ሀሳብን በተግባር የለወጠ
በደረሰ አስፋው
ወጣትነቱ ለስራ ፈጠራው አግዞታል፡፡ የሰላ አእምሮውን እና ያልዛለው ጉልበቱን ከፈጠራ ሀሳቡ ጋር አዋህዶ በትንሹ የጀመረው ስራ እየተመነደገ ነው፡፡ ነገን አርቆ የሚያስብና ለዚህም የሚተጋ ትጉህ ወጣት ስራ ፈጣሪ ነው፡፡ ተማሪ እያለ ሁሉ ምኞቱ የስራ ፈጣሪ ባለቤት ሆኖ ሀብት መፍጠርን ነበር፡፡ ትናንት የነገውን ውጥን አስቦ የጀመረው ስራው ዛሬም ነገን አርቆ እንዲመለከት ዕድል ፈጥሮለታል፡፡
ለደንበኞቹ ተገቢ የሆነ መረጃ በመስጠት የገበያውን እድል ለመጠቀም ይጥራል፡፡ በጠባቧ ክፍል ውስጥ ሁለት የልብስ ማሽኖች ይታያሉ። ከውስጥና ከውጭ በተለያየ መጠን፣ ቀለምና ዲዛይን የተዘጋጁ ቦርሳዎች በአይነት በአይነት ተሰቅለዋል፡፡ እነዚህም የባለታሪካችን የእጅ ጥበብ ውጤቶች ናቸው፡፡ በርካቶችም ከውጭና ከውስጥ ሆነው ስራዎችን ይመለከታሉ፡፡ የሚገዙትም በቦርሳዎች ጥራትና ዲዛይን ደስተኛ ስለመሆናቸው ሀሳባቸውን አጋርተውኛል፡፡
ባለታሪካችን ንግድን ገና በልጅነቱ ነው የጀመረው፡፡ ቤተሰቦቹ በንግድ ስራ የሚተዳደሩ በመሆኑ እሱም ይህን ልምድ አሳድጓል፡፡ ሞባይል አክሰሰሪዎችን በመነገድ ነው ስራውን የጀመረው። ሌሎች ትናንሽ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን በመስራትም የንግድ ክህሎቱን አሳድጓል፡፡ ዛሬ ላይ የተሰማራበትን ስራ ሲጀምር ስራው ለሱ አዲስ አይደለም፡፡ እንዴት ሰርቶ ማትረፍ እንደሚቻል ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በተለይ ባለታሪካችን የገበያን ዕድል አጥንቶ መስራት ልዩ መገለጫው ነው፡፡
በባሀል አዳራሽ ክፍለ ከተማ ሳውዝ ስታር ሆቴል ፊት ለፊት የስራ ቦታው ነው፡፡ በሰዎች ፍላጎት የተማሪዎች ቦርሳ፣ የጉዞ ቦርሳ፣ የጀርባ ቦርሳዎች፣ የካሜራ ቦርሳዎች በተለያዩ ቀለማት መጠን እና አይነት በትዕዛዝ ያዘጋጃል፡፡ የሰዎችን ሀሳብ ከራሱ ፈጠራ ጋር አዋህዶ የሚሰራቸው ቦርሳዎች በእርግጥም ምቹና ተወዳጅ ናቸው፡፡ ባገኘው ልምድና ዕውቀት ካለው የንግድ ልምድ ጋር አዋህዶ ውጤታማ እየሆነ እንደሚገኝ ነው የተናገረው፡፡
“ወደ ስራ ለመግባት የምንጠብቀው አካል ሊኖር አይገባም፡፡ ከቤተሰብ፣ ከመንግስት እንዲሁም ከማህበረሰቡ የምንጠብቀው ነገር ውጥናችንን ሊያደናቅፍ አይገባም፡፡ እኔ መስራት ስፈልግ እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች ከማንኛውም አካል ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ቦታ፣ ገንዘብ፣ ግብአት አለፍ ሲልም የዋጋ መዋዠቅ ፈታኝ ነገሮች ነበሩ፡፡ ልሰራ ስነሳ ምቾት የሚነሳ ነገር ነበር፡፡ እነዚህን ጎታች ነገሮች አስቤ መቀመጥን ምርጫዬ አላደረኩም፣ ባለኝ አቅምና ዕውቀት ስራ ጀመርኩ። ብር ብቻ ውጤታማ እንደማያደርገኝም አስብ ነበር፡፡
“ወደ ስራው ከመግባቴ በፊት የስፌት ክህሎት አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን ንግድን አውቃለሁ። በንግድ ከልጅነት እስከ እውቀት ያካበትኩት ልምድ አለኝ፡፡ ትልቅ ቦታ ለመድረስ ህልም ግን ነበረኝ፡፡ እንዲሁም ንግድ ጥረት፣ ትጋት እና ጊዜን በተገቢው መጠቅምን ይሻል” ሲል ነው ሀሳቡን የጀመረው፡፡
ወጣት ሀብታሙ አወቀ ይባላል፡፡ “MH Line 126” ቦርሳ አምራችና አከፋፋይ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ነው፡፡ የተወለደው ኦሮሚያ ክልል ቢሆንም እድገቱ ግን ሀዋሳ ከተማ ነው፡፡ ፊደል ቆጥሮ ከአንደኛ ደረጃ እስከ 2ኛ ደረጃ የተማረው ሀዋሳ ከተማ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ትቅደም 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተምሯል፡፡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ነው የተማረው። ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በኤሌክትሮ መካኒካል የትምህርት ዘርፍ ለ3 ዓመታት ተከታትሎ በሌብል 4 ተመርቋል። በተመረቀበት የትምህርት መስክ ግን እየሰራ አይደለም፡፡
ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ በተለያዩ የንግድ ስራዎችን ያሳለፈው ወጣቱ ስራ ፈጣሪ ሀብታሙ ከትምህርቱ ጎን ለጎን በተለያዩ የንግድ ስራዎች ተሰማርቶ ሰርቷል፡፡ በግልና በቡድን ያለፈባቸው ትናንሽ የሚመስሉ ነገር ግን ሀብታሙ ልምድ የቀሰመባቸው የንግድ ስራዎቹ ናቸው፡፡ ይህ የንግድ ስራ ሚዛኑን ደፋና ከነጋዴ ቤተሰቦቹ የቀሰመውን ተሞክሮ አዋህዶ ወደ ስራ ተሰማራ፡፡ በተለይ ከታላቅ ወንድሙ ጋር የሰራው የንግድ ስራ ትልቅ ልምድ የቀሰመበት እንደነበር በማስታወስ፡፡
ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በግሉ ንግድን መስራት ጀመረ፡፡ የጀመረው የሞባይል አክሰሰሪዎችን በመሸጥ ነበር፡፡ የአልባሳት ንግድንም ሞክሯል። በየጊዜው ወቅታዊ የገበያ ዕድሎችን ለመጠቀምም ይሞክራል፡፡ ጊዜውን በከንቱ ከማባከን ይልቅ የተለያዩ የንግድ አማራጮችን በመመልከት ህይወቱን ለመለወጥ ምንጊዜም አይታክትም፡፡ የወጣትነት ዕድሜውን በከንቱ ከማሳለፍ ይልቅ ሊጠቀምበት ነው የሚሻው፡፡
የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሲከታተል እንኳ ጎን ለጎን ከንግዱ አልተለየም፡፡ ማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ አላማ ይጠቀምበታል፡፡ ቲክቶክ፣ ፌስቡክ የሱ መረጃ ምንጮቹ እንጂ የፌዝ መተግበሪያዎች ወይም መቀለጃዎች አልነበሩም፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው ሀብት፣ እውቀትና ክህሎትን ለመጨበጥ ይጠቀምበት እንደነበር ነው የተናገረው፡፡
የኤሌክትሮ መካኒካል ሙያ አብዛኛው ማሽን ላይ የሚሰራ ነው፡፡ በሙያው በሀዋሳ ከተማ ባሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተቀጥሮ ለመስራትም ተመኝቶ ነበር፡፡ ብዙዎች ልምድን የሚጠይቁ በመሆናቸው ብዙ አላራመዱትም። በዜሮ አመት ልምድ ተቀጥሮ የሚከፈለው ደግሞ ኑሮውን እንደማያሻሽለው ተገነዘበ። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ወደ ስራ ፈጠራው እንዲያዘነብል አደረገው፡፡
እጁ ላይ ባለው ገንዘብና ግብአት ወደ ንግዱ ገባ፡፡ ከእለት ዕለት አዳዲስ ሀሳቦችን እያመነጨ በሚሰራው የንግድ ስራም ከጊዜ ወደ ጊዜ የንግድ ልምዱን እያዳበረና ውጤታማ እየሆነ ይሄድ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ አሁን ላይ እየሰራ ያለው ቦርሳ ማምረት ነው፡፡ ወደዚህ ስራ ከመሰማራቱ በፊት የገበያ ጥናት ማድረጉን ነው የተናገረው። የገበያ አማራጩ ሰፊ እንደሆነም አረጋገጠ፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ የአጭር ጊዜ ስልጠና ሀዋሳ ከተማ ሳሮን ዲዛይንና ፋሽን ማሰልጠኛ ተቋም የ3 ወር ስልጠና ወስዷል፡፡
ከስልጠናው ማግስትም የራሱን ፈጠራ በመጨመር በሚሰራቸው የቦርሳ ስራዎች ተመራጭ ሆነ፡፡ የገበያ ዕድል ያለበት እንደሆነ ስለመገንዘቡም ነው የተናገረው፡፡ የተማሪዎች ቦርሳ፣ የላፕቶፕ ቦርሳ፣ የተለያዩ መጠንና ቅርጽ ያላቸው የጉዞ ቦርሳዎችን ትዕዛዝ በመቀበል ያመርታል፡፡
ወደ ስራው ሲገባ መነሻ ካፒታል አልነበረውም ሀሳብ እንጂ፡፡ በየሰፈሩ ትናንሽ የንግድ ስራዎችን ሲሰራ የሚያገኛትን ውስን ገንዘብ የመቆጠብ ልምድን አዳብሯል፡፡ ሌላው ገንዘቡን በንብረት ላይ በማዋልም የገንዘብን ብክነት ይታደግ ነበር። እነዚህ ጠቃሚ የንግድ ክህሎቶችን መከተሉ የንግድ ስራውን ለማሳለጥ እንዳገዘው ነው የጠቆመው፡፡
ሌላው ወደ ንግድ ከመሰማራት በፊት የገበያ አማራጩን አጥንቶ መግባት አዋጭ ነው ይላል። የገበያ መቀዛቀዝ ሲፈጠርም ወደ ሌላ የገበያ አማራጮች መዞር ብልጠት ነው ባይ ነው፡፡ የተዘጋጁ አልባሳትን መስራት አቁሞ ወደ ቦርሳ ስራው ሲገባም ገበያውን መሰረት በማድረግ እንደሆነ ነው የገለጸው፡፡
ወደ ቦርሳ ማምረት ሲገባ በእጁ የነበሩትን የሞባይል አክሰሰሪዎች በመሸጥ አንድ የልብስ ማሽን ገዛ፡፡ ጥሬ እቃ ለመግዛትም ሌላ ተጨማሪ ገንዘብ አላስፈለገውም፡፡ በእጁ የነበሩትን፣ ካኪ ጨርቆችን፣ ሸሚዞችንና ጂንስ ሱሪዎችን በግብአትነት በመለወጥ ባማረ ዲዛይን ወደ ቦርሳ ቀየራቸው፡፡ በዚህም የበርካታ ደንበኞችን ቀልብ መማረክ ቻለ፡፡ እራሱን ያስተዋወቀበት ስራ ሆነ፡፡ አዲስ ሀሳብና አሰራር ስለነበር ገበያውን ከመጠቀም ባሻገር በሰዎች ዘንድም አድናቆት አገኘበት፡፡
አሁን ደግሞ አቅሙ ሲያድግ ከቀድሞው በተለየ አዳዲስ ጥሬ ዕቃዎችን በማቅረብ ነው የሚሰራው፡፡ እራሱ ፈጥሮ በጀመረው የፈጠራ ስራም ለስራው የሚያስፈልጉ የቦርሳ ጨርቆችን በመግዛት በሚሰራቸው ምርቶቹ ጥሩ ገቢ እያገኘበት እንደሆነም ገልጾልናል፡፡ ወደ ስራው ከገባም አንድ አመት ማሳለፉን ገልጾ በዚህ ስራም ውጤታማ እየሆነ ነው፡፡ በሚሰራበት ቦታ ሰዎች እየተመለከቱ በሚሰጡት ዲዛይን ይሰራል፡፡ ምርቶቹንም ማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም የገበያው ማስታወቂያ ያደርጋል፡፡
በቲክቶክ አካውንቱ እና በቴሌግራም ግሩፖቹም ምርቶቹን በማስተዋወቅ የገበያውን አማራጭ አስፍቷል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የምርቶቹ ተጠቃሚዎች የፈጠሩለት ገበያ የላቀውን ስፍራ እንደሚይዝ ነው የተናገረው። ወጣት ሀብታሙ ዛሬ ላይ ከራሱ ባለፈ ለሌሎችም የስራ እድል በመፍጠር አድማሱን እያሰፋ መጥቷል፡፡ ባለቤቱ፣ እህቶቹ የዚሁ የስራ ዕድል ተጠቃሚ ሲሆኑ ሌሎች 2 ሰዎችንም በመቅጠር የስራ ባለቤት እንዲሆኑ ማድረጉን ተናግሯል፡፡
ወጣት ሀብታሙ ለቦርሳ መስሪያነት የሚያገለግሎ ጥሬ እቃዎችን የሚያመጣው ከሀዋሳ እና አዲስ አበባ ነው፡፡ እንደ ደንበኛው ፍላጎት በተለያዩ ጨርቆች በተለያየ ዲዛይንና መጠን ቦርሳዎችን ያመርታል፡፡ ለተለያዩ ተቋማት ለስራ የሚያገለግሉ ቦርሳዎችን እንዲሁ በአይነትና በመጠን ያመርታል፡፡
ወጣቱ ስራ ፈጣሪ ሀብታሙ ስራውን ሲጀምር የማንንም እጅ ለመጠበቅ ተመኝቶ አያውቅም፡፡ ወጣትነትና የዘመኑ ቴክኖሎጂም በሱ ላይ ተጽእኖውን እንዲሳርፍበት አለፈቀደም፡፡ ይልቁንም ይህን ቴክኖሎጂ ለበጎ ዓላማ በመጠቀም ውጤታማ እንደሆነበት ነው የገለጸልን፡፡
“የወጣትነት ዘመናችን በተገቢው ካልተጠቀምን የምናጣው በርካታ ነገር ነው። እራስን ማወቅ፤ እኔ ማነኝ? በማለት በእጅ የሚገኝ ዕድልን መጠቀም ይገባል። ሌላ አካልን መጠበቅ ቆሞ እንደመቅረት ነው የሚቆጠረው፡፡ በስራ ለመለወጥ የግድ ከትልቅ ነገር መነሳትን አይጠይቅም፤ ከትንሽ በመጀመር ማደግ ይቻላል፡፡ የአጭር ኮርስ ወስዶ ወደ ስራ ለመግባት ቢታሰብ አማራጩ አለ፡፡ አብዛኛው ወጣት ዛሬ ላይ የስማርት ስልክ ተጠቃሚ በመሆኑ ይህን የመረጃ ምንጭ በበጎ ጎን መጠቀም አለብን፡፡ ጊዜን ወደ ገንዘብ መለወጥ በሚቻልበት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል፡፡ እኔ ለስራዬ የሚያስፈልገኝን መረጃ የማገኘው ከስልኬ ነው፡፡ ከሀገር እስከ ውጪ ድረስ ያሉ አማራጮችን በሚገባ እከታተላለሁ፡፡ ቲክቶክ በማየት የምናወጣውን ገንዘብ ለበጎ ዓላማ ተጠቅመን ወደ ስራ ብንለውጠው ሀብት ነው፤ ተጠቃሚዎች እንሆናለን፡፡ በዚህ አሰራር ወደ ስራው ገብቼ ዛሬ ላይ ለሌሎችም የስራ ዕድል መፍጠር ቻልኩ፡፡ ዝግጁነት ግን ከራስ መጀመር አለበት፡፡ በትንሽ እውቀትና ገንዘብ ተነስተን ነጋችንን ማሳመር እንችላለን” ሲል ነው አስተያየቱን የሰጠው፡፡
ዛሬ ላይ ወጣት ሀብታሙ ትዳር መስርቶ ልጆችንም አፍርቷል፡፡ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው በዚሁ ስራ ነው፡፡ ነገም የተሻለ የስራ አካባቢን በመፍጠር ለሌሎች የስራ እድል የመፍጠር ውጥን አለው፡፡ ለዚህም ስራውን ወደ ትልቅ ፋብሪካ የመለወጥ ዕቅድ እንዳለውም ነው የተናገረው፡፡ ብዙ ስራ የሌላቸው ሰዎች እንዳሉ እገነዘባለሁ ያለው ወጣት ሀብታሙ በሚፈጥረው የስራ ዕድልም እውቀታቸውን ተጠቅመው እራሳቸውን፣ ሀገራቸውን ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉበትን መንገድ ለመፍጠር ይመኛል፡፡
“ስጀምርና አሁን ያለሁበት ደረጃ ብዙ ልዩነት አለው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው ልምድም ነገም ወደ ትልቅ ፋብሪካ ቢያድግ መስራት የሚያስችል እውቀትን አግኝቻለሁ። ከንብረትም አኳያ ቢሆን ከአንድ ወደ ሁለት ማሽኖች አሳድጊያለሁ፡፡ ገበያው ውስጥ መቆየት ችያለሁ፡፡ ወደ ፊት የገበያውን አድማስም ከሀዋሳ ባሻገር ወደ ሌሎች አጎራባች አካባቢዎች የማስፋት ዕቅድ አለኝ” ሲል ነው የወደፊት ዕቅዱን የተረከልን፡፡
More Stories
“ጥጃን በጆሮው የምትጎትተው ቀንድ ከማብቀሉ በፊት ነው” – የሀገር ሽማግሌ አቶ ሁዱጋ ሰዲቃ
ኦሾአላ ÷ ከእግር ኳስ ተጫዋችም፣ ባሻገር
“የማዕከሉ ዋና ዓላማ ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ ድጋፍ ማድረግ ነው” – ወ/ሮ ሮማን ሰለሞን