የቴክኖሎጂ ዘርፍ በየጊዜው እየተፋጠነ ባለበት በዚህ ወቅት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፎች ወሳኝ መሆናቸውን  የምስራቅ ጉራጌ ዞን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ ገለፀ

የቴክኖሎጂ ዘርፍ በየጊዜው እየተፋጠነ ባለበት በዚህ ወቅት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፎች ወሳኝ መሆናቸውን  የምስራቅ ጉራጌ ዞን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ ገለፀ

ግራንድ ቪው ኮሌጅ ቡታጅራ ካምፓስ በቴክኒክና ሙያ ዘርፎች ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰልጠናቸውን 204 ተማሪዎችን  አስመርቋል።

የግራንድ ቪው  ኮሌጅ የቡታጅራ ካምፓስ  ፕሬዝዳንትና ባለቤት አቶ ሰለሞን ሚፍታ  እንደተናገሩት ኮሌጁ  ከመማር ማስተማር ስራዉ ጎን ለጎን ማህበራዊ ኃላፊነትን እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል።

ኮሌጅ በቴክኖሎጂ የበለፀጉና የሠለጠኑ ዜጎችን ማፍራት ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰራ መሆኑን  ጠቁመዋል።

በኮሌጁም ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ  የትምህርት  መስኮች ያሰለጠናቸውን  204 ተማሪዎችን  ማስመረቁን ጠቁመው ከነዚህም ውስጥ 1 መቶ 20 ተመራቂዎች ሴቶች መሆናቸውን  ገልጸዋል ።

ኮሌጁ ማህበራዊ  ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር  ለ8 ተማሪዎች  ነፃ የትምህርት  ዕድል መስጠቱንም ጠቅሰዋል ።

በምረቃው ፕሮግራም  ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል  የምስራቅ ጉራጌ ዞን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመዲን ጀማል  ባስተላለፉት መልዕክት የቴክኖሎጂ ዘርፍ በየጊዜው እየተፋጠነ ባለበት በዚህ ወቅት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፎች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተማሪዎች በኮሌጁ ያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም እራሳችውንና  ቤተሰባቸውን ለመለወጥና ለሀገሪቱ ብልጽግና ጠንክረው መስራት እንዳለባቸውም አቶ አህመዲን አሳስበዋል ።

ተመራቂዎች በበኩላቸው በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ  ህዝብንና ሀገርን  በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዕለቱም በትምህርታቸዉ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የዋንጫ እና የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ: ታምራት አለሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን