“በሥራዬ ኃላፊነቴን በአግባቡ መወጣት ያስደስተኛል” – ወ/ሮ ህይወት ዮሐንስ
በአስፋው አማረ
በሀገራችን በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ በመሳተፍ ችግሮችን በመጋፈጥ የስኬት ማማን የተቆናጠጡ በርካታ እንስቶችን መመልከት እየተለመደ ነው፡፡
የዛሬዋ እቱ መለኛ ወ/ሮ ህይወት ዮሐንስ ይባላሉ፡፡ የወላይታ ሶዶ ከተማ ሴቶችና ህጻናት ጽ/ቤት ኃላፊ ሲሆኑ የተወለዱት በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ነው፡፡
እድሜቸው ለትምህርት ሲደርስ ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል “በሊጋባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” ተከታትለዋል፡፡ ከ9ኛ እና 10ኛ ክፍል ደግሞ “ቦጋለ ዋለሎ ትምህርት ቤት” ተከታትለዋል፡፡
የ11ኛ እና 12ኛ ከፍል ትምህርታቸውን ደግሞ ሶዶ መሰናዶ መከታተል ችለዋል፡፡ ከዚያም ወደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በሶሻል ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ በሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡
በህይወት ተሞክሮቸው በትምህርት ቤት ገብቶ መማር እንደሚያስደስታቸው የገለጹት ወ/ሮ ህይወት ዮሐንስ በመደበኛ እና መደበኛ ባልሆነ የዕውቀት ዘርፎች ዕውቀታውን ለማሳደግና ለመማር ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
የሥራ ዓለምን “ሀ” ብለው የጀመሩት ደግሞ በወላይታ ሶዶ መሰናዶና ሁለተኛ ደረጀ ትምህርት ቤት የስነ ልቦና ባለሙያ በመሆን ነው፡፡ በሙያቸው ተማሪዎችን የማማከር አገልግሎት ከመስጠት ጐን ለጐን የእንግሊዘኛ ትምህርት ያስተምሩ እንደነበር አውግተውናል፡፡
በርዕስ መምህርነት እያገለገሉ ባገኙት የሥራ አፈጻጸም ተወዳድረው የተሻለ ውጤት በማስመዝገባቸው ነበር የማስተርስ (ሁለተኛ ድግሪ) ትምህርት እንዲማሩ እድሉን ያገኙት፡፡ የሥራ ዓለምን ከተቀላቀሉ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ “በኢዱኬሽን ሊደርሽፕ” ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡
ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የትምህርት ቤቶች ሱፐርቫይዘር በመሆን ህብረተሰባቸውን ማገልገል ጀመሩ፡፡ “በሥራዬ ኃላፊነቴን በአግባቡ መወጣት ያስደስተኛል” የሚሉት ወ/ሮ ህይወት በተሰማሩበት የሙያ መስክ ለውጤት እንደሚተጉም ተናግረዋል፡፡
ከፐተርቫይዘርነት በመልቀቅ መንግስታዊ ባልሆነና “ጠረቤዛ ልማት” በሚባል ሴቶች ላይ በሚሰራ ግብረ ሠናይ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ለአራት ዓመት አገልግለዋል፡፡ ይህ ድርጅት በኮቪድ ምክንያት ስራውን ሙሉ በሙሉ ሲያቋርጥ ካለ ሥራ ቤት ተቀምጠው እንደነበረ አውግተውናል፡፡
“ለልጆቼ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችን ለማሟላት ስራ መስራት ነበረብኝ፡፡ ይህን ተከትሎ ከዚህ ቀደም ሰርቼው ወደ ማላቀው የንግድ ዓለም ተቀላቀልኩ” ብለውናል፡፡
“ወቅቱ ዓለምን በሙሉ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያስገባ ወረርሽኝ የተከሰተበት በመሆኑ ፕሮጀክቱ የሚያልቅበት ጊዜና ወረርሽኙ ተገጣጠመ፡፡ ይህን ተከትሎ ሱቅ ከፈትኩኝ፡፡ ለሱቁ እቃዎችን የማመጣው ደግሞ ከአዲስ አበባ ነው፡፡ መርካቶ የሚያስፈልገኝን ገዝቼ ካስጫንኩ በኋላ በምሽት ተጉዘን ሶዶ የምንገባበት በርካታ ጊዜ ነበር” በማለት አድካሚነቱን አጫውተውናል፡፡
“በጥዋት ተነስቼ ከአዲስ አበባ የገቡ እቃዎችን ቆጥሬ ካረጋገጥኩኝ በኋላ ሱቅ ላይ የመደርደርና ማዘጋጀት ስራ እሰራለሁ፡፡ ሥራው ደግሞ በጣም አድካሚ እና አሰልቺ ነበር፡፡ ያም ሆና በሥራው በጣም ውጤታማ ነበርኩ” በማለት ስለንግዳቸው ስኬት ተናግረዋል፡፡
በንግድ ዓለም ላይ የተለያዩ እድሎችን ይሞካክሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ባለቤታቸውም በአንድ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ ይሰሩ ነበር፡፡ የሁለቱም ሥራ በተመሳሳይ ጊዜ በመቋረጡ ግን ለወ/ሮ ህይወት ቤተሰብ ከባድ ጊዜ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
“በተለይም ሱቅ ላይ በምሰራበት ወቅት በርካታ ደንበኞች ለመግዛት ሲመጡ ‘አንችን እኮ ትልቅ ደረጃ ላይ እንጠብቅሻለን፡፡ እዚህ መስራት የለብሽም’ የሚል ሀሳብቸውን ያጋሩኝ ነበር” በማለት አስተያየታቸውን ይሰጧቸው ነበር፡፡
“በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ሌላ አማራጭ ሥራ ለማግኝነት አይታሰብም ነበር፡፡ እኛም ያሉንን ሶስት ልጆች ለማሳደግ የባለቤቴ እገዛ እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ እሱ ለእኔ ምሳሌ ነው፡፡ ጠንካራ እና መንፈሳዊ ሰው መሆኑ ለእኔ ትልቅ አቅም ይሆነኝ ነበር” ሲሉ ለባለቤታቸው ያላቸውን አክብሮት ይናገራሉ፡፡
“ሁለታችንም በአንድ ትንሽ ሱቅ ውስጥ ቁጭ ብለን የምንሸጥበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በሰፊው ለለመደ ሰው የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ፣ በስነ-ልቦና እና በማህበራዊ ህይወት የሚፈጥረው ጫና ከባድ ነበር፡፡ ከቤተሰቦቻችን የቀሰምነው ጠንካራ የሥራ ባህል ተቸገርን ብለን የሰው እጅ አላየንም። በተለይም ይህ ጊዜ ለእኔ ቤተሰብ በጣም የተፈተነበትና የተቸገረበት ወቅት ነበር” በማለት ያለፉበትን ችግር እና ከችግር የወጡበትን መንገድ አጋርተውናል፡፡
በድጋሚ ወደ አመራርነት የመጡበትን አጋጣሚ ሲናገሩ፦
“ፕሮጀክት ላይ በምሰራበት ወቅት በተለያዩ ጊዜያቶች ከመንግስት አካላት የሚመጡልኝ የሥራ እድሎች ነበሩ፡፡ ከንግድ ሥራ ወደ ሶዶ ከተማ የወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ በመሆን ተመድቤ የመንግስት ሥራን ዳግም መስራት ጀመርኩ” በማለት ስለአጋጣሚው አውግተውናል።
“እዚህ ዘርፍ በኃላፊነት ከአንድ ዓመት በላይ አገልግያለው፡፡ የተጣለብኝን ሃላፊነት በብቃት በመምራትና በማስተባበር አገልግያለሁ። ዘርፉ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ሥራዎች የሚሰሩበት ነው፡፡ ወጣቶችን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ፣ ላብ መተኪያ፣ የስፖርት ቁሳቁስ ያስፈልጋሉ፣ የወጣቶች በጊዜያዊና በቋሚ የሥራ እድሎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ማመቻቸት እና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን” ማከናወን መቻላቸውን አጫውተውናል፡፡
ወ/ሮ ህይወት የሶዶ ከተማ ፕላንና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በዚህም ተቋም የመምራትና የማስተባበር ግዴታቸውን ከባለሙያዎች ጋር ተጋግዘው አገልግለው አልፈዋል፡፡
አሁን ደግሞ የሶዶ ከተማ ሴቶችና ህጻናት ጽህፈት ቤት በኃላፊነት ተመድበው ህብረተሰባቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ሴክተሩ ትልልቅ ሥራዎች የሚሰሩበት መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
በተለይም ከሴቶችና ህጻናት መብት ጋር ተያይዞ ሰፊ ሥራ የሚሰራበት ነው፡፡ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ የስራ ቦታ በመሆኑ ጠንካራ አመራር መሆን እንደሚጠይቅ ይናገራሉ፡፡ በተለይም ደግሞ እናት ሲኮን ለሥራው ከማንም በበለጠ በሴክተሩ ለመስራት የሚያነሳሳ ነው ብለዋል፡፡
“ሥራ ሲሰራ ሁሉም ባሰብነው መንገድ ይሳካል ማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ ሳይሰሩ የሚያልፉ (የሚያመልጡ) ሥራዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ሴክተሩን ስመራ የሚታየኝ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋን በማሰብ ነው የምሰራው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ልጆች ተስፋዎች ናቸው፣ ማንነት ነው፣ ልጆች መስታወቶች ናቸው፡፡ ከዚህም አንጻር ልጆች ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት የመከላከል ሥራ መስራት ሥራ በዋናነት ይመለከታል፡፡ ከደረሰ በኋላ ደግሞ ማናቸውም የመብት ጥሰቶች የፈጸመን አካል ለህግ በማቅረብ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ይደረጋል” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡
ከህጻናት ጋር በተያያዘ በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ የህጻናት ፓርላማ አላቸው፣ የፈጠራ ሥራዎቻቸው የሚታይበት ኤግዚቢሽን ማዘጋጀት፣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፎችን፣ መደበኛ ትምህርት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ እና ሌሎች አሰፈላጊ ነገሮችን ያደርጋሉ፡፡
