“ሳይደግስ አይጣላም”
በየሩቅነሽ ሰሙንጉስ
የሰው ልጅ የተፈጠረበት ዓላማ ከገባው ወደፊት መራመድ የሚያስችሉ ሥራዎችን ያለተስፋ መቁረጥ ይሰራል፡፡ ጠንክሮ ከሰራ እንደሚለወጥና ከራሱም አልፎ በቅርቡ ላሉ ሰዎች መፍትሄ መሆን እንደሚችል የዛሬዋ እቱ-መለኛ ማሳያ ናቸው፡፡
የዛሬ የእቱ መለኛ አምድ ባለተሞክሮ ከልጅነታቸው ጀምሮ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈው የራሳቸውን ህይወትና ኑሮ ማሻሻል የቻሉ ብርቱ ሴት ናቸው ሲሉ ብዙዎች የሚመሰክሩላቸው ናቸው፡፡
ወ/ሮ ስንታየሁ በቀለ ይባላሉ፡፡ ተወልደው ያደጉት ይርጋዓለም ከተማ 03 ቀበሌ ሲሆን እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የ1ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዳራሽ ትምህርት ቤት፣ የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ደግሞ በጮራ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡
ቤተሰቦቻቸው የተለያዩ የእንጨትና ዕደ ጥበብ ሥራዎችን በመሥራት አራት ልጆቻቸውን ማሳደግ ችለዋል፡፡ አባታቸው የእንጨት ስራዎችን በተለይ ደግሞ ወንበርና ጠረጴዛ በመስራት የሚታወቁ ሲሆን እናታቸው ደግሞ የእጅ ስራዎችን በመሥራት በሚያገኙት ገቢ ቤታቸውን ይደግፉ ነበር፡፡
ሆኖም ግን ከጊዜ በኋላ አባታቸው የሳምባ በሽታ ስለተገኘባቸው ቀድሞ እንደሚሰሩት ተንቀሳቅሰው ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር አልቻሉም፡፡ በዚህም ምክንያት 4ኛ ልጅ የሆኑት ወ/ሮ ስንታየሁ ትምህርታቸውን አቋርጠው ቤተሰቡን የመደጎም እጣ ፋንታ እንደወደቀባቸው ይናገራሉ፡፡
ይሁን እንጂ አባታቸውን ሙሉ በሙሉ ሥራ ለማስቆም የወጠኑት ውጥን በቤተሰቡ ዘንድ በአንዴ ተቀባይነት ባያገኝም ባደረጉት ጥረት አሳምነው ያገኙትን ሥራ መሥራት ጀመሩ፡፡
በዚህም የቤተሰቡን ሙሉ ኃላፊነት ተረክበው የሰፈር ልጆችን ፀጉራቸውን ሹሩባ በመስራት፣ ዳቦ ቆሎ አዘጋጅቶ በመሸጥ እንዲሁም ከሰልና እንጨት እየቸረቸሩ በሚያገኙት ገቢ ቤተሰባቸውን በመደገፍ ደስታ የተሞላበት ኑሮ መኖር መጀመራቸውን ያስታውሳሉ፡፡
ሆኖም ግን ይላሉ ወ/ሮ ስንታየሁ ‹‹አባቴ ትምህርቴን በማቋረጤ ደስተኛ ስላልነበረ ቀን እየሰራሁ ማታ እንድማር በተደጋጋሚ ይጠይቀኝ ነበር፡፡
በኋላ ላይ ተመዝግቤ ትምህርቴን ብቀጥልም ተረጋግቼ ትምህርቴን እየተማርኩ ባለመሆኑ 8ኛ ክፍል 2 ጊዜ ደገምኩኝና ትምህርት ላይ ተስፋ ቆረጥኩ። በኋላም አባቴን ከዚህ በላይ መቀጠል እንደማልፈልግና የፀጉር ሙያን መማር እንደምፈልግ ነግሬው ሙያ ተማርኩ›› ሲሉ ያለፉበትን መንገድ ይናገራሉ፡፡
‹‹ቢሆንም አባቴ በትምህርቴ ውጤታማ ሆኜ ቢያየኝ ይመርጥ ስለነበረ ወደፊት እንደምቀጥል አሳውቄው በከተማችን ወደሚገኝ አንድ የሴቶች ፀጉር ቤት ስራ ለመቀጠር ሄድኩ፡፡ ይሁን እንጂ የፀጉር ቤት ባለቤቷ የጸጉር ሙያውን መጀመሪያ በማየት መልመድ እንደሚጠበቅብኝ ነግራኝ ቤት በመወልወል፣ ፎጣና ቢጎዲን በማጠብ በነፃ ለአንድ ወር ለማገልገል ተገደድኩ፡፡
‹‹በዚህ ሁሉ ግን የደንበኞቿን ፀጉር እንዳጥብና እንድጠቀልል ስለማትፈቅድልኝ ፀጉር እንዴት እንደሚታጠብና እንደሚጠቀለል በተደጋጋሚ እያየሁ ማታ ወደቤት ስመለስ ቢጎዲን ደብቄ በመውሰድ ዊጎችን ሰብስቤ ልክ እንደ ፀጉር በመጠቅለል እለማመድና ጠዋት ደግሞ ወደቤት የወሰድኩትን ቢጎድን እመልስ ነበር፡፡
‹‹አንድ ቀን ግን አሰሪዬ ማርፈዷን ተከትሎ ለመሠራት ከመጡ ደንበኞች መካከል የሶስቱን ፀጉር በመሥራት ጉርሻ ጭምር ያስገኘልኝን ጥሩ ሥራ መሥራት ቻልኩ፡፡ ነገር ግን አለቃዬ ስትመጣ ከመደሰት ይልቅ ተናዳ የሰራሁበትን እንኳን ሳትከፍል አባረረችኝ›› ሲሉ ሥራውን ለመልመድ ያደረጉትን ጥረት አንስተዋል፡፡
‹‹ይሁን እንጂ በዚህ ብስጭት ውስጥ እያለሁ ‹ፈጣሪ ሳይደግስ አይጣላም’ እንደሚባለው አንድ ከአዲስ አበባ መጥታ ፀጉር ቤት የከፈተች ሴትዮ የፀጉር ባለሙያ እንደምትፈልግ የሰሙ ሰዎች እኔን ጠቁመዋት በአጭር ጊዜ ሥራ ጀመርኩ፡፡
“ወቅቱ የገና በዓል ሰሞን ስለነበር ሹሩባና የፀጉር ስፌት እንዲሁም የፀጉር ተኩስ ስራ እሰራ ስለነበር ብዙም ሳልቆይ ደመወዜን በእጥፍ ጨምራ 600 መቶ ብር መክፈል ጀመረች፡፡ በስራዬ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። ቤተሰቦቼም የሚያስፈልጋቸውን እያደረኩ እዚያው ቤት ለ8 ወራት ሰራሁ፡፡
“ከዚያም አንዲት ሴት ወደ ሀዋሳ ብትሄጂ በተሻለ ደመወዝ ከመሥራት ባለፈ ልምድሽንም ታዳብሪያለሽ የሚል ሃሳብ ስለነገረችኝ፤ በሃሳቡ በመስማማት ከእሷ ጋር በ2000 ዓ.ም መጀመሪያዎቹ አካባቢ ወደ ሃዋሳ መጣሁ›› ሲሉ ያለፉበትን የመጀመሪያ የሥራ ዓለም ጉዞ ይናገራሉ፡፡
ወደ ሀዋሳ መጥተውም የሴቶች ፀጉር ቤት በ1 ሺህ ብር ተቀጥረው መሥራት ጀመሩ። ፀጉር ቤቱ ገበያ ያለው በመሆኑ እዚያው ልምዳቸውን በማሻሻል ጥሩ የፀጉር ስራዎችን መስራት ቻሉ፡፡ ነገር ግን 2 ወር ከ15 ቀን ከሰሩ በኋላ ከፀጉር ቤት ባለቤቷ ጋር አለመግባባቶች መፈጠራቸውን ተከትሎ ወደ ሌላ ፀጉር ቤት በ1 ሺህ 200 ብር ተቀጥረው ገቡ፡፡
ስለሁኔታው ሲያስታውሱ፡- ‹‹የፀጉር ቤቱ ባለቤቱ ወንድ ነው፤ ባህሪውም ጥሩ ነበር፡፡ በመግባባትና በመተጋገዝ ለ2 ዓመት እሱ ጋር በመሥራት ለቤተሰቦቼ በየወሩ ብር እልክላቸዋለሁ፡፡
‹‹ከአሰሪዬ ጋር በጥሩ መግባባት እየሰራን እያለ፤ አንድ ቀን ድንገት እንደሚወደኝና ለትዳር እንደሚፈልገኝ ነገረኝ፡፡ እኔ የቤተሰብ ኃላፊነት ስለነበረብኝ ይህንን ጥያቄ ማስተናገድ ስላልፈለኩኝ ስራዬን ትቼ ወደተከራየሁበት ቤት ሄጄ ተቀመጥኩኝ›› ሲሉ የትዳራቸው ጅማሬ እንዴት እንደነበር ከትዝታ ማህደራቸው አጋርተውናል፡፡
‹‹አሰሪዬ ስራ እንዳቆምኩ ሲረዳ የተከራየሁበት ቤት ድረስ መጥቶ ለቁም ነገር እንደሚፈልገኝና የወደፊት ሚስቱ እንድሆን ማሰቡን ነገረኝ፡፡ እኔም አባቴና እናቴን አስፈቅዶ ፈቃደኛ ከሆኑ እንደምንጋባ ነገርኩት፡፡ እሱም ወደ ይርጋዓለም ሽማግሌ ልኮ ቤተሰቦቼ ስለፈቀዱ ከአሁኑ ባለቤቴ ጋር ተጋባን›› ሲሉም ግንኙነቱ ወደ ቁም-ነገር መሸጋገሩን ያስታውሳሉ፡፡
በትዳራቸው ደስተኛ መሆን የቻሉት ባለታሪካችን ወ/ሮ ስንታየሁ አንድ ልጅ ከወለዱ በኋላ የፀጉር ቤት ስራቸው በፈለጉት ልክ ማደግ ስላልቻለ ከባለቤታቸው ጋር በመማከር ወደ አረብ ሃገር ለመሄድ ወሰኑ፡፡
ባለቤታቸው ህፃኑን ከማሳደግ ጎን ለጎን የፀጉር ቤት ሥራውን በመሥራት የአባትነት ሚናቸውን መወጣታቸውን እና እሳቸውም ከ3 ዓመታት የአረብ ሃገር ቆይታ በኋላ ያሰቡት ሳይሳካ ቀርቶ መመለሳቸውን ቁጭት ባዘለ ስሜት ነግረውናል፡፡
በዚህም ግን ተስፋ መቁረጥ አልፈለጉም፡፡ በዙሪያቸው ያለውን አጋጣሚዎች ሁሉ እንደ አማራጭ ይጠቀሙ ስለነበር፤ ባህል አዳራሽ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ግለሰቦች በሴፍትኔት በማደራጀት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ሲያስብ እሳቸውም በወር 1 ሺህ 900 ብር እየተከፈላቸው መንገድ መጥረግ ጀመሩ፡፡
በዚህ ሥራ ለአንድ ዓመት ከሰሩ በኋላ በሴፍትኔት ለታቀፉ ሁሉም አባላት 25 ሺህ ብር ሲሰጥ እሳቸውም የድርሻቸውን ወስደው አንድ ተጨማሪ ካክስ በመግዛት ፀጉር ቤታቸውን ማጠናከራቸውን ይናገራሉ፡፡
ቀን ቀን ፀጉር ቤት ባለቤታቸውን እያገዙ፤ ሌሊት ደግሞ መንገድ በመጥረግ ኑሮን ለማሸነፍ ታግለዋል፡፡
የመንገድ ጠረጋ ሥራውን ለ3 ዓመት ከሰሩ በኋላ እሳቸውንና አብረዋቸው ይሰሩ የነበሩ ሴቶችን አዲስ አበባ ከሚገኝ አንድ ድርጅት ጋር በመቀናጀት እንዲሰለጥኑ መደረጉን ይናገራሉ፡፡ ሥልጠናው በቃንጫ የሚሰሩ የተለያዩ ዲዛይን ያላቸው ቦርሳዎችን መሥራት የሚያስችል ሲሆን ለሦስት ወራት 1 ሺህ 500 ብር እየተከፈላቸው ተከታትለው የሙያ ባለቤት ሆኑ፡፡
በዚህ ሁሉ ግን ባለቤታቸው የፀጉር ቤቱን ስራ በመሸፈን እና ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት በመቀበል እንዲሁም አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ በብዙ እንደደገፏቸው በማንሳት ያለባለቤታቸው የትም መድረስ እንደማይችሉ በመግለፅ ምስጋናቸውን አድርሰዋል፡፡
ስልጠናው ከጠዋት 2 ሰዓት እስከ 6 ሲሆን፤ ከስልጠናው ያገኙትን ክህሎት ከገበያ ቃጫ በመግዛት እንዴት እንደሚገመድና ቦርሳዎች እንዴት እንደሚሰሩ ባለቤታቸውን ማሰልጠናቸው፤ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደሚባለው ያደረገላቸው ይመስላል፡፡ ሙያውን በአጭር ጊዜ ከመለድመድ ባለፈ ባለቤታቸውን የተጨማሪ ሙያ ባለቤት በማድረግ ገቢያቸው እንዲያድግ አድርጓል፡፡
በዚህም ጠዋት ስልጠና ሲሄዱ ባለቤታቸው ቃጫውን እየገመዱ ለሥራ እያዘጋጁ ይጠብቋቸዋል፤ ከስልጠናው መልስ ከሰዓት የፀጉር ደንበኞቻቸው እስኪመጡ ድረስ ቦርሳዎችን በመስራት የተለያዩ ቦርሳዎችን መምረጥ ጀምረዋል፡፡
አሁን ወ/ሮ ስንታየሁ የ3 ወር ስልጠናቸውን የጨረሱ ሲሆን እዚያው ፀጉር ቤት በመሆን እንደ ሁለተኛ ስራ ከባለቤታቸው ጋር በመተጋገዝ በተለያዩ ቀለሞች የተሰሩ ቦርሳዎችን በማምረት ለፀጉር ደንበኞቻቸው ከሺህ እስከ 1 ሺህ 500 ብር በመሸጥ እየተጠቀሙ ነው፡፡
ትዳራቸው መተሳሰብ እንዲኖረው የሄዱበት የተለየ መንገድ ካለ በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡- ‹‹ባለቤቴ በጣም ትዕግስተኛ ሰው ነው፡፡ እኔ በባህሪዬ በጣም ችኩል ነኝ፡፡ ዛሬ ከባለቤቴ ጋር አብረን በትዳር ህይወት 16 ዓመታትን ኖረን 3 ልጆችን ወልደናል፡፡
‹‹ያለፍንበት መንገዶች ብዙ ናቸው። በሕይወት መንገዳችን አሳዛኝም፤ ደስ የሚሉ ጊዜያትም ነበሩ፡፡ ሁሉንም አብረን አሳልፈናል፡፡ ነገር ግን ይሄ ቀን እንደሚያልፍ እየመከረኝ፤ እኔ ፈጠን ስል አትቸኩዪ እያለ በእሱ መልካም ፀባይ ነው ዛሬ ላይ የደረስነው፡፡ በህይወታችን ፈጣሪን ማስቀደም እንዳለብኝ ይነግረኝ ስለነበር ለዛሬ በቅተናል፡፡
‹‹ዛሬ በቤታቸን መደማመጥና ፍቅር አለ፡፡ እሱ ለቤታችን ጥሩ ነው ብሎ የሚያመጣውን ሃሳብ እሰማና እንመካከርበታለን፡፡ እሱም የሚያመጣውን ሃሳብ እንዲሁ እየተነጋገርን እንግባባለን፡፡ ስለዚህ ብዙ ችግሮችን አልፈን እዚህ ብንደርስም ነገ የተሻለ እንደሚሆን እናምናለን›› ሲሉ የተከተሉትን መንገድ አጋርተውናል፡፡
አሁን ወ/ሮ ስንታየሁና ባለቤቷ በስልጠና ያገኙትን የቦርሳ አሰራር ሙያ ላይ የራሳቸውን ቅርጽና ውበት በመጨመር ለመስራት እየሞከሩ ነው፡፡ ለዚህም የመንግስት አካላት የመስሪያና መሸጫ ቦታዎችን በማመቻቸት ጥራቱን የጠበቀና ለሃገር ውስጥ ቱሪስቶች የሚመጥን ስራ እንድንሰራ ቢያግዙን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
More Stories
በሃሳብ የበላይነት ዘመን በጠብመንጃ ማሰብ
“መምህርነት ቅናትና ምቀኝነት የሌለበት ንጹህ ሙያ ነው” – መምህር አባተ ሐላሎ
“በጀት በፍትሀዊነት ካልተመራ በህዝቦች መካከል መተማመን ያሳጣል” – ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