“የማዕከሉ ዋና ዓላማ ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ ድጋፍ ማድረግ ነው” – ወ/ሮ ሮማን ሰለሞን
በገነት ደጉ
የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን ወ/ሮ ሮማን ሰለሞን ይባላሉ፡፡ የአርባ ምንጭ ተሀድሶ ማዕከል ምክትል ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በተቋሙ በተለያዩ ዘርፎች ከ24 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ ማዕከሉ ስለሚሰጣቸው አገልግሎቶች፣ ከአቻ ተቋማት ጋር ስላለው ትስስር እና ተያያዥ ጉዳች ዙሪያ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ንጋት፡– በቅድሚያ ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ በጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ወ/ሮ ሮማን፡– እኔም እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፡– ለመነሻ እንዲሆነን ከትውልድ እና እድገትዎ ብንጀምር?
ወ/ሮ ሮማን፡– ትውልድና እድገቴ በጋርዱላ ዞን ጊዶሌ ከተማ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ጊዶሌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 8ኛ ከፍል የተከታተልኩ ሲሆን ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ጊዶሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው ተምሬ ያጠናቀኩት፡፡
ትምህርቴን እንዳጠናቀኩ የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችን ከወሰድኩ በኋላ ከቅድስተ-ማሪያም ኮሌጅ በሠው ኃይል አስተዳደር/ሂውማን ሪሶርስ ማኔጅመንት/ በዲፕሎማ ተመርቄያለሁ፡፡ በመቀጠልም በማኔጅመንት የመጀመሪያ ድግሪዬን ተከታትዬ ተመርቄያለሁ፡፡
ንጋት፡– ሥራ እንዴት እንደጀመሩ ቢያስታውሱን?
ወ/ሮ ሮማን፡– አርባምንጭ አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል ሥራ ሲጀምር ወደ እኛ አካባቢ በመምጣት (ጋርዱላ ዞን በዚያን ወቅት ደራሼ ልዩ ወረዳ ይባል ነበር) በየቤቱ ተደብቀው የነበሩ አካል ጉዳተኞችን በተለይም ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑትን በመለየት ስልጠና በመሥጠት ነው የጀመርኩት፡፡ ከዚያም ከአምሰት ዓመት በኋላ ወደተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በመግባት ከሶሻል ወርከር ባለሙያነት አሁን እስካለሁበት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ደርሻለሁ፡፡ ለሰባት ወራት ያህልም ተወካይ ስራ አስኪያጅ ሆኜም ሰርቻለሁ፡፡
በአጠቃላይ ከ24 ዓመታት በላይ ከአካል ጉዳተኞች ጋር በተያያዘ በአርባምንጭ ተሃድሶ ማዕከል በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡
ንጋት፡– የአካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል ከተቋቋመ ምን ያህል ጊዜ ነው?
ወ/ሮ ሮማን፡– ተቋሙ ከተመሰረተ 29 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ ሃገር በቀል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት (ሎካል ኤንጂኦ) ሆኖ ነበር ሲሰራ የቆየው፡፡ ምንም እንኳን ተጠሪነቱ በወቅቱ ለነበረው የደቡብ ብሔር ብሄረሰቦች ክልል ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሆንም ለጋሾችን በማፈላለግ በሚያገኘው ገንዘብ ነበር የሚሰራው፡፡
የክልሉ ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ማህበራዊ ድጋፍ ያደርግ ስለነበር ከጥር 2005 ዓ.ም ጀምሮ በባለቤትነት ወስዶት ወደ መንግስት ተቋምነት ዞረ፡፡ ይሁን እንጂ አስተዳደር ሰራተኞችና የአካል ድጋፍ ሰጪ ስራዎች ሁሉ በመንግስት በጀት ቢንቀሳቀሱም ቀሪ ስራዎች ‹ላት ፎር ዶነር› በተባለ ግብረሰናይ ድርጅት ፕሮጀክት ነው ይንቀሳቀስ የነበረው፡፡
አሁን ላይ ተጠሪነቱ ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ስራውን እየሰራ ይገኛል፡፡
ንጋት፡– የአካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል ዋና ተልዕኮና ተግባሩ ምንድን ነው?
ወ/ሮ ሮማን፡– የተቋሙ ዋናው ተልዕኮና ተግባሩ አካል ጉዳተኞችን ካሉበት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ወደ ተሻለ ደረጃ የማምጣት ተግባር ነው። አካል ጉዳተኞችንና ወላጆቻቸውን በመርዳት መልሶ ማቋቋም ነው ዋናው ዓላማ፡፡
አሁን ግን አካል ጉዳተኛ ሲባል የተለያየ ጉዳት ነው ያለው፡፡ ይህም የተለያዩ ጉዳት ያለባቸውን አካል ጉዳተኞች በሁለት መልኩ ነው አግልግሎቱን እየሰጠን ያለነው፡፡ ለዓብነትም በዋናው መስሪያ ቤት የሚተገበሩ ተግባራት እና በመሰረተ ማህበረሰብ ተሀድሶ ፕሮግራም የሚሰሩ ስራዎችም እንዳሉ ሁሉ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ የሚሰጡ አገልግሎቶችም አሉ፡፡
በዋና መስሪያ ቤት የምንሰጣቸው አገልግሎት የአካል ድጋፍ ብቻ ነው፡፡ ይህም ማለት የሰው ሰራሽና የአካል ድጋፍ የሚመረተው እዚሁ ተቋም ነው፡፡ የአካል ጉዳት በተለያዩ ምክንያት ከተከሰተ በኋላ የእንቅስቃሴ ጉዳት ያለባቸው ወደ ተቋሙ በመምጣት ቢበዛ እስከ 12 ቀናት ጉዳያቸውን ጨርሰው አርትፊሻል ለሚፈልጉ ተሰርቶላቸው ወደመጡበት ይሸኛሉ፡፡
አሁን ላይ ተቋሙ ዊልቸር፣ ክራንች፣ ኤልቦ ክራንች በማምረት አገልግሎቱ የሚሰጥ ሲሆን በተጨማሪም የፊዚዮቴራፒ አግልግሎት በተለያየ ምክንያት በአካላቸው ላይ የእንቅስቃሴ ችግር ያለባቸው ኤሌክትሮ ቴራፒ፣ የማሳጅ አገልግሎት ስራዎች ይሰራሉ፡፡
ከዚህም ባሻገር የዞረ እግር ችግር ላለባቸው ህፃናት ዕድሜቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑት የእግር ማቃናት ስራ በተሃድሶ ማዕከሉ ይሰራል። በሌላ መልኩ የመሰረተ ማህበረሰብ ተሀድሶ ባለሙያ ቤት ለቤት በመሄድ የተደበቁ አካል ጉዳተኞች ካሉ በማፈላለግ የተለያዩ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡
በዚህም የተለያየ የአካል ጉዳት ያለባቸው ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን እንደ ጉዳታቸው ዓይነትና መጠን ሶሻል ወርከሮች ዕቅድ በማውጣት ቤት ለቤት በመሄድ በሳምንት ሁለት ጊዜ ለአንድ ሰዓት የሚቆይ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ይህም ለአካል ጉዳተኛው ብቻ ሳይሆን ለቤተሰብ ጭምር ነገ ላይ ትምህርት ቤት ሲገባ እንዳይቸገር በማስተማር ያሰለጥናሉ፡፡
ንጋት፡– ከአቻ ተቋማት ጋር በትስስር የሚሰራቸው ተግባራት ምን ምንድን ናቸው?
ወ/ሮ ሮማን፡– የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ የአንድ ተሀድሶ ማእከል ጉዳይ ብቻ አይደለም። እንደዛ ከታሰበ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው የሚሆነው፡፡ ችግሩ የማህበረሰብ ችግር በመሆኑ ቅንጅታዊ ስራ ይፈልጋል፡፡
ተቋሙ ከሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ጋር በቅንጅት ነው የሚሰራው፡፡ ቢሮው የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ በጋራ የምንሰራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ሌላው ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር ከ25 ዓመታት በላይ ለዚህ ተቋም ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ አለም አቀፍ ቀይ መስቀል ለዚህ ተቋም ድጋፍ ባያደርግ ኖሮ ይህ ተቋም በሁለት እግሩ አይቆምም ነበር፡፡
ማህበሩ ሰው ሰራሽ አካል የሚመረትበት ቦታ ላይ ቀጥታ አርቲፊሻሉ እግር የሚሰራበትን ጥሬ ዕቃ እነሱ ባያቀርቡት ኖሮ እግራቸው በተለያየ ምክንያት ተጎድቶ ለሚመጡ ዜጎች የአርትፊሻል እግርና እጅ መስራት አንችልም ነበር፡፡ ምክንያቱም እነሱ የሚያቀርቡት ጥሬ ዕቃ በቀላሉ ሀገር ውስጥ አይገኝም፡፡ እነዚህ አካላት ነገ ላይ በቃ ብለው ቢወጡ ምንድን ነው ዕጣ ፈንታችን የሚሆነው የሚለው ያሳስባል፡፡ ለዚህም ከክልል እስከ ፌዴራል ጤና ሚኒስተር በቅንጅት ለመስራት መዘጋጀት አለባቸው፡፡
ሌላው ኦፕ ኦክስ ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በተለይም “ክለብ ፉት” (ቆልማማ/የዞረ እግር) በተለምዶ ተብሎ ህፃናት ከእናታቸው ማህፀን ሲወለዱ ጀምሮ የሚያጋጥም ችግር በፊዚዮቴራፒ ማስተካከል ስራዎችን እየሰሩ ነው፡፡
ሌላው ከአርባ ምንጭ ሆስፒታል ጋር በጋራ ለመሥራት ተፈራርመናል፡፡ በአንድም በሌላ መልኩ የሚሰራው የጤና ስራ በመሆኑ የዞረ እግር በየ15 ቀኑ በመስራትና የቀዶ ጥገና/ሰርጀሪ በማድረግ ምንም ዓይነት ክፍያ ሳይከፈላቸው ዶክተሮች እየመጡ ያግዛሉ፡፡ ለዚህም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ሳላመሰግን አላልፍም፡፡
ከጬንቻ ሆስፒታልም ጋር የግብ ስምምነት ተፈራርመናል፡፡ የፊዚዮቴራፒ ባለሙያ ለአንድ ወር ስልጠና በመስጠት ሲያግዙን ነበር፡፡ ከሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታልም ጋር አመርቂ የሆኑ ስራዎችን እየሰራ ነበር፡፡ አሁን ላይ እንቀጥላለን መሀል ላይ የተወሰነ ክፍተት ተፈጥሮ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ላይ አይፖስ ከተባለ መንግስታዊ ድርጅት ጋር በርካታ ስራዎችን ሰርተናል፡፡
ሌላው ከታችኛው ከዞን ጀምሮ ከሴቶችና ህፃናት፣ የከተማ ማህበራዊ ጉዳይ፣ ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት፣ ከወርልደ ቪዥን ኢትዮጵያ ጋር በመሆን በጋራ እየተሰራ ነው፡፡
በዚህም ከ60 እስከ 70 ሺህ ብር ሊፈጅ የሚችለውን አገልግሎት በነፃ እየሰጠን ነው። ከየትኛውም ኢትዮጵያ ጫፍ ይምጣ አገልግሎታችን በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በመሆኑ የደሃ ደሃ መሆኑን አስመስክሮ ከመጣ አግልግሎቱ ነፃ እንሰጣለን፡፡
ንጋት፡– ከታችኛው መዋቅር ጋር ያለው ትስስርስ ምን ይመስላል?
ወ/ሮ ሮማን፡– አርባ ምንጭ ተሃድሶ ማዕከል ላይ አራት ዋና ዋና የስራ ክፍሎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው አካል ጉዳትና ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ፣ ፊዚዮ ቴራፒ፣ ማህበረሰቡን መሰረት ያደረገ የተሀድሶ አገልግሎት እንዲሁም የሥነ-ልቦና/ሳይኮሎጂ/ የትምህርት ከፍል አገልግሎት በያዝነው ዓመት አስፈቅደን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የፐብሊክ ሰርቢስ ቢሮ በሰጠው ትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
የሳይኮሎጂ ዲፓርትመንት ከተቋሙ ጋር አብሮ መቋቋም ያለበት ሲሆን በተለይም በሰው ሰራሽ አደጋ ለአካል ጉዳት የተዳረጉ የህበረተሰብ ክፍሎች አምኖ ከመቀበል አንፃር ስለሚቸገሩ የስነ-ልቦና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡
አሁን ላይ ከተለያዩ ዞኖችና አጎራባች ክልሎች የሚመጡ አካል ጉዳተኞች የመጀመሪያው የስነ-ልቦና ድጋፍ በአግባቡ ከተሰጣቸው በኋላ ነው ወደ አካል ድጋፍ የሚሄዱት፡፡
የማዕከሉ ዋና ዓላማ በአርቲፊሻሉ ድጋፍ ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ እንጂ መለመኛ እንዲያደርጉ ሳይሆን ከተረጂነት ወጥተው እንዲነግዱ እና እራሳቸው ስራ ፈጥረው ቤተሰብ መስርተው ሀገርን እንዲረዱ ነው፡፡ ይህንንም እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን።
ንጋት፡– ህብረተሰቡ ስለ አካል ጉዳተኞች የተሳሳተ አመለካከት እንዳይኖር ምን እየተሰራ ነው?
ወ/ሮ ሮማን፡– በተለይም በሶሻል ወርከሮች አማካይነት በየትምህርት ቤቶች ስለ አካል ጉዳተኞች መማር፣ የጤና አገልግሎት እንዲሁም የህብረተሰቡ አንድ አካል ስለመሆናቸው በ15 ቀን ሁለት ጊዜ እርስ በእርስ የመማማር መድረክ በቋሚነት ተዘጋጅቷል፡፡
ተማሪዎችም አካል ጉዳተኞችን እንዲያገለግሉ ከመምህራን ጋር በመሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ይካሄዳሉ፡፡ በተለይም ትምህርት ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች በሚመች ሁኔታ ነው የተገነቡት የሚለውን ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ስራዎች በቅንጅት ይሰራሉ፡፡ ያም ማለት ሙሉ ለሙሉ ክፍተቶች የሉም ማለት ግን አይደለም፡፡
ንጋት፡– አገልግሎቱን ከዚህም በተሻለ በጥራት ተደራሽ ለማድረግ ምን መሰራት አለበት ይላሉ?
ወ/ሮ ሮማን፡– የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ የአንድ ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ወይም የተሃድሶ ማዕከል ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የሁሉም አካል ርብርብን እና ቅንጅታዊ ስራን ይፈልጋል፡፡
ማንኛውም የመንግስት አካል በጀት ሲይዝ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ዕቅዶች መታቀድ እንዳለባቸው መታሰብ አለበት የሚል እሳቤ አለኝ።
በስራ ቅጥር እና ምደባ ላይ የሚሰጣቸው ልዩ ትኩረት ምንድ ነው? አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም ስንል የማይመች ቦታ ላይ መላክ በችግሩ ላይ ሌላ ችግር መፍጠር ነው፡፡
በቢሮ ደረጃ ሲመደቡ እንኳን ተመደበው ለሚመጡ አከል ጉዳተኞች አመቺ ነው ወይ? ለአብነትም የአርባምንጭ ተሃድሶ ማዕከል ቅጥር ጊቢ ለማንኛውም ዓይነስውርም ሆነ ለአካል ጉዳተኛ ሙሉ ለሙሉ ምቹ ነው፡፡ በማዕከሉ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ደረጃ የሚባል የለውም፡፡
ለዚህም አዋጅ ቁጥር 6/24 ማንኛውም ህንፃ ሲገነባ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሆን አለበት ይላል፡፡ ከዚህ በፊት ካለው የተሻሉ ነገሮች አሉ ግን አሁንም ያልተቀረፉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ አሁንም ቢሆንም ብዙ ተቋማት ታሳቢ አድርገው የተሰሩት ጉዳት አልባውን ነው፡፡
ንጋት፡– በዘርፉ እንደ ችግር በዋናነት የሚነሳው ምንድን ነው?
ወ/ሮ ሮማን፡– በተቋማችን በተለያዩ የሙያ መስኮች ማስታወቂያ ሲወጣ የማዕከሉ ቅጥር ጊቢ ይጨናነቃል፤ ነገር ግን በሌሎች የሥራ ዘርፎች ለምሳሌ ኦርቶፔዲክ ሲወጣ ግን ምንም የተማረ የሰው ሀይል አይገኝም፡፡
አንድ ወቅት የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር በጋራ በመሆን ያሰለጠናቸው እና በዲፕሎማ ደረጃ እራሳቸውን ያበቁ ቢኖሩም በድግሪ ደረጃ ግን ምንም የተማረ ሀይል ማግኘት አልተቻለም፡፡ ይህ በመሆኑ በማዕከሉ ያሉት ባለሙያዎች ሁለት ብቻ በመሆናቸው አገልግሎቱን በሚፈለገው ያህል ለመስጠት እንቸገራለን፡፡
አሁን ላይ ከሚመጡ ተገልጋዮችአብዛኛው የእንቅስቃሴ ጉዳት ያለባቸው ቁጥሩ ከፍተኛ ነው፡፡ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ እግሩ ወይም እጅ ከተቆረጠ ከስድስት ወራት በኋላ ነው የእንቅስቃሴ ድጋፍ ማግኘት የሚችለው፡፡ ካለን የሰው ሀይል አንፃር ሁለት የኦርቶፔዲክ ቴክኒሺያልን እና እረዳቶች ናቸው፡፡ ይህም አገልግሎቱን አዝጋሚ ያደርገዋል፡፡ ፊዚዮቴራፒም አራት ባለሙያ ብቻ ነው፡፡ ይህም በቂ አይደለም፡፡ እነዚህን የሰው ይል ለማሟላት በጤና ሚኒስቴር ደረጃም በእቅድ ተይዟል፡፡ በቀጣይም ስርዓተ ትምህርት ተቀርፆለት ችግሩ እንዲፈታ ቢደረግ መልካም ነው፡፡
ያሉትም ባለሙያዎች ከጥቅማጥቅም አንፃር ለቀውም ይሄዳሉ፡፡ ይህም ችግር ቶሎ ካልተፈታ ያሰብነውን ስራ ተደራሽ እንዳናደርግ እንቅፋት ይሆናል፡፡ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበርም ጫማ፣ የምግብና የጥሬ ዕቃ ያቀርብ የነበረው በያዝነው ዓመት ጥሬ ዕቃ ብቻ እየሰጠን ሌሎችን ድጋፍ ማድረጉን አቋርጧል፡፡ ነገ ላይ በተመሳሳይ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ቢቋርጥ ሊገጥመን የሚችለው ችግር ከባድ በመሆኑ የሚመለከተው የመንግስት አካል በሀገር ውስጥም ሊሟላ የሚችልበትን የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ቢመቻች መልካም ነው፡፡
ንጋት፡– የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
ወ/ሮ ሮማን፡– አካል ጉዳት ሰዎች ወደውና ፈቅደው የሚያመጡት አይደለም፡፡ ለምሳሌ በበሽታ፣ በሰው ሰራሽ አደጋ እና በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፡፡ ከተከሰተ በኋላ ይህንን ለመገልገል ወደሚሄዱበት የመንግስት ተቋማት ከመግቢያ በር ጀምሮ አካባቢውን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የማድረግ ስራዎች ቢሰሩ መልካም ነው፡፡
በሌላ መልኩ የእኛ ማህበረሰብ አብዛኛውን ጊዜ የአካል ጉዳት መንስኤው እርግማን፣ ከእግዚአብሔር የመጣ ቁጣ፣ ከልክፍት እንዲሁም እናትና አባቱ የሰሩት ሀጢያት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው የሚል የተሳሳተ አመለካከት ይስተዋላል። በዚህም ምክንያት የማግለል ሁኔታዎች ዛሬም አሉ፡፡ እነዚህንም ለመከላከል ማህበረሰቡን ለማስተማር ሁሉም በእኔነት ስሜት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል የሚል መልዕክት ነው ያለኝ፡፡
More Stories
“በመምህርነቴ የሚሰማኝ እርካታ ከፍተኛ ነው” – መምህር ቆስቲ ስማ
“አካል ጉዳተኝነት ህይወትን በሌላ መልኩ መኖር መቻል ነው” – ወጣት ታምራት አማረ
ትንሽ ዕድሜ፤ ትልቅ ዓላማ