በህጻናትን ህገ ወጥ ዝውውር ጋር ተያይዞ በሴክተሩ ብቻ የሚሰራ አለመሆኑን ገልጸው። ከሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር ፖሊስ፣ ትራንስፖርት ፅ/ቤት፣ አሰሪና ሰራተኛ ኤጀንሲዎች ጋር በመሆን ህገ ወጥ የህጻናት ዝውውር የመቆጣጠር ሥራዎችን በመስራት ላይ ናቸው፡፡
“በተለይም ከህገ ወጥ የህጻናት ዝውውር ጋር ተያይዞ ትልቅ ችግር የሆነብን ወላጆች በደላሎች ተታለው ልጆቻቸውን ለደላሎች አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡ በመጓጓዝ ላይ እያሉ ይዘን ወደ ህግ በምናመጣበት ጊዜ ወላጆች ቀርበው ለትምህርት ወደ አዲስ አበባ ወይም ለእረፍት ወደ ሌላ ቦታ እየሄዱ ነው ብለው ለፍርድ ቤቱ ምላሽ የሚሰጡበት ሁኔታ አለ” በማለት ለስራቸው መስተጓጎል እየፈጠረባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዋናነት ትኩረት አድርገው የሚሰሩት ደግሞ ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራን በመስራት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የተገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም ለህጻናትም ሆነ አዋቂዎች የህገ ወጥ ዝውውር አስከፊነቱን የማስገንዘብ ሥራ በሚዲያም ሆነ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ላይ፣ በሀይማኖት ተቋማት፣ በእቁብ ቦታ፣ እድር እና በሌሎች ማህበረሰቡ በሚሰባሰቡባቸው ቦታዎች ላይ በመገኘት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ስለተሰሩ ስራዎች ሲናገሩ፡-
“ሴቶችን በንግድ እና በተለያዩ ዘርፎች የራሳቸውን ገቢ እንዲፈጥሩ የሰራናቸው ስራዎች አሉ፡፡ ወደ አመራርነት
እንዲመጡ ከማድረግ አንጻርም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየሰራን ነው” ሲሉ ወ/ሮ ህይወት የተናገሩት፡፡
አመራርነት እና ትዳር አንድ ላይ መምራት አይከብድም? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፦
“ሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋሉ፡፡ ቢሮ 2፡30 ሰዓት በመግባት 6፡30 እንደዚሁም 7፡30 በመግባት 11፡30 በመግባት ኃላፊነትን በአግባቡና በግዜ መወጣት የራሱ ጊዜ፣ ጉልበት እና ሀሳብን መስጠት ይፈልጋል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ከሥራ ሰዓት ውጭ ሥራ ላይ የምናሳልፍበት ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ እንዲዚሁም ለቤተሰብ ለልጆች እና ለባለቤቴ የምሰጣቸው ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ግዴታ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሥራውን ባህሪ የሚረዳ የትዳር አጋር ያስፈልጋል፡፡ ከትዳር አጋር ጋር ግልጽ እና እውነተኛነት ወሳኝ ነው፣ በማንኛውም ቦታ እና ሰዓት ላይ ግልፅ የሆነ መግባባት ካለ ምንም ችግር አይኖርም” ሲሉ የሚመሩበትን መርህ ይናገራሉ፡፡
“በተለይም ደግሞ በሥራ ሰዓት ላይ መድረክ ልመራ እችላለሁ ወይም ግዴታ የምገኝበት ቦታ ላይ ከቤት ለመውጣት ስነሳ ልጆች ወይም የትዳር አጋር ሊታመም ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ በጣም የሚፈተንበት ነው፡፡ መድረክ እየመራሁ ከትምህርት ቤት ተደውሎ ‘ልጅሽ ታሟል’ ነይ የተባልኩበት ጊዜ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ከባለቤቴ ጋር በመመካከር መፍትሄ በማስቀመጥ ችግሮችን የተወጣሁበት አጋጣሚ ነበር” በማለት አውግተውናል፡፡
በሥራቸው አጠገባቸው በመሆን ከፍተኛ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ አዳዲስ ነገሮች ሁልጊዜ ማወቅና ለስኬታቸው ከፍተኛ ሚና እንዳለው ስለባለቤታቸው አውርተው ማይጠግቡት ወ/ሮ ህይወት ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው ስጦታ እንደሆነ እና ሲሳሳቱ ከስተቶቻቸው የመለሷቸው የስራ አጋሮቻቸውን አመስግነዋል፡፡
More Stories
“መንገድ ላይ እያረፍኩ ነበር ትምህርት ቤት የምሄደው” – ወ/ሮ ፍሬህይወት አይሴ
“በእጅ ጋሪ ያመላልሱኝ ነበር” – ተወዳ መንጌ
የስም ነገር