በማህበረሰቡ ዘንድ ይስተዋሉ የነበሩ ነባር ችግሮችን መቅረፍ የቻሉ ቴክኖሎጂዎች እያቀረበ መሆኑን የቡታጅራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ
ኮሌጁ አሁን ላይ ወቅቱን የዋጁና የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት የቻሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በማምረት ላይ መሆኑም ተመላክቷል።
የቡታጅራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ አብድልዋሂድ መሃመድ ከወልቂጤ ኤፍ ኤም 89.2 ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ የቡታጅራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በሁሉ አቀፍ ዘርፎች ላይ ደረጃ በደረጃ እራሱን እያጎለበተ በመምጣት አሁን ላይ ጥራት ያለው ትምህርትና ስልጠና ከመስጠት ባሻገር ወቅቱን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠርና በመቅዳት ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።
ኮሌጁ ለስልጠና ምቹ ከማድረግ ባለፈ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ማህበረሰባዊ ጠቀሜታ ያላቸው ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል የኮሌጁ ዲን አቶ አብድልዋሂድ መሀመድ።
አሁን ላይ ወቅቱን የዋጁና የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት የቻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማምረት ላይ መሆኑን ተናግረው፤ እነዚህም በማህበረሰቡ ዘንድ ይስተዋሉ የነበሩ ነባር የሆኑ ችግሮችን መቅረፍ የቻሉ ናቸው ብለዋል።
በዚህም ኮሌጁ ቀደም ሲል በውጭ ይገባ የነበረ የተንጠልጣይ ድልድይ ቴክኖሎጂ ወጤታማ በሆነ መልኩ በመስራት ለአገልግሎት ማብቃቱንም ዲኑ በማሳያነት አንስተዋል።
በምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ አሽገዴ ቀበሌ የተሰራው የተንጠልጣይ ድልድይ ቴክኖሎጂ በሃገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳካ መልኩ የተሰራ እንደሆነ አመላክተዋል።
120 ሜትር ርዝመት ያለው ተንጠልጣይ ድልድዩ በመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ተራርቆ የነበረን ማህበረሰብ ማገናኘት ከመቻሉም በላይ ጊዜን በመቆጠብ ማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮቹን በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲከውን ያደረገ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በዚህ ወቅት ኮሌጁ በዘርፉ እራሱን በማላቅ የተሞክሮ መቀመሪያ ሆኗል ያሉት የኮሌጁ ዲን አቶ አብድልዋሂድ መሃመድ፤ በዚህም በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ ዞኖች ቴክኖሎጂውን በመስራት አሻራውን እያኖረ ነው ብለዋል።
በሌላ መልኩ የአርሶአደሩን ችግር በመቅረፍ ተጠቃሚነቱን የሚያሳድጉ ተግባራት ማከናወን አንዱ የኮሌጁ ዓላማ መሆኑን ጠቁመው፤ በዘንድሮው አመትም ወጪ ቆጣቢና በአንዴ ብዙ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችል ቴክኖሎጂ መፍጠሩን አውስተዋል።
በዚህም ኮሌጁ በዘርፉ በክልል አቀፍ ወድድር ቀዳሚ ከመሆን ባሻገር በሃገር አቀፍ ወድድርም ከአዲስ አበባ ቀጥሎ 2ኛ ደረጃን በመያዝ ክልሉን ማስጠራት ችሏል በማለት በቀጣይም ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በብዛትና በጥራት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ዲኑ አመላክተዋል።
በተጨማሪም የኢንደስትሪ ኤክሰቴንሽን ስልጠና በመስጠት ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ እንዲሆኑ ይደረጋል ነው ያሉት።
በመንግስት እቅድ መሰረት ኮሌጁ ከመንግስት የበጀት ጥገኝነት ለመውጣት አቅዶ እየሰራ ስለመሆኑም ገልጸው አሁን ላይ ይህንኑ እቅድ በሚያሳካ መልኩ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ይህን ተከትሎም ኮሌጁ አራት ዘርፎች ላይ ኢንተርፕራይዞችን ከፍቶ እየሰራ መሆኑን በማስታወቅ ህብረተሰቡም በተቋሙ የሚፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቃሚ መሆን እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።
በመሆኑም በ2017 በጀት አመት ኮሌጁ በሁሉም ዘርፍ ወጤታማ ተግባራት የተከናወኑበት ነው ያሉት አቶ አብድልዋሂድ፤ ግቡ እንዲሳካ ላደረጉ በየደረጃው የሚገኙ አካላትን አመስግነዋል።
ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ሃገሪቱ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የያዘችውን ውጥን በማሳከቱ ረገድ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራችዎች እየተሰሩ መሆናቸው ተገለጸ
ዜጎች የተሻለ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ማንኛውም ተግባር እንዲያሳልጡ መንግስት ከሚሠራው በተጨማሪ የልማት አጋር አካላት ተግባር ወሳኝ መሆኑን የኣሪ ዞን አስታወቀ
እንደ ሃገር የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለማፋጠን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉን በሚገባ መደገፍ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