በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሽከርካሪዎች ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን የወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ካምፓስ ገለፀ

በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሽከርካሪዎች ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን የወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ካምፓስ ገለፀ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሽከርካሪዎች ስልጠና እየሰጠ መሆኑን የወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ካምፓስ አስታወቀ።

በስልጠናው ተገቢውን እውቀት እያገኙ መሆኑን ሰልጣኞች ተናግረዋል።

ኮሌጁ ማህበረሰቡን ለማገልገል የተለያዩ ስልጠናዎች እየሰጠ እንደሚገኝ የገለፁት የወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ካምፓስ ምክትል አካዳሚክ ዲን አቶ አጅመል መሀመድ ከዚህም መካከል የመንጃ ፍቃድ ስልጠና ነው ብለዋል።

በትራፊክ አደጋ እየደረሱ ያሉ ችግሮችን ለመቀነስ በቴክኖሎጂ የታገዘ ስልጠና እንደሚሰጥ አቶ አጅመል ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የተሽከርካሪ ምርመራ አገልግሎት በኮሌጁ ውስጥ ባለመኖሩ አሽከርካሪዎች ወደሌላ ቦታ ይሄዱ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አጅመል አገልግሎቱ በመጀመሩ አላስፈላጊ ወጪና እንግልት ማስቀረት መቻሉን ጠቅሰዋል።

የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ከሞተር እስከ ህዝብ አንድ ስልጠና እየሰጡ መሆኑን የገለፁት ደግሞ አሰልጣኝ ሀብታሙ አያሌው ናቸው፡፡

ስልጠናው በንድፈ ሀሳብና በተግባር እየተሰጠ መሆኑንም አንስተዋል።

ከስነ ባህሪ ጋር ተያይዞ የተሳፋሪ አያያዝ፣ የማሽከርከር ስልት እንዲሁም የእቃ አያያዝ ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም አምስቱ የስሜት ህዋሶቻቸውን በመጠቀም የተሽከርካሪን ብልሽት መለየት የሚችሉበትን የጥቃቅን ጥገና ስልጠና እንደሚሰጡም ነው የገለፁት።

አሰልጣኝ ሀብታሙ አክለውም የሰውን ህይወት እየቀጠፈ ያለው የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከአሰልጣኝ ጀምሮ ሁሉም የበኩል እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ሰልጣኝ በረከት አዘነው እና መከተ ኢብራሂም እንደገለፁት ከስነ ምግባር ጀምሮ የተለያዩ ስልጠናዎች እንደተሰጣቸውና በስልጠናው በቂ እውቀት ማግኘታቸውን አንስተዋል።

ስልጠናውን በተገቢው በመውሰድ በንብረትና በሰው ህይወት ላይ እየደረሰ ያለው አደጋ መቀነስ ይኖርብናል ሲሉ አስታየታቸውን ሰጥተዋል።

ዘጋቢ፡ አስፍር ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን