“ወርቃማ የሚባለውን ዘመን በመምህርነት በማሳለፌ ደስተኛ ነኝ” – መምህር መንግስቴ አየለ
በደረሰ አስፋው
የሙያዎች ሁሉ አባት በሆነው መምህርነት 50 ዓመታትን አገልግለዋል። በዚህ ሙያ ማገልገላቸው ኩራት ይሰማቸዋል። የሙያዎች ሁሉ አባት የማለታቸው ምስጢር ሁሉም ሙያዎች በመምህርነት ድልድይ የተሻገሩ በመሆናቸው ነው ሲሉ ይገልፃሉ፡፡
የዛሬን አያድርገውና ድሮ እሳቸው ጠመኔን ከጥቁር ሰሌዳ ጋር አዋህደው ማስተማር ሲጀምሩ ለመምህር የሚሰጠውን ክብርና ዝና ሲያስታውሱት ልዩ ስሜት ይሰማቸዋል፡፡
“የእኛ ሙሽራ ሹራብ ሠሪ፣ ወሰዳት አስተማሪ” ተብሎ የተዜመለት መምህር በማህበረሰቡ ዘንድም የነበረው ተቀባይነት የተለየ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በ50 አመታት አገልግሎታቸው የሙያውን ክብር አውቀው የበለጠ የሚያስከብሩ መምህራንም እንደነበሩ መታዘባቸውን ነግረውናል፡፡
ባለታሪካችን አቶ መንግስቴ አየለ ወልደ ኢየሱስ ይባላሉ፡፡ የመምህርነት ሙያን ከ1964 ዓ.ም ጀምሮ ነው የተቀላቀሉት፡፡ ወደ መምህርነት መግባት ከልጅነት ጀምሮ ሕልማቸው ነበር። ተማሪዎች ትልቅ ደረጃ ሲደርሱ ማየት በእጅጉ ደስ ይሰኙ ነበር። ደስ እያላቸው የሚሰሩት ስራ በመሆኑ መምህርነትን ከሌሎች ሙያዎች ይልቅ ምርጫቸው እንዳደረጉ ነው የተናገሩት፡፡
አቶ መንግስቴ በቀድሞው ባሌ ጠቅላይ ግዛት በፋሲል አውራጃ በጎሮ ወረዳ ፈንቀል በምትባል መንደር ጥቅምት 12/1943 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡ ወላጅ አባታቸው የቤተክህነት አገልጋይ በመሆናቸው ልጃቸውን አቶ መንግስቴን በመንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰማሩ ይመኙ ነበር፡፡ ዕድሜያቸው 7 ሲሆንም በአካባቢያቸው በሚገኝ በፈንቀል ጊዮርጊስ ደብር የቄስ ትምህርት ቤት እንዲገቡ አደረጉ፡፡ አለቃ ባዬ መንግስቱ በሚባሉ የደብሩ አስተማሪ እግር ስር ሆነው ፊደል ቆጠሩ፣ ማንበብና መጻፍን ጠንቅቀው በማወቅ፣ ዳዊት ደግመዋል፣ ግዕዝም ተምረዋል፡፡
በየደረጃው የሚሰጠውን ትምህርት አጠናቀው በወቅቱ በነበሩት ጳጳስ “በአቡነ ቴዎፍሎስ” በጎባ ከተማ ባለወልድ ስላሴ ቤተክርስቲያን የድቁናና ክህነት ተቀብለው ለአንድ አመት ያህል በፈንቀል ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በድቁና አገልግለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የቤተክህነት አገልግሎታቸው ከአንድ አመት አልዘለለም፡፡ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ይልቅ በዘመናዊ ትምህርት (አስኳላ) ልባቸው ተማረከ፡፡ የአባታቸው ምኞትም እንዳሰቡት አልሆነም፡፡ በ1952 በጎሮ ወረዳ ትምህርት ቤት በመግባት ዘመናዊ ትምህርት (አስኳላ) መከታተል ጀመሩ፡፡
በ1953 ዓ.ም በ1ኛ ክፍል የጀመሩት ዘመናዊ ትምህርት መሰረታዊ የተባሉ ማንበብና መጻፍን በቤተክህነት ትምህርት ጨርሰው ስለነበር ትምህርቱ ጫና አልፈጠረባቸውም። በሂሳብ ትምህርት አንድ አለኝ የምትለዋ ነገር እንቆቅልሽ ሆና ከመፈተናቸው ወጪ የአስኳላው ትምህርት አዲስ አልሆነባቸውም።
