለበት። ሁሉም ሰው ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል። የመቻቻል፣ የመፈቃቀር፣ የመዋደድ፣ የመረዳዳትና ሌሎችም የጋራ እሴቶቻችንን ተረክበው ማስቀጠል ይገባቸዋል። በየአካባቢው የሚፈጠሩ ግጭቶች ለማስወገድና ሰላም ለማስፈን የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በዘመናት ያበረከቱትን ሚና ተረክበው ማስቀጠል አለባቸው፡፡ ወጣቱ ትውልድ የሰላም አስፈላጊነትና የግጭት አውዳሚነት በመገንዘብ ለሰላም ዘብ እንዲቆምና ለሀገሩ እድገት የበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረግ አለበት እላለሁ።

ንጋት፡በመጨረሻ ስለ ልጆችዎ እናንሳ ስንት ልጆች አፍርተዋል? የእርስዎን ፈለግ የተከተለስ አለ?

አቶ ሁዱጋ፡ አዎ፤ የ4 ልጆች አባት ነኝ። ሁሉንም ልጆቼን አስተምሬ ለቁም ነገር አድርሻለሁ። የመጀመሪያ ልጄ የ2ኛ ዲግሪውን ይዞ በተማረበት ሙያ ሀገርን እያገለገለ ነው፡፡ 2ኛዋ ሴት ልጄ በህክምናው ዘርፍ ስፔሻላይዝ አድርጋ በሙያዋ ህዝብንና ሀገርን እያለገለች ትገኛለች፡፡ 3ኛው በኬኒያ ሀገር የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሆኖ እያገለገለ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ወደ ሀገር ውስጥ ተመልሶ በራሱ የንግድ ስራ ተሰማርቷል። የመጨረሻዋ ሴት ልጄ ደግሞ በህክምናው ዘርፍ ላይ እየሰራች ሲሆን 2ኛ ዲግሪዋን ይዛ በስነ-ተዋልዶ ጤና ዘርፍ እያገለገለች ትገኛለች። ልጆቼ ጥሩ ደረጃ በመድረሳቸውም ደስተኛ ነኝ። ልጆችን ከህጻንነታቸው ጀምሮ በስነ ምግባርና በእውቀት ኮትኩቶ ማሳደግ መልካም ስብእና ይዘው እንዲያድጉ ያደርጋል፡፡ ይህን እያደረኩ ነው ያሳደኳቸው፤ ያስተማርኳቸው፡፡                                                           

ንጋት፡ለቃለ መጠይቁ ጊዜዎትን ሰውተው ላደረግነው ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ሁዱጋ፡ እኔም ለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ፡፡