የወላጆች ቀን እና አንዳንድ ወላጆች
ሠላም ተወዳጆች÷ እንዴት ናችሁ? … ያኔ ያኔ እንደልጅ የማውቃትን ሰኔ 30÷ ሰሞኑን እንደ ወላጅ ታደምኩላችሁ። የልጄን ካርድ ለመቀበል ነው አብሬው የታደምኩት። እናላችሁ በቆይታዬ ራሴን ስታዘበው ነበር።
ትዝብቴ ምን መሰላችሁ?÷ … እኔ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን በምከታተልበት ዘመን÷ ለወላጆች በዓል በልዩ ሁኔታ ነበር የምንዘጋጀው። ድራማው፣ ግጥሙ፣ መነባንቡ፣ ጭፈራው … ብቻ ብዙ ነበር ዝግጅታችን። እያንዳንዳችን የተዘጋጀንበትን ጉዳይ ለታዳሚው እስክናቀርብ÷ እዛው እንዳለን መሽቶ ቢነጋ እንኳን ጉዳያችን አልነበረም። ዋናው እኛ እንታይ እንጂ። ደግሞስ መታየትን ማን ይጠላል?
እናላችሁ አሁን ታዳሚ ስሆን÷ ከሶስት ሰዓት ለማይልቅ ጊዜ ታግሶ መቆየት ከብዶኝ ስቁነጠነጥ ነበር። ለነገሩ እኔ ብቻ አልነበርኩም። አብዛኛው ወላጅ ከሚታየው እና ከሚነገረው ነገር ጋር ጉዳይ አልነበረውም። ሁሉ ታግሶ የቆየው (መታገስ ከተባለ) የልጁን ካርድ ለመቀበል ብቻ ነው።
እኔ ተማሪ የነበርኩበትን ዘመን ካነሳሁት አይቀር÷ ጥቂት ልበላችሁማ። በኛ ጊዜ የድራማ በሉት የግጥም ማጠንጠኛ ሆኖ የሚነሳው ኤች አይ ቪ ኤድስ ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ጥቂት የማይባለው ታዳሚ ድራማን ከእውነተኛ ህይወት ነጥሎ መመልከት የማይሆንለት ነው።
እንዳጋጣሚ ለወላጆች በዓል በተዘጋጀው ድራማ ላይ÷ እናት እና አባቱን በበሽታው ተነጥቆ ከእህት እና ወንድሞቹ ጋር በችግር የሚኖር ገፀ ባህሪ ተሰጥቶኝ ነበር። በወቅቱ ባለን መረዳት ልክ÷ ጥሩ አድርገን አቀረብነው። ለደቂቃዎች የቆየ የማያባራ ጭብጨባ ተሸለምን።
ችግሩ የተፈጠረው በኋላ ነው። አባቴን በቅርበት የምታውቅ አንዲት የሰፈራችን ሴትዮ÷ በጥላቻ እያየችኝ፦
“አንተ ሟርተኛ …” ብላ ስድቧን ልትቀጥል ስትል÷ ነገሯ ስለገባኝ፦
“ኧረ ድራማ ነው÷ ድራማ እኮ ነው። ህብረተሰቡን ለማስተማር …” ብዬ ማብራራቴን ስጀምር… አላስጨረሰችኝም። ከመጀመሪያው ይልቅ ግንባሯን አኮሳትራ÷ አርቃ እየተመለከተችኝ፦
“አንተ ሟርተኛ!÷ ወንድሜ እናንተን አሳድግ ብሎ በርሃ ለበርሃ ይንከራተታል÷ አንተ እዚህ ታሟርትበታለህ። ቆይማ ይምጣ÷ ባልነግርልህ” አለችኝ።
አልተገናኝቶም ነው ነገሩ።
ወዳጄ÷ ባልከው እና ልትል በፈለግከው መካከል እንዲህ ያለ ልዩነት ከገጠመህ ከስረሃል። በተለይ በዚህ ዘመን ነገሮች ወደ ብዙ አቅጣጫ ይጎተታሉ። በፊት በፊት ምንም ነገር ብትል÷ ያልከው ነገር እንኳን ስህተት ቢኖርበት÷ ከጥቂቶች ጆሮ የማለፍ ዕድል አልነበረውም። “ካፍ የወጣ አፋፍ ነው” ማለት ዘንድሮ ነው።
ዘንደሮ ያልከው ብቻ እንዳይመስልህ÷ ልትል ያሰብከው ሁሉ አደባባይ ላይ ተሰጥቶ ነው የሚቆይህ። ወሬ እንደ ንፋስ ሽው እልም በሚልበት በዚህ ጊዜ ሰዎች በስህተት ሲታወቁም÷ ከእውቅና ማማ ሲፈጠፈጡም አይተናል። ቅድሚያ ያልከውን እንጂ እንዲህ ልል ፈልጌ ነው ማለትህን ማንም አይሰማም።
የዛሬዎቹን ልጆች ሳያቸው ስልጥን ያሉ ናቸው። ወላጆቻቸውን ለማዝናናት እንጂ ለማስተማር የሚደክሙ አይነት አይደሉም። ዝግጅታቸውም ስለ እናት እና ስለ እናት ሀገር ይበዛዋል። በዚያ ላይ ሀገርን በልጆች አፍ መስማት የሆነ ደስ የሚያሰኝ ነገር አለው።
ዝግጅቱ ወደ መገባደዱ ሲቃረብ÷ በየክፍሉ በደረጃ የወጡ ተማሪዎች እየተጠሩ ሽልማት መቀበል ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ፈንጠር ብለው የነበሩ ሁለት ወላጆች ወደ ተሸላሚዎቹ ተጠጉ። አንደኛው እንኳን መቅረብ የፈለገ አይመስልም። ሌላኛው ነው እየጎተተ የወሰደው።
ባጠገባችን ሲያልፉ÷አንደኛው ሌላኛውን ይጠይቀዋል፦
“እዚሁ ብንቆም እኮ ይሰማናል። ለምንድነው መጠጋት የፈለግከው?” ተጠያቂው መለሰለት፦
“ምናልባት ልጄ ከተሸለመ ላየው ፈልጌ ነው” አለው።
ከንግግራቸው እንደተረዳሁት÷ ሰውዬው ስለ ልጁ ምንም አያውቅም። ስለ መጀመሪያ ስሚስተር ውጤቱ መረጃ የለውም። የሁለተኛ ሴሚስተር የፈተና ወረቀቶቹን አላያቸውም። ግን ደግሞ ምናልባት ከተሸለመ ብሎ እየጠበቀው ነው።
ወዳጄ÷ ምናልባት የሚባል ተሸላሚ የለም። እዚህ ጋ በስም ተለይተው የሚጠሩትን እና የሚሸለሙትን ተማሪዎች÷ ወላጆቻቸው በቅርበት ያውቋቸዋል። አብረዋቸው ብዙ ጊዜ የቤት ስራ ሰርተዋል። አብረዋቸው አጥንተዋል። ስለ ልጆቻቸው ውጤት ከመምህራኖቻቸው ጋር ተወያይተዋል።
“ብርቱካን በልቼ÷ ሎሚ ሎሚ አገሳኝ” የሚባል ነገር÷ ዘፈን ላይ እንጂ ትምህርት ላይ አይሰራም። እዚህ ብርቱካን ከበላህ ብርቱካንህን÷ ሎሚ ከበላህም ሎሚህን ነው የምታገሳው።
ወዳጄ÷ ልጅህ ውጤታማ እንዲሆን ከፈለግህ÷ ከስልክህ ጋር ያለህን ጊዜ ቀንስ። በጊዜ ወደቤትህ ግባ። ልጅህ ከመተኛቱ በፊት የቤት ስራውን አሰራው። ያልገባውን ጠይቀው። ቀለል ባለ መንገድ አስረዳው። አስተማሪዎቹን አግኛቸው።
