እድሚያቸው ከ40 አመት በላይ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የአንጀት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአንጀት ካንሰርን ለመከላከል እድሚያቸው ከ40 አመት በላይ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የአንጀት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት ሃኪም ዶክተር ሃምዛ አህመድ ገለጹ።
በአለማችን በገዳይነቱ በ3ተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የአንጀት ካንሰር ምልክቶች ከታዩ ፈጠን ብሎ ሐኪምን ማማከር በሽታውን ለመቆጣጠር ወሳኝ እንደሆነም ተመላክቷል።
ከወልቂጤ ኤፍ ኤም 89.2 ሬዲዮ ጋር ቆይታ ያደረጉት በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት ሃኪም ዶክተር ሃምዛ አህመድ፥ አንጀት በምግብ መፍጫ ሥርዓት ውስጥ ወሳኝ ሚና በመጫወት ለሰው ልጅ ጤና አስፈላጊ እና ጠቃሚ የሆኑ በርካታ ተግባራት የማከናወን ኃላፊነት ያለው የሰውነታችን አካል ክፍል መሆኑን ገልጸዋል።
ካንሠር ሰውነታችን የማይቆጣጠራቸው ጤነኛ ያልሆኑ ወይም ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ህዋሳት እድገት እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ሃምዛ፥ ይህም ካንሠር በሁሉም የሰውነት ክፍሎች ላይ ሊከሰት ይችላል ብለዋል።
የአንጀት ካንሰር አብዛኛውን ጊዜ ከትልቁ አንጀት የውስጠኛው ክፍል የሚነሱ ህዋሳት ከቁጥጥር ውጭ ሲራቡ የሚፈጠር አንደሆነም ጠቁመዋል።
ሲጋራ ማጤስ፣ የአልኮል መጠጦችን አብዝቶ መውሰድ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት እንዲሁም የላሙ እና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ የአንጀት ካንሰር ህመም መንስኤዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በቤተሰብ ምክንያት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ሌሎችም የህመሙ አጋላጭ ሁኔታዎች መሆናቸው ነው ዶክተር ሃምዛ ያነሱት።
የአንጀት ካንሰር ህመም ምልክቱ ሳይታይ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆይ የሚችል ሲሆን በሽታው የመጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርስ ግን የሰገራ መዛባት፣ ሰገራ ላይ ደም መኖር፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ የአንጀት መነፋት፣ ከብደት መቀነስ፣ ማስማጥ፣ ከእንብርት በታች ቁርጠት፣ የሆድ ማበጥ፣ ተቅማጥ የህመሙ ምልክቶች ናቸው።
በአለማችን በገዳይነቱ በ3ተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የአንጀት ካንሰርን ለመከላከል እድሚያቸው ከ40 አመት በላይ የሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የአንጀት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በካልሺዬም እና ማግኒዥዬም ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ምግቦችን እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬን አዘውትሮ በመመገብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማድረግ የአንጀት ካንሰርን በመጠኑም ቢሆን መከላከል እንደሚቻል መክረዋል።
የአንጀት ካንሠር ምልክቶች ከታዩ ፈጠን ብሎ ሐኪምን ማማከር በሽታውን ለመቆጣጠር ወሳኝ እንደሆነ የሚጠቁሙት ዶ/ር ሃምዛ፥ ምርመራውም ቱቦ በመጠቀም ሁሉንም የአንጀት ክፍሎች በካሜራ በሚያሳይ መሣሪያ (ኮሎኖስኮፒ) በማድረግ ካንሠሩ መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በመጀመሪያው የአንጀት ካንሰር ደረጃ ላይ ምርመራ ያደረጉ ሰዎች በሽታውን በቶሎ በመለየት አስፈላጊውን ሕክምና በወቅቱ ማግኘት ስለሚችሉ የሚከሰተውን ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ የሚቻል መሆኑንም አስረድተዋል።
አጠቃላይ የህክምና አይነቶቹም የቀዶ ህክምና፣ ኬሞቴራፒ እና ራዲዮቴራፒ መሆናቸውን የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት ሃኪም ዶክተር ሃምዛ አህመድ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ አስቻለው አማረ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ዙሪያ የሚደረገው ጥንቃቄ በመቀዛቀዙ አሁንም የቫይረሱ ስርጭት እየተስተዋለ መሆኑን ተገለጸ
የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የጤናው ዘርፍ ዕቅድ አፈፃፀም እና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አደረገ
የጤና ሚኒስቴር 4.2 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የህክምና መሣሪያዎች ለክልልና ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች ድጋፍ አደረገ