እንዲያውም በትምህርታቸው ጉብዝና ስማቸው በትምህርት ቤቱ እና በአካባቢው የናኘ ነበር፡፡ ወላጅ አባታቸው ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ሲገቡ የተቃወሙ ቢሆንም በሂደት ግን ለአቶ መንግስቴ ትምህርት ቤት መግባት ድጋፋቸውን ነው የሰጡት፡፡ እንዲያውም ተሳስቼ ነበር አሁን ግን ቀጥል፤ ህይወትህን ላሰናክል አልፈልግም በማለት አበረታቷቸው፡፡ በአካባቢው ለሚገኙ ወላጆችም ምሳሌ በመሆን ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ አነሳሳቸው፡፡
በወቅቱ በ3 መንፈቀ አመት ነበር የትምህርት ዘመኑ የሚያልቀው ያሉት አቶ መንግስቴ በመጀመሪያው መንፈቀ አመት ከ1ኛ ክፍል ወደ 2ኛ ክፍል፣ በ2ኛው መንፈቀ አመት ከ2ኛ ወደ 3ኛ ክፍል፣ በ3ኛው መንፈቅ አመት ከ3ኛ ክፍል 4ኛ ክፍልን ዘለው ወደ አምስተኛ ክፍል ማለፍ እንደቻሉ ነው ያጫወቱን፡፡ በጎሮ 1ኛና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ1953 ዓ.ም ጀመረው በ1957 ዓ.ም እስከ 7ኛ ክፍል አጠናቀቁ፡፡ የተማሪው በእውቀቱ ብቁ መሆን በመምህራንና በትምህርት ቤቱ ከተረጋገጠ በተርም ማሳለፍ የተለመደ የትምህርት ስርአት እንደነበረም ነው የተናገሩት፡፡
በ1958 ዓ.ም ጎባ ከተማ አዝማች ደግልሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው የ8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ጀመሩ፡፡ ከጎሮ ወደ ጎባ ሲሸጋገሩ እንደቀድሞው ዘመድ ጋር ተጠግተው አልነበረም፡፡ ከቤተሰብ ተለይተው መኖር ለጀመሩት አቶ መንግስቴ ርሃብና ጥማቱ ለችግር ቢያጋልጣቸውም ለትምህርታቸው የሚሰጡት ትኩረት ግን የተለየ እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡ በአንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ቤት ተከራዩ፡፡ እንጨት ለቅመውና ፈልጠው ቂጣ እየጋገሩ ነበር የተማሩት፡፡ ትምህርት ቤት ሲዘጋ በአህያ ዱቄት ጭነው ያመጣሉ። በአዝማች ደግልሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ8ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለው በ1962 ዓ.ም አጠናቀቁ፡፡
የ12ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቁ ለመምህርነት ሙያ የሚያበቃ የመግቢያ ፈተና ተፈትነው ጥሩ ውጤት በማምጣት ወደ ደብረ ብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገቡ፡፡ ለአንድ አመት የተሰጠውን ስልጠና አጠናቀው በ1963 ዓ.ም ተመረቁ፡፡ ከስልጠናው በኋላም በ1964 ዓ.ም በእጣ ምድብ ቦታ ተሰጥቷቸው በቀድሞው ወሎ ጠቅላይ ግዛት ወረሂመኖ አውራጃ በአጅባር ከተማ በአሊ ትምህርት ቤት ተመድበው ለአንድ አመት በመምህርነት አገልግለዋል፡፡
