የኬንያዊያኑ ክብረ ወሰን

የኬንያዊያኑ ክብረ ወሰን

በአንዱዓለም ሰለሞን

በዘንድሮ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ኬንያዊያን አትሌቶች ክብረ ወሰን ማሻሻል ችለዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በኢውጅን በተካሔደው ውድድር ኬንያዊቷ ቤትሪስ ቼቤት 13:58.06 በመግባት በ5ሺህ ሜትር ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን አሻሽላለች። ይህም ርቀቱን ከ14 ደቂቃ በታች በመሮጥ የመጀመሪያዋ አትሌት አስብሏታል፡፡

ከዚህ ቀደም ክብረ ወሰኑ ተይዞ የነበረው በኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ጸጋይ ሲሆን፣ አትሌቷ እ.ኤ.አ በ2003 በተመሳሳይ ውድድርና ስታዲየም ያስመዘገበችው ነበር፡፡ 14:00.21 በመግባት፡፡

ቼቤት ሪከርዱን ከሰበረች ከአንድ ሰዓት ተኩል ቆይታ በኋላ፣ ሌላኛዋ ኬንያዊት አትሌት ፌዝ ኪፕዬጎን ሌላኛውን መሰል ድል ለኬንያ አበርክታለች፡፡ አትሌቷ ያሻሻለችው የ1500 ሜትር ሪከርድን ሲሆን የገባችበት ሰዓትም 3:48.68 ነበር፡፡ ይህም በርቀቱ የራሷን የቀድሞ ክብረ ወሰን በ 036 ሰከንድ ያሻሻለችበት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

አትሌቷ በዳይመንድ ሊግ ውድድር በተለያዩ የውድድር ዓይነቶች የዓለምን ሪከርድ ለ5ኛ ጊዜ ስታሻሽል፣ ቼቤት በበኩሏ 2 ጊዜ ክብረ ወሰን መስበር ችላለች፡፡

ቤትሪስ ቼቤት ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው አስተያየት፡-

“ርቀቱን ከ14 ደቂቃ በታች ለመሮጥ የመጀመሪያዋ አትሌት በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ከሮም ውድድር በኋላ (14:03.69 ከገባችበት) የዓለም ክብረ ወሰንን ለማሻሻል በምችልበት ሁኔታ ላይ እንደምገኝ ተረድቼ ነበር” በማለት በውድድሩ ክብረ ወሰኑን ለመስበር ስለነበራት ተስፋ ተናግራለች፡፡

የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች በአሸናፊነት በሚታወቁበት