በሃሳብ የበላይነት ዘመን በጠብመንጃ ማሰብ
በኢያሱ ታዴዎስ
ከወዲህ በቴላቪቭ፣ ከወዲያህ በቴህራን፣ ደግሞም በጋዛ፣ በሌላ አቅጣጫ በዶሃ፤ ይህም ሳያንስ በኪዬቭ፣ ደግሞም በሞስኮ ሰማዮች ሚሳይሎች ሳያቋርጡ ይርመሰመሳሉ።
እነዚህን ሚሳይሎች የተመለከታቸው በየከተሞቹ የሚከበሩ ዓመታዊ ክብረ በዓላትን የሚያጅቡ የደስታ ርችቶች ነው የሚመስሉት። እንጂማ ማን ጦርነት ነው ብሎ ያምናል፣ ያውም በዚህ ዘመን?
የተፈራው ግን ሆኗል። ጠብመንጃ እየነገሰ የመጣ ይመስላል። የከባድ ጦር መሳሪያ አፈሙዞች በተጠንቀቅ ቆመው ባላንጣ ተብለው ወደ ተፈረጁት ተደቅነው የበላይ ትዕዛዝ መጠባበቅ ከጀመሩ ሰነባበቱ። ዓለም ከምንም በላይ የሚፈራው ከባዱ የኒውክሌር መሳሪያም እንዳይመዠረጥ ተሰግቷል።
ብቻ ሀገራት መላ ቅጣቸውን አጥተዋል። መሪዎችም የጥይት ባሩድ የጠጡ ይመስል ጦርነት ጦርነት ብሏቸዋል። የያዛቸው የጦርነት ዛር ከወዲህ ከወዲያ እያዳፋቸው ያለ አሳማኝ ምክንያት መሳሪያ እያስጨበጣቸው ጥይቱን በአናት በአናት ያስልካቸዋል።
በጥቅሉ አሁን የሚታየው የዓለማችን ሁኔታ ብዙም ደስ የሚያሰኝ አይደለም። አውሮፓ እና መካከለኛውን ምስራቅ የጦርነት ደመና በኃይል ተጭኖ እያስተዋልን ነው።
ከዓመታት በፊት ሩሲያ እና ዩክሬይን በመሳሪያ ታግዘው እንካ ቅመስ እየተባባሉ የጀመሩት ጦርነት እንደ ቀልድ ሲጀመር አሁን ድረስ ይዘልቃሉ ብሎ ማንም አልጠበቀም ነበር። ይኸው አሁን ከሶስት ዓመታት በላይ ሆናቸው። ይህ በእንዲህ ባለበት ሁኔታ ለዘመናት በባላንጣነት የዘለቁት እስራኤልና ሀማስ ድንገት ጦርነት ከፍተው መላውን ዓለም ድንጋጤ ውስጥ ከተቱ።
እነሱም አያመሩም ተብለው ቢጠበቁም ጭራሽ እያፋፋሙ ዓመት ከስድስት ወር ያህል ደም እየተቃቡ ዘልቀዋል።
ይህም ይሁን እሺ፣ ብቻ በዚህ ቢያበቃ እየተባለ ባለበት በዚህ ጊዜ ደግሞ ከወደ ደቡብ እስያ በባለፈው የፈረንጆቹ ግንቦት ወር (ከአንድ ወር በፊት) ሌላኛዎቹ ባላንጣ ጎረቤታሞች ህንድ እና ፓኪስታን እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው ጦር ተማዘዙ። እነሱም ድንገተኛ ጦርነት ውስጥ ገብተው ለጥቂት ጊዜም ቢሆን መላውን ዓለም አስደነገጡ።
የህንድ እና ፓኪስታን ግን እንደሌሎቹ ስር ሳይሰድ በተኩስ አቁም ስምምነት በአጭር ተቋጨ። ዳግም ይነሳ ይሆን? ጊዜ በሰሌዳው ላይ ያሰፈረው እውነታ ይፈታዋል። ግን አሁንም የጠብመንጃው ነገር በዚህ ሳያበቃ በሌላው መዘዝ ተከተለ።
ከሀማስ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብታ አልበርድ ያለችው እስራኤል በጎን ደግሞ ከኢራን ጋር ሌላ ጦርነት ከፍታ ፍልሚያዋን ቀጥላለች። እዚህ ጋር ነው እንግዲህ ሌላው ጉድ የተመዘዘው። እስራኤል ከኢራን ጋር አንዴ በማጥቃት ሌላ ጊዜ በመጠቃት ጦርነቱን እያፋፋመች ባለበት ቅጽበት ወዳጇ አሜሪካ ጣልቃ ገብታ ኢራን ላይ ጥቃት አደረሰች።
አሜሪካ ኢራን እየገነባች ያለውን የኒውክሌር ፕሮግራም እግረ መንገዴን ድምጥማጡን ላጥፋ በሚል ሰበብ ነው ጦርነቱን የተቀላቀለችው። ወትሮ ከአሜሪካ ጋር የጎሪጥ ስትተያይ የከረመችውም ኢራን የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች በሚገኙባቸው ኳታር እና ኢራቅ ድብደባ በማድረግ አጸፋዋን መለሰች። ጦርነቱ እግር በእግር እየተተካ ወደ ኳታር እና ኢራቅ ተስፋፋ ማለትም አይደል!
ለዚህም ኳታር በስጨት ብላ ሉዓላዊነቴ ተደፈረ ስትል በአደባባይ ጩኸቷን ማሰማቷ አልቀረም። እንደ ሳዉዲ አረቢያ ያሉ የኳታር ወዳጆች ደግሞ የኳታር መደፈር እኛንም ይመለከታል ሲሉ ጦርነት ውስጥ ለመግባት እያሟሟቁ ያሉ የሚመስል ዛቻ ለኢራን ልከዋል።
በሌላ ጎራ የኢራን ወዳጅ እንደ ሆነች የሚነገርላት ሩሲያ ወዳጇን አብራ እስራኤል እና አሜሪካንን ለመውጋት እያማተረች እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች እየገለጹ ይገኛሉ። ይህንን አቋሟን ሩሲያ በቀድሞ ምክትል የደህንነት መሪዋ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በኩል አስታውቃለች ተብሎ እየተነገረ ይገኛል።
በሜድቬዴቭ በኩል ይፋ የተደረገው ሩሲያን ጨምሮ ሌሎችም ደጋፊዎቿ ኢራንን ኒውክሌር ያስታጥቃሉ የሚል መልዕክት ያዘለ ነው። አሜሪካም በሜድቬዴቭ አስተያየት በርግጋ ከባድ አጸፋ እመልሳለሁ ስትል በፕሬዝደንቷ ዶናልድ ትራምፕ በኩል አስጠንቅቃለች።
ይህ በእንዲህ ባለበት ሁኔታ ራሷ አሜሪካ አሸማጋይ ሆና እስራኤል እና ኢራን ለጥቂት ጊዜያት ተኩስ እንዲያቆሙ ወትውታ ጦርነቱ አልፎ አልፎ ከመታኮስ ባለፈ ጋብ ያለ ይመስላል። ከሩቅም ከቅርብ የተናከሰችው እስራኤል ግን ይህን ዕድል ተጠቅማ አሁን ደግሞ ፊቷን ወደ ሀማስ አዙራ ጥቃት መሰንዘሯን ቀጥላለች።
ቀጠናውም ከምን ጊዜውም ይልቅ ውጥረት የሞላበት ሆኗል። በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ ሀገራት ከወዲሁ አሰላለፋቸውን በመለየት ራሳቸውን ለጦርነት ማዘጋጀቱ አይከፋም በሚል ስሜት በተጠንቀቅ ቆመዋል።
በየሀገራቱ ጣልቃ የምትገባው አሜሪካም ኃያልነቷን የምታሳይበትን አጋጣሚ ያገኘች ይመስል በጦርነት በሰከረ አባዜዋ ባላንጣዎቿን መተነኳኮሷን ቀጥላለች። እስራኤልን ወግና ኢራን ላይ ተነስታለች። ከወዲያ ደግሞ ዩክሬይንን በመደገፍ ሩሲያ ላይ የመነሳት ፍላጎት አላት።
ቻይና እና ሰሜን ኮሪያም በብርቱ የምትፈልጋቸው ጠላቶቿ እንደሆኑ ታምናለች። ኃያላኑ የአውሮፓ ሀገራትም ከዩክሬይን ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ምክንያት አድርገው ሩሲያ ላይ እንዳይነሱ ተሰግቷል።
ቻይና በበኩሏ ታይዋንን የራሷ ግዛት አድርጋ እንዳታስተዳድር ማነቆ የሆነችባትን አሜሪካ በዋዛ ፈዛዛ ትለቃለች ተብሎ አይታሰብም። ሰሜን ኮሪያም ከደቡብ ኮሪያ ጋር ለገባችበት የከረረ ጸብ አሜሪካ ጣልቃ የምትገባ ከሆነ አሜሪካንን ለማደባየት ቆርጣ ተነስታለች።
ብቻ ነገር ዓለሙ ሁሉ በጦርነትና ይዞ በሚመጣው ጣጣ ሰክሯል ማለት ይቻላል። ቀጣይ እርምጃ ግዙፉ ኒውክሌር ሊሆን እንደሚችል ሲታሰብ ደግሞ ዘግናኝ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ስጋት መደቀኑ አልቀረም።
ታዲያ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ዓለም የዘመናዊነትን ጥግ ባየበት በዚህ ጊዜ መሆኑ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ነው። ቴክኖሎጂው ረቅቆ፣ የሰው ልጅ አስተሳሰብ በልጽጎ፣ ልፋትን በርሆቦት በመተካት ቅንጡ ሕይወት ለመምራት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሳለ ጦርነት ይህንን የሚያፈርስ ተልዕኮ ሆኖ ብቅ ሲል ከመመልከት በላይ የሚገርም ነገር የለም።
ጦርነት በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ አብሮ ያለ ቢሆንም ይህንን ወቅት ግን የሚመጥን አይደለም። የሃሳብ ሉዓላዊነት ከምንም ነገር በላይ የሚቀድምበት ጊዜ ላይ ነንና። በእርግጥ ኃያላን መንግስታት አሁንም ቅድሚያ ሩጫቸው ጠንካራ ጦር ኃይል መገንባት ላይ ነው። ይህ ደግሞ ኒውክሌር መሳሪያን እስከመታጠቅ የሚደርስ ነው።
ይህ አካሄዳቸው አሁንም በጦርነት የማመን አባዜያቸው እንዳልተቀረፈ አመላካች ነው። ክፉ ጊዜ ከመጣ በጡንቻቸው ኃያልነታቸውን የማረጋገጥ ዓላማ አላቸው።
እንደ ግለሰብ ግን የሰው ልጅ አዕምሮ ከጠብመንጃ በላይ ማሰብ እንደሚችል ያረጋገጠበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው። እንደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ያሉ ታላላቅ ቴክኖሎጂዎች የሰው ልጆችን ደህንነት ከመጠበቅ በተጨማሪ ቅንጡ ሕይወት እንዲመሩ ያለሙ ናቸው። የዚያኑ ያህል የሀገራት የምጣኔ ሃብት ተመንድጓል፤ የማሰብም አቅም በእጅጉ አይሏል።
ይሄ ዘመናዊነት በፖለቲካውም ቢሆን ዓይነተኛ ሚና አለው። ሀገራት ከየትኛውም ጊዜ በላይ በመልካም ዲፕሎማሲ ያምናሉ። ይህም ማለት የትኛውም ልዩነት በጠረጴዛ ዙሪያ እንደሚፈታ ይታመናል። ከጠረጴዛ የሚያፈተልክ ጉዳይ አይኖርም።
ባስ ሲል ሀገራት እርስ በርስ፣ ካልሆነ ደግሞ እንደ ጸጥታው ምክር ቤት ባሉ ተቋማት ልዩነቶችን በመነጋገር ይፈታሉ። ለዚህም ነው ዘመኑ የሃሳብ ሉዓላዊነት የተረጋገጠበት ነው የሚባለው።
አሁን ግን በኃያላን ሀገራት ድንፋታ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኗል። ጠረጴዛው ቀርቶ ጠብመንጃው ወደ ፊት መጥቷል። ጦርነት እንደ ቀልድ የሚገባበት ዕቃ’ቃ ጨዋታ ሆኗል። ማስፈራሪያው ደግሞ ኒውክሌር። ይሄ የኃያላን ሀገራት መሪዎች የገቡበት የጦርነት ስካር ወደ ጠረጴዛው እስካልተመለሱ ድረስ የሚበርድ አይደለም።
አንዳንዶች ደግሞ የሶስተኛው የዓለም ጦርነት መንደርደሪያ አድረገው እየተመለከቱ ነው። ሃሳብን የመናቅ ትርፉ እንግዲህ ይኸው ነው። ለመንግስታቱ ልቦና ይስጣቸው! ምን ይባላል! ሶስተኛው የዓለም ጦርነት የተባለውንም ፈጣሪ ከመሆን ይከልክለው!
More Stories
“መምህርነት ቅናትና ምቀኝነት የሌለበት ንጹህ ሙያ ነው” – መምህር አባተ ሐላሎ
“በጀት በፍትሀዊነት ካልተመራ በህዝቦች መካከል መተማመን ያሳጣል” – ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ
ጨረቃ እና ሙዚቃ