የእናቶችንና ህጻናትን ሞት ለማስቀረት የቅድመ ማህጸን በር ካንሰርንና ከቅድመ ወሊድ እስከ ድህረ ወሊድ ያሉትን ምርመራዎች ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ
የእናቶችንና ህጻናትን ሞት ለማስቀረት የቅድመ ማህጸን በር ካንሰርንና ከቅድመ ወሊድ እስከ ድህረ ወሊድ ያሉትን ምርመራዎች በማድረግ ተገቢውን ህክምና ማግኘት ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የንግስት ኢሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ብርሃኑ ንጉሴ ገለፁ።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የንግስት ኢሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የማህጸን እና ጽንስ እስፔሻሊስት ዶክተር ብርሃኑ ንጉሴ፤ የማህጸን በር ማለት የግብረስጋ ግንኙነት የሚደረግበት ጫፍ ሳይሆን የጽንስ መቀመጫ የሆነው የማህጸን ጫፍ መሆኑን አስረድተዋል።
የማህጸን ጫፍ ካንሰር በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት እና 99 በመቶ ለዚህ በሽታ መከሰት ምክንያቶቹ ያለዕድሜ የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ፤ ዕድሜ ከደረሰ በኋላም ከተለያዩ ወንዶች ጋር የግብረስጋ ግንኙነት መፈጸም ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ ሲጋራ ማጨስም መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ዶክተር ብርሃኑ አብራርተዋል።
በመሆኑም በየደረጃው የዕድሜ ክልል የሚሰጡ ክትባቶችን በአግባቡ በመውሰድ እና የቅድመ ማህጸን ጫፍ ካንሰር ምርመራ በማድረግ በጊዜው መታከም ከተቻለ በቀላል ህክምና የሚድን በሽታ ነው የሚሉት ዶክተር ብርሃኑ፤ ከቅድመ ማህጸን ጫፍ በሽታ አልፎ ስር ከሰደደ የማይድን እና ገዳይ በሽታ ነው በማለት ዶክተር ብርሃኑ በአጽንኦት አሳስበዋል።
ከቅድመ ማህጸን ጫፍ ምርመራ እና ልጆችን ከማስከተብ በተጨማሪ ያለዕድሜ እና ዕድሜ ከደረሰ በኋላም ከተለያዩ ወንዶች ጋር የግብረስጋ ግንኙነት ከማድረግ እና ሲጋራ ከማጨስ በመቆጠብ የማህጸን ጫፍ ካንሰርን መከላከል ይገባል ሲሉ ዶክተር ብርሃኑ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ጽንስ ከመያዝ አስቀድሞ የግፊት፣ የስኳር፣ የጉበት፣ የዕጢና ሌሎች መሰል በሽታዎች ምርመራ በማድረግ እንደሚገባና ተገቢውን ህክምና ሳያገኙ መጸነስ ግን ለእናትና ህጻን ጤንነት እንዲሁም በህይወት ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል ዶክተር ብርሃኑ አክለዋል።
ከጽንስ ጀምሮ እስከ ወሊድ ወቅት ድረስ ተገቢውን የህክምና ክትትል ማድረግ ጤናማ እናት ጤናማ ልጅ እንድትወልድ ያደርጋል ብለዋል።
በተለይም እናቶች በምጥ በሚቆዩበት ወቅት በሚወለድ ህጻን እና በእናት ላይ አደጋ ስለሚደርስ በኦፕሬሽን መውለድ እንደሚበረታታ ነው ዶክተር ብርሃኑ የገለጹት።
በአሁኑ ወቅት በግልም ይሁን በመንግስት ጤና ተቋማት ዘመናዊ መሳሪያዎች ስለሚገኙ እናቶች እና ልጃገረዶች በወቅቱ የቅድመ ማህጸን በር ካንሰር ምርመራም በማድረግና ከጽንስ በፊት ምርመራ እና ከጽንስ እስከ ወሊድ ያለውን የህክምና ክትትል እንዲያደርጉ በሚዲያ በኩል ግንዛቤ በመፍጠር መንግስትና ህብረተሰቡ ተቀናጅተው በመስራት እናቶችንና ህጻናትን ከሞት እና በሽታ መታደግ አለበት በማለት ዶክተር ብርሃኑ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ: ሳሙኤል መንታሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የአርባምንጭ ደምና ህብረህዋስ ባንክ በ2017 በጀት አመት ከ6 ሺህ 378 ዩኒት በላይ ደም መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ
ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተሰራ ነው – የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
በሽታ መከላከልንና አክሞ ማዳን ላይ ትኩረት በማድረግ በድንገተኛ ክስተት ለተጎዱ ወገኖች እና ወረርሽኝ ምላሽ የሚሆን 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ግብአት ተሰራጭቷል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