ኦሾአላ ÷ ከእግር ኳስ ተጫዋችም፣ ባሻገር

ኦሾአላ ÷ ከእግር ኳስ ተጫዋችም፣ ባሻገር

በአንዱዓለም ሰለሞን

ናይጄሪያ በአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ውጤታማ በመሆን በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፤ እስከአሁን ከተካሄዱት ውድድሮች በቅርቡ የተካሔደውንና ሞሮኮን በማሸነፍ ሻምፒዮን የሆነችበትን ጨምሮ 10 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት፡፡

በዚህ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ለዓመታት ደምቃ የታየችው የፊት መስመር ተጫዋቿ አሲሳት ኦሾአላ ደግሞ 6 ጊዜ፣ ማለትም በ2014፣ 2016፣ 2017፣ 2019፣ 2022 እና 2023 የዓመቱን የአፍሪካ (ሴት) ኮከብ ተጫዋች ሽልማት ማግኘት ችላለች፡፡

ከ2001 ጀምሮ ለተጫዋቾች በሚበረከተው በዚህ ሽልማት፣ የናይጄሪያ ተጫዋቾች 13 ጊዜ ሲሸለሙ እሷ 6 ጊዜ በሽልማቱ መድረክ ላይ በክብርና በአሸናፊነት ተገኝታለች፡፡

እ.ኤ.አ ጥቅምት 9 ቀን፣ 1994 ወደዚህች ምድር የመጣችው ይህች ተጫዋች፣ ምንም እንኳ በእግር ኳስ ዝነኛ ብትሆንም፣ ለዚህ ስኬት የበቃችው ግን እንዲህ በቀላሉ አልነበረም፡፡ ለዚህ አንዱና ዋንኛው ምክንያት ደግሞ ቤተሰቦቿ እግር ኳስ እንድትጫወት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነበር። እግር ኳስን እንደሙያ ይቅርና ለመዝናኛነት እንኳ ለመጫወት ለእሷ የማይታሰብ ነገር ነበር። አባቷ ይህን የሚፈቅዱላት አልነበሩም፡፡ ይህን አስመልክቶ በአንድ ወቅት በሰጠችው አስተያየት እንዲህ ብላለች፡-

“እግር ኳስ እንዳልጫወት በዋንኛነት እንቅፋት የሆኑኝ ቤተሰቦቼ ነበሩ፡፡ ጎዳና ላይ፣ ለጨዋታ ምቹ ባልሆነ ቦታ (ኮረኮንቻማ መንገድ) ላይ እና በውቂያኖስ ዳርቻ ከወንዶች ጋር እጫወት ነበር። ይህን የማደርገው ዝም ብዬ ዘና ለማለት ያህል ነበር፡፡ እነርሱ ግን ሁሌም ይገስጹኝና ያስቆሙኝ ነበር፡፡”

በዚህ መሀል ግን አንድ መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ አንድ ቀን የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች እሷና ጓደኞቿ ከሚጫወቱበት ቦታ አቅራቢያ ልምምድ ሲሰሩ ተመለከተች። ይህ በእርግጥም አስባው የማታውቀውና የተደነቀችበት፣ ግን ደግሞ ጥሩ አጋጣሚ ነበር። የዚያኑ እለት የአሰልጣኙን ፈቃድ ጠይቃ መጫወት ጀመረች፡፡ አሰልጣኙ እንቅስቃሴዋን አይቶ የእግር ኳስ ክህሎት እንዳላት ተገነዘበ፡፡ እንድትጫወትም ፈቀደላት፡፡ ሳታስበው ባገኘችው እድል ብትደሰትም፣ የቤተሰቦቿ ፈቃደኛ አለመሆን ግን አሳስቧት ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ አባቷ እሺ እንደማይሏት ታውቅ ነበር፡፡

ብዙ ጊዜ ከጓደኞቿ ጋር እየተጫወተች ሳለ አባቷ መምጣታቸውን አይተው ጓደኞቿ ሲነግሯት ጨዋታውን አቋርጣ ትሮጥ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ አባቷ እግር ኳስ እንድጫወት ይፈቅዱልኛል ብላ አስባ አታውቅም፡፡ አባቷ ግን ሁኔታዋን በማየትና ተሰጥኦዋን በመረዳት ሀሳባቸውን ቀየሩና ያልጠበቀችውን ብስራት ነገሯት፡፡ በወቅቱ ይህን ማመን ተቸግራ እንደነበር “በተለየ ዓለም ውስጥ ያለሁ ያህል ነበር የተሰማኝ” በማለት ስለሁኔታው ታስታውሳለች፡፡

በእንዲህ ዓይነት መልኩ ወደምትወደው ስፖርት በመምጣት ለስኬት መብቃቷ የሌሎችን ችግርና ስሜት እንድትረዳ አድርጓታል፡፡ ይህም ለብዙዎች አርዓያ ከመሆን ባለፈ፣ በርካታ ታዳጊዎችን ለመደገፍ አስችሏታል፡፡ ይህንንም እንዲህ በማለት ትገልጻለች፡-

“ስብእናዬ በተለየ መልኩ እንደተገነባ አምናለሁ፡፡ እኔ ለአዲሱ ትውልድ ድጋፍ ለማድረግ በዚህ መልኩ የተገነባሁ ነኝ፡፡”

በእግር ኳስ አካዳሚዋም ይህንኑ ተግባር በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡ አካዳሚዋ የእግር ኳስ ክህሎት ያላቸው ታዳጊዎች የሚሰለጥኑበት ብቻም ሳይሆን ትምህርታቸውን የሚከታተሉበት ጭምር ነው፡-

“በእኔ አካዳሚ የሚኖሩ ልጃገረዶች ትምህርታቸውን ይከታተላሉ፡፡ በዚህም እርግጠኛ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ ለእግር ኳስ ብለው ትምህርታቸውን እንዲተው አልመክራቸውም። ሁለቱንም ጎን ለጎን እንዲያስኬዱ ነው የምነግራቸው፡፡” በማለትም ስለሁኔታው ትናገራለች፡፡

በአካዳሚው ለተወሰኑ ታዳጊዎች የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች፡፡ ይህን አስመልክታ በሰጠችው አስተያትም፡-

“ለሁሉም ታዳጊዎች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ አንችልም፡፡ ምክንያቱም ለዚህ የሚበቃ ገንዘብ የለንም፡፡ ቢሆንም ግን የቤተሰቦቻቸውን ሸክም ልናቃልል ጥረት እናደርጋለን፡፡ ከዚህ ባሻገርም፤ ከዓለም ጋር እንዲገናኙ ሁኔታዎችን እናመቻቻለን፡፡ ይህ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ እኮ የራሳቸውን ሲቪ እንኳ መጻፍ የማይችሉ ናቸው፡፡

“ነገሩን ለሚያውቁት ቀላል ነገር ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል፡፡ ለእነሱ ግን የተወሳሰበ ነገር ነው የሚሆንባቸው፡፡ እንደእነዚህ ዓይነት ነገሮችን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ እንደእነዚህ ዓይነት እድሎችን ለእነዚህ ታዳጊዎች መፍጠርም ልናደርግላቸው የሚገባ ነገር ነው፡፡”

ከተጫዋቿ ጋር ቆይታ ያደረገው የስካይ ስፖርት ጋዜጠኛ እዚህ ጋ የግል አስተያየቱን ያክላል፤ እንዲህ በማለት፡-

“በቃለ ምልልሳችን ወቅት ውስጤን የነካኝ ነገር ኦሾአላ ምንያህል ሃላፊነቷን በትክክል ለሌሎች አርዓያ ለመሆን በሚያስችላት መልኩ እየተወጣች መሆኑን መገንዘቤ ነው፡፡ አንዳንዶች ከአንገት በላይ የሆኑበት ይህ ነገር ለእሷ ግን የእምነት ጉዳይ ነው፡፡”

ተጫዋቿ ይህን ድጋፍ ስታደርግ በእርግጥም የምታሳካውን ታላቅ ግብ ጠንቅቃ በማወቋ ነው፡፡ የነገ ጥረቷ ምን ያህል ፍሬ እንደሚያፈራ መገንዘቧም ለበርካታ ታዳጊዎች ተስፋ መሆን ችላለች፡-

“አንድ ታዳጊ ስታስተምር፣ እሱ ደግሞ ታናናሾቹንና መላ ቤተሰቡን ያስተምራል፡፡ እንዲህ ዓይነት እድሎች መገኘታቸው በአፍሪካ አስደናቂ ነገሮች እንዲከሰቱ የሚያደርግ ነው፤ ምክንያቱም በርካታ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች ስላሉ፡፡” በማለትም በታዳጊዎቹ ላይ ስላላት ተስፋ ትናገራለች፡፡

ከዚህ ተግባሯ ባሻገር፤ ታዳጊዎቹ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ የራሷን ጥረት ታደርጋለች። በዚህ ረገድ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ለማያገኙ ሰዎች ቴክኖሎጂውን ተደራሽ ለማድረግ የሚሰራ ዓለም አቀፍ ተቋም አምባሳደር በመሆን እየሰራች ነው፡፡ ጉዳዩን አስመልክታ በሰጠችው አስተያየትም፡-

“ይህ የአፍሪካዊያንን አቅም የሚገድብ ከባድ ችግር እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ መንግስታት ለዚህ ብዙም ትኩረት አይሰጡም፤ እነሱ ትልቅ ነገር እንደሆነ አያስቡም፡፡ እነሱ የሚያስቡት ኢንተርኔት እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ እንደማህበራዊ ሚዲያ ብቻ ነው የሚመለከቱት፡፡ ነገር ግን እንደዛ አይደለም፤ ታዳጊዎቹን ተጠቃሚ የሚያደርግ የፈጠራ (የቴክኖሎጂ) ግኝት ነው፡፡”

እዚህ ላይ የራሷን ተሞክሮም እንዲህ በማለት ታጋራለች፡-

“ከወኪሌ ጋር የተገናኘሁት የእግር ኳስ ክህሎቴን የሚያሳይ ቪዲዮ በኢንተርኔት ካጋራሁ በኋላ ነበር፡፡ ከዚያም ወደ ውጪ የመሄድ እድል አገኘሁ፡፡ ስለእኔ ያወቁት በፌስ ቡክ አካውንቴ አማካይነት ነበር፡፡ አብሬያቸው የተጫወትኳቸውና ይህንን እድል ባለማግኘታቸው በአጭር ጊዜ ከእግር ኳስ የተገለሉ ጓደኞች አሉኝ፡፡

“ከእነርሱ ባሻገርም ሌሎች በርካታ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎችም ይህን እድል ባለማግኘታቸው ያሰቡትን ሳያሳኩ ቀርተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ስልክ እንኳ የላቸውም፡፡ ከዓለም የሚገናኙበት ምንም ዓይነት መንገድ የላቸውም፡፡ የእኔ ህይወት የተቀየረው ግን ይህን ባደረኩበት አንድ አጋጣሚ ነው፡፡ ለዚህ እኔ ምስክር ነኝ፡፡ ይህ ያነበብኩት ታሪክ አይደለም፤ ራሴ ያየሁት የህይወት ተሞክሮ እንጂ፡፡”

ከአፍሪካ ባሻገር ከወጣትነቷ ጀምሮ በእግር ኳስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናዋ የናኘው ኦሾአላ፣ በክለብ ደረጃም በአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች ማለትም፣ ሊቨርፑል፣ አርሰናል እና ባርሴሎና በመጫወት በስፖርቱ ስኬታማ ለመሆን ችላለች። ተጫዋቿ በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካ ካሊፎርኒያ የምትኖር ሲሆን ባይኤፍሲ ለተባለ ክለብ በመጫወት ላይ ትገኛለች፡፡