የወጣቶችን አካላዊና አዕምሮዊ ጤና ለመጠበቅ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

የወጣቶችን አካላዊና አዕምሮዊ ጤና ለመጠበቅ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ታሕሣሥ 02/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የወጣቶችን አካላዊና አዕምሮዊ ጤና ለመጠበቅ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን የአልቾ ውሪሮ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።

በወረዳው በተለያዩ ጊዜያት የውስጥ ለውስጥ የቀበሌ ውድድሮችን በማዘጋጀት ተተኪ ወጣት ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ተመላክቷል።

የአልቾ ውሪሮ ወረዳ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤ ዞን ደጋማ የአየር ፀባይና ታራራማ የመሬት አቀማመጥ ካላቸው የሀገራችን አካባቢዎች ተጠቃሽ ሲሆን አካባቢው በተለይም ለአትሌቲክስ የስፖርት ዘርፍ ምቹ አጋጣሚ በመፍጠር ሙክታር እድሪስን የመሳሰሉ አትሌቶችን ለሀገራችን የአትሌቲክስ ዘርፍ እያበረከተ ይገኛል።

ወጣቶች ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉ፣ ጤናቸውን በሚጎዱ ሱሶች እንዳይወድቁ፣ በስነ ምግባር የበለፀገ፣ አምራችና ጤናማ ትውልድ ለማፍራት ለወጣቶች የስብዕና ግንባታ ስልጠናዎችን ከመስጠት ጎን ለጎን የእግር ኳስ፣ የአትሌቲክስ፣ በእጅ ኳስና በሌሎች የስፖርት አይነቶች የበጋና የክረምት ውድድሮችን በማዘጋጀት ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን የሚናገሩት የወረዳዉ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ቶፊቅ በድሩ ናቸው።

በወረዳው የተለያዩ የስፖርት ውድድሮችን ከማዘጋጀት በተጨማሪ በከተሞችና በገጠር ቀበሌያት የስፖርት ማዘውትሪያ ስፍራዎችንና የወጣቶች ማዕከላትን የማስፋፋት ከዚህ ቀደም የነበሩትን የማደስና ምቹ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት አቶ ቶፊቅ ህብረተሰቡ ለስፖርት ልማት ትኩረት በመስጠት በትምህርት ቤቶች እንዲሁም በተለያዩ ቀበሌያት የሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን የመንከባከብና የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።

በወረዳው የሚገኘው የአልቾ ዉሪሮ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በርካታ ሕፃናትንና ታዳጊዎቹን በአትሌቲክስ የስፖርት ዘርፍ ስልጠና እየሰጠ የሚገኙ ሲሆን በወረዳው የሚገኙ የእግር ኳስ ፕሮጀክቶችም የስፖርቱ ዝንባሌ ያላቸውን ወጣቶችን በማሰልጠን የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑንም ተናግረዋል።

የዘንድሮ የ2018 ዓ.ም የአልቾ ውሪሮ ወረዳ የበጋ ወራት የቀበሌዎች የእግር ኳስ ውድድር በ29 ቀበሌያትና በ3 የጤና ቡድኖች መከከል ውድድር እየተካሄደ መሆኑን የገለፁት አቶ ቶፊቅ በውድድሩም ወረዳውን በዞናልና በክልላዊ ጨዋታዎች መወከል የሚችሉ ወጣት ስፖርተኞችን ለመመልመል እንደሚያግዝ ገልፀዋል ።

ስፖርታዊ ውድድሮች ወንድማማችነትን በማጠናከር ማህበራዊ መስተጋብርን ለማጎልበት ካላቸው ፋይዳ በተጨማሪ ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ ከመሰለፍ ተቆጥበው በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች በመሳተፍ ጤናቸውን እየጠበቁ መሆኑን የውድድሩ ተሳታፊ ወጣቶች ተናግሯል።

በሌላ በኩል ወጣቶች በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ጤናቸውን ከመጠበቅ በተጨማሪ ጊዜያቸውን ማህበረሰቡን ብሎም ሀገርን በሚጠቅሙ ተግባራት ላይ በመሳተፍ የበኩላቸው ሊወጡ እንደሚገባ የውድድሩ ተመልካቾች አሳስበዋል ።

ዘጋቢ: ሙጅብ ጁሃር – ከሆሳዕና ጣቢያችን