በ1965 ዓ.ም በቀድሞ አጠራሩ ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ሲዳማ አውራጃ ተዛወሩ። የተዛወሩትም ለቤተሰብ እንዲቀርባቸው በማሰብ እንጂ ቦታውን ጠልተው እንዳልሆነ ነው የተናገሩት፡፡ በዚህም አርቤጎና አውራጃ ቦና ቀበለንካ በሽሮ ትምህርት ቤት ከ1965 ዓ.ም ጀምሮ ለ4 ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በ1969 ዓ.ም ወደ ሀዋሳ ከተማ ታቦር 1ኛና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዛዋውረው ማገልገል ጀመሩ፡፡ በዚህ ትምህርት ቤትም ጡረታ እስከወጡበት 2003 ዓ.ም ድረስ ማገልገላቸውን ነው የገለጹልን፡፡
አቶ መንግስቴ በመምህርነት ላይ እያሉ በስራ ላይ ስልጠና እውቀታቸውን ከማጎልበት አልቦዘኑም፡፡ ቀድሞ በደብረ ብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም በሰርተፊኬት የተመረቁ ሲሆን ይህን ለማሳደግ በሀዋሳ እርሻ ኮሌጅ ገብተው በእጽዋት ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ በአድቫንስ ዲፕሎማ ተመርቀዋል። በተመሳሳይ በሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የክረምት ስልጠና በባዮሎጂ ትምህርት በዲፕሎማ እንደተመረቁ ነው የተናገሩት፡፡
አቶ መንግስቴ በስራ ላይ ትጉህ ነበሩ፡፡ ይህም በተለያዩ ጊዜያት ተሸላሚ እንዳደረጋቸው ነው የገለጹልን፡፡ በ1978 ዓ.ም ሀዋሳ ታቦር መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባስመዘገቡት የስራ ትጋትና ውጤት ከነበሩት መምህራን መካከል በአውራጃ ደረጃ በመመረጥ የምስክር ወረቀትና የእውቅና ሽልማት አግኝተዋል፡፡ በተለያዩ ክበቦች እና የትምህርት ክፍል የሃላፊነት ቦታዎች ባሳዩት ትጋት የምስጋና እና የምስክር ወረቀቶችን ተሸልመዋል፡፡ በመኖሪያ ቀበሌያቸውም ቢሆን በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች በመሳተፍ በእውቀታቸውና ጉልበታቸው ህዝብን አገልግለዋል፡፡
መምህርነትን የሚወዱት ሙያ መሆኑን የሚገልጹት አቶ መንግስቴ ጡረታ ቢወጡም እንኳ ከሙያው መቆራረጥን አልፈለጉም። ከጡረታ በኋላም በግል ትምህርት ቤቶች ተቀጥረው መስራቱን ቀጠሉ፡፡ በ2004 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ አረብ ሰፈር እናት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተምረዋል፡፡ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 9 ዓመታት ሌክ ሳይድ ትምህርት ቤት በመቀጠር አገልግለዋል፡፡ በአጠቃላይ አቶ መንግስቴ በመንግስት ትምህርት ቤት ለ40 ዓመታት፣ በግል ትምህርት ቤቶች ደግሞ ለ10 ዓመታት በድምሩ ለ50 ዓመታት ያህል በገጠር እና በከተማ ሀገርንና ህዝብ አገልግለዋል፡፡
ማስተማሩን ካቆሙ 13 ዓመታት እንደሆናቸው የገለጹልን አቶ መንግስቴ፤ አሁንም ከእውቀቱ መንደር አልራቁም፡፡ የባይሎጂና ኬሚስትሪ ማገናዘቢያ ሞጁሎችን በማዘጋጀት እና በመሸጥ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡ ይህን ስራ ታቦር 1ኛ ደረጃ ሲያስተምሩ እንደጀመሩት ጠቁመው በዚህ ስራቸውም ትምህርት ቤቱን፣ ተማሪዎችንም በማገልገል ያበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅና ያገኙበት ጭምር እንደሆነ ነው የተናገሩት። አሁንም ቢሆን ማገናዘቢያ ሞጅሎችን ማዘጋጀታቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡ በዘርፉ የካበተ ልምድና ዕውቀት ባላቸው ባለሙያዎች በማስገምገም ጭምር ለሽያጭ እንደሚያውሉ ነው የተናገሩት፡፡
አቶ መንግስቴ የትምህርት ስርዓቱ መልካምና መጥፎ ሂደቶችን እያለፈ እንደመጣ ያነሳሉ፡፡ ቴክኖሎጂው ለትውልዱ ይዞት የመጣ በረከት እንዳለ ሁሉ መረገምም ይዞ የመጣ ነው ባይ ናቸው፡፡ ቴክኖሎጂው ትምህርቱን አንድ እርምጃ እንደሚያሳድገውም ተስፋ ያላቸው ቢሆንም ተጽዕኖም ይዞ መጥቷል ይላሉ፡፡ በተለይ ጠቃሚ ባህሎቻችንና እሴቶቻችን በመሸርሸር ተጽእኖ እየፈጠረ እንደሆነ ትዝብታቸውን አጋርተውናል፡፡
ከስነ ምግባር አኳያ ለመምህራንና ቤተሰብ የማይታዘዝና የማያከብር ትውልድ መጥቶብናል፡፡ በዚህም የተነሳ በርካቶች መምህርነትን እየጠሉት መጥተዋል የሚሉት ባለታሪካችን ችግሩ በተማሪው ብቻ ሳይሆን በወላጆችም የሚንጸባረቅ በመሆኑ አሳሳቢ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡ ተጨባጭ ክህሎትን ጨብጦ ከመውጣት አንጻርም ጉድለት አለበት ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡
“የቀድሞው ተማሪ አንባቢ ነው፣ የራሱን ጥረት ያደርጋል፣ እውቀቱን ለማሳደግ የማይፈነቅለው ድንጋይ አልነበረም፣ የውድድር ስሜት ነበር፣ እልክና ቁጭትም በተማሪዎች መካከል ይታይ ነበር፡፡ ዛሬ ይህ የለም” ሲሉ ነው ያለውን ሁኔታ የገለጹት፡፡ በአሁን ወቅት በስርአተ ትምህርቱ እንደሚያፍሩ ገልጸው ለዚህም አብነት ያደረጉት በሌክ ሳይድ ትምህርት ቤት በመምህርነት ሲያገለግሉ የተመለከቱትን ነው፡፡
“ትምህርት ቤቱ መምህራንን ለመቅጠር ማስታወቂያ ያወጣል፡፡ እነዚህንም መፈተን ለእኔ የተሰጠ ሥራ ነበር፡፡ ተፈታኞች የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም 2ኛ ዲግሪ እንዳላቸው እና ከመንግስት ዩኒቨርስቲዎች እንደተመረቁ ይጠቅሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ በተግባር ሲፈተኑ በቂ እውቀትና ክህሎት ጨብጠዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ አንዳንዶችን ሊያስቀይም ቢችልም እውነቱና በተግባር ያረጋገጥኩት ይህ ነው፡፡ ስለዚህ የዘመኑ ትምህርት ፈውስ ወይም መድሃኒት ያስፈልገዋል ሲሉ ነው ትዝብታቸውን ቁጭ በተሞላ ሁኔታ የገለጹት፡፡
ጡረታ መውጣት ሙሉ ለሙሉ ከስራ ውጪ ነህ ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል ይላሉ፡፡ ዛሬም ቢሆን በስራ ላይ ነኝ ያሉ ሲሆን በእሳቸው ዘንድ በከንቱ የምትባክን ጊዜ እንደሌለች ነው የተናገሩት፡፡ ሁሌም ከመጽሃፍት ጋር ነው የሚያሳልፉት፡፡ መጽሃፍትን በማዘጋጀትም ብዙ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ በርካቶች ግን ከዚህ በተቃራኒው ሆነው ስለሚመለከቱ ከሳቸው ልምድ ሊወሰዱ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ ጡረታ ከመውጣት በፊት እራስን ቀድሞ ማዘጋጀት ከጡረታ በኋላ ለሚከሰተው ችግር ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን በመጠቆም፡፡
አቶ መንግስቴ በወለዷቸው ልጆቻቸውም መባረካቸውን ነው የተናገሩት። የስራ ባልደረባቸው ከነበሩት መምህርት ጋር በ1976 ዓ.ም ከመሰረቱት ትዳር አራት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ እነዚህም አስተማሪ፣ ሀኪም፣ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሙያው የሚያገለግል፣ እንዲሁም ዶክተር ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ልጆቻቸው እራሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን በሙያቸው እያገለገሉ መሆናቸውን ጠቅሰው በዚህም ደስተኛ እንደሆኑ ነው የተናገሩት፡፡
አቶ መንግስቴ በመምህርነት ማገልገል ሲጀምሩ የሚከፈላቸው 225 ብር ብቻ ነበር፡፡ በበቅሎ ወይም በእግር ወደ ተመደቡበት ትምህርት ቤት መሄድ ግድ ነበር፡፡ መንገዱ ዳገትና ቁልቁለት የበዛበት ቢሆንም ድካምን እንደማያስቡት ያስታውሳሉ፡፡ ለሚወዷት ሀገራቸው የሚከፈል ዋጋ እንጂ የጥቅም ጉዳይ አልነበረም፡፡
‹‹በመንገድ ቢሆን በመኖሪያ መንደር ባዳ የመሆን ስሜት አልነበረም፡፡ ረሃብና ጥማት ለአስተማሪ አይታሰብም፡፡ ባቄላ እሸት ይዞ የሚሸኝ አርሶ አደር አለ፡፡ ህዝቡ ለመምህር ያለውን ገልብጦ ለመስጠት አይሰስትም። ሲመሽ መኝታውን ለቆ የሞቀውን አልብሶ እራት ጋብዞ ያስተኛን ነበር፡፡ ወተቱ የኛ ነበር። መምህር ያልተጠራበት ድግስ አይደምቅም። የጫካ ሽፍታ እንኳ መምህርን በመንገድ ሲያገኝ በአጃቢ ነበር የሚሸኘው፡፡ አንድ ችግር ቢፈጠር ሽፍታው እከሌ ነው ይህን ያደረገው ተብሎ ስሙ እንዲጎድፍ አይፈልግም ነበር ሲሉ ነው በወቅቱ ለመምህራን የሚሰጠውን ክብር የገለጹት፡፡ በዚህም ወርቃማ የሚባለውን ዘመን በመምህርነት በማለፋቸው ደስተኛ እንደሆኑ በኩራ ይናገራሉ፡፡
በወር በሚከፈላቸው 225 ብር የተንደላቀቀ ኑሮ ይኖር ነበር፡፡ በማህበረሰቡ ዘንድም አስተማሪ ያለው ተቀባይነት የተለየ ነበር፡፡ “የኛ ሙሽራ ሹራብ ሰሪ፣ ወሰዳት አስተማሪ” እየተባለ የሚዘፈንለትን አስተማሪ ማግባት ብርቅ የነበረበት ጊዜ እንደነበር ወደ ኋላ ዘወር ብለው ያስታውሳሉ፡፡ የኑሮውንም ነገር ሲያነሱ ጤፍ አንድ ኩንታል 12 ብር፣ ፍየል 2 ብር፣ ቅቤ በቅል 2 ብር፣ የቤት ሰራተኛ የወር ደመወዝ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ነበር ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡
ታድያ ይህን የሚያህል የኃላፊነት ዙፋን ላይ ያለው የመምህርነት ሙያ ሊከበር እንደሚገባ ሳያሳስቡ አላለፉም። የሰዎች የማንነት ግንባታ በሚጀምርበት የልጅነት እድሜ ላይ ነገሮችን እንዲያገናዝቡ፣ ችግር እንዲፈቱና መረጃዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያስችላቸውን ጥበብ የሚያስተምሩት መምህራን በመሆናቸው ለመምህራን ትኩረት ሊደረግ ይገባል ሲሉም መልዕክት አዘል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
More Stories
ሀብት ያካበቱ ኢንተርፕራይዞችን ለመፍጠር
የወላጆች ቀን እና አንዳንድ ወላጆች
በርካታ የቀለም ልጆችን ያፈሩ መምህርት