ለዜጎች በሶላር ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ ስልጠና በመስጠት ዘርፉ ላይ ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ
ኮሌጁ ከአድራ ጋር በመተባበር በግሪን ኢነርጂ ዙሪያ በዘርፉ ለሚሰሩ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።
የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ኸይሩ አህመዲን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በሶላር ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ ስልጠና በመስጠት ዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን ችግር በመቅረፍ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
በተለያዩ የአለም ክፍሎች የምናያቸው የአየር ንብረት ለውጦች ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የሚያያዙና የኢነርጂ ልዩነት ያመጣቸው ናቸው ያሉት አቶ ኸይሩ፤ ግሪን ኢነርጂን በአግባቡ በመጠቀም የተስተካከለ ከባቢን መፍጠር እንችላለን ብለዋል።
የግሪን ኢነርጂን በመጠቀም ለአለም ሀገራት የተሞክሮ መቀመሪያ እየሆንን መጥተናል ያሉት ሀላፊው፤ በቀጣይም ክፍተቶቻችንን በመሙላት የበለጠ መስራት ይኖርብናል ነው ያሉት።
የወልቂጤ ግሪን ኢነርጂ ቲቪኢቲ ፕሮጀክት ማናጀር ኤፍሬም ተሰማ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ በሶላር ሀይል ላይ ለሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግና ለውጤታማነቱም ከመንግስት መዋቅሮች ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በአራት ዙር ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሰልጠን እቅድ ይዞ ወደ ተግባር መገባቱን የገለፁት አቶ ኤፍሬም፤ አሁን ለአራተኛ ዙር ስልጠና ምዝገባ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የሶላር ቴክኖሎጂዎች ከመጠቀም አንጻር ልምድ አላት ያሉት ደግሞ የአማራጭ ሃይል ባለሙያ አቶ አስመላሽ ሃይሌ፤ በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረጉ ረገድ ችግር እንዳለ ገልጸዋል።
በተለይም እንደ ሶላር ያሉ በጸሃይና ታዳሽ ሃይል የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎች ለገጠሪቱ የሃገሪቱ ክፍል ወሳኝ በመሆናቸው በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት አስፈላጊ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የሶላር ቴክኖሎጂ በመስኖ ልማትና ሌሎችም በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጨማሪ አገልግሎት የሚሰጥ ቴክኖሎጂ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎችም ዘርፉ ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረው፤ ፕሮጀክቱም የተጠናከረ ስራ እየሰራ መቆየቱን በማንሳት አሁንም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።
በግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረኩ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡ አስፍር ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን ተግባራዊ በማድረጋቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን በየኪ ወረዳ የኩቢጦ አካባቢ አርሶአደሮች ተናገሩ
በዓለም አቀፍ ደረጃ በዕውቀትና ክህሎት ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ላይ የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑ ተገለጸ
በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሽከርካሪዎች ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን የወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ካምፓስ ገለፀ