ደካማ እና ጠንካራ ጎኖቹ ምን እንደሆኑ ጠይቃቸው። አግዘው። አበረታታው። በዚህ መልኩ የመጣህ ወላጅ ከሆንክ÷ ውጤት ብትጠብቅም ያምርብሃል።
አጠገቤ ከነበረ ሰው ጋር ስለ ሰውዬው እያወራን በመሃል አንዲህ የሚል ጨዋታ አመጣ፦
“አንተ የሱ ይገርምሃል እንዴ?÷ እሱኮ ቢያንስ ልጁ ስንተኛ ክፍል እንደሆነ ያውቃል …” ብሎ ንግግሩን ሊቀጥል ሲል፦
“እሱ ደግሞ ምን ማለት ነው?!” አልኩት÷ መደነቄን በሚያሳብቅ መልኩ።
“ቀን ስራ ቦታ ማታ ደግሞ ግሮሰሪ የማይጠፋ አንድ ሰው አውቃለሁ። ተአምር ካልተፈጠረ በቀር ከግሮሰሪ አይቀርም። ሁል ጊዜም ልጆቹ ከተኙ በኋላ ነው ቤቱ የሚገባው። ባለፈው ስድስተኛ ክፍሎች ሚኒስትሪ የተፈተኑ ቀን÷ ሚስትየው ‘ዛሬ እንኳን መልካም ዕድል ተመኝለት እና ሸኘው÷ ልጅህ ለፈተና እየሄደ ነው። መቼም ዛሬ ሚኒስትሪ እንደሚጀምሩ አትዘነጋውም’ ስትለው ‘እንዴ እንዴ … ስድስተኛ ክፍል ደረሷል እንዴ?’ አይላትም መሰለህ” አለኝ።
ንግግሩ ምንም ስሜት ያልሰጠኝ እኔ፦
“ምነው ባክህ?÷ ስለ ልጁ ቢዘነጋ÷ ስለሚከፍለው ገንዘብ ይዘነጋል እንዴ?” አልኩት÷ የብዙ ወላጆች ራስ ምታት የሆነውን የትምህርት ቤት ክፍያ እያሰብኩ።
“ወዳጄ እኔ፣ አንተ እና መሰሎቻችን የትምህርት ቤት እና መሰል ወጪዎቻችን የሚያስጨንቁን ሰርተን ስለምናመጣ ነው። ያለወዝህ ያመጣኸውን ገንዘብ የትም እንዴትም ብትከፍለው ትዝታው አይኖርህም” አለኝ።
እኛ እንዲህ እየተጨዋወትን÷ ቀደም ብለው ባጠገባችን ያለፉት ሁለት ሰዎች ተመለሱ። የተማሪዎች የሽልማት መርሃ ግብር አልቆ ነው መመለሳቸው። ቅድም “ልጄ ይሸለም ይሆን?” በሚል ተስፋ÷ ጓደኛውን እየጎተተ ያለፈው ሰውዬ፦
“ይኼ ደደብ የሆነ ልጅ÷ እንዴት ሳይሸለም ይቀራል?÷ ስንት ዋጋ ከፍዬ አስተምሬው አንድ ቀን እንኳን አያኮራኝም?!” ሲል÷ ጓደኛው ከአፉ ቀበል አድርጎ፦
“በአባቱ ወጥቶ ይኾናላ!” አለው።
ሰውዬው ፊት ላይ ካነበብበው ብስጭት የተነሳ÷ መሳቅ እየፈለግን ሳንስቅ ቀረን። እንዲህ መበሳጨቱ ግን በልጁ ውጤት ይሁን በጓደኛው ተረብ÷ አንዳችንም ሊገለጥልን አልቻለም።
More Stories
ሀብት ያካበቱ ኢንተርፕራይዞችን ለመፍጠር
በርካታ የቀለም ልጆችን ያፈሩ መምህርት
“አካል ጉዳተኛ ተቀባይ ብቻ አይደለም ሰጪም ነው” – አቶ ልብአገኘሁ ገ/ማሪያም