የጤና ሚኒስቴር 4.2 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የህክምና መሣሪያዎች ለክልልና ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች ድጋፍ አደረገ

የጤና ሚኒስቴር 4.2 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የህክምና መሣሪያዎች ለክልልና ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች ድጋፍ አደረገ


የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ስርአትን ለማጠናከር የሚያስችል የህክምና መሣሪያዎች ድጋፍ ጤና ሚኒስቴር ለክልል እና ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች አድርጓል።


የህክምና መሣሪያዎች የህክምና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ናቸው ያሉት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ የተደረገው ድጋፍ የጤና ተቋማት የህክምና መሣሪያዎች የረጅም ጊዜ ፍላጎትን የሚያሟላ መሆኑን ገልፀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ በመቀጠልም የጤናው ዘርፍ ትልቁ ወጪ የህክምና መሣሪያዎች ግዢ መሆኑን በመግለፅ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት የህክምና መገልገያ መሳሪያዎቹን በተገቢዉ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲያዉሉ አሳስበዋል።


የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፤ አዲሱ የመድሃኒት ግዢ አዋጅ የተሻለ የህክምና መሣሪያዎች ግዢ ስርዓት እንዲፈጠር በማድረጉ አገልግሎቱ በፍጥነት የህክምና መሣሪያዎች ማቅረብ እንዲችል አድርጎታል ብለዋል።

በድጋፉም ለ48 የጤና ጣቢያዎች ሙሉ ኪት፣ ለ162 አጠቃላይ ጤና ኬላዎች ኪት፣ ለ50 መሰረታዊ ጤና ኬላዎች ግብዓት፣ ለ14 ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጫ ሙሉ መሳሪያዎች(ኪት)፣ ለ60 የፅኑ ህክምና ማዕከል ግብዓት፣ 33 ዲጂታል X-Ray መሳሪያዎች፣ 19 የላውንደሪ ማሽን፣ 117 የአይን የህክምና መሳሪያዎች እና ከ3000 በላይ የደም ግፊት መመርመሪያ መሳሪያዎች ተካተዋል።


ከጤና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የክፍፍል ስርዓቱ በፍትሀዊነት ሁሉንም አካባቢ ተጠቃሚ እንዲያደርግ የታሰበ ሲሆን ድጋፉን የክልል እና የከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊዎች ተረክበዋል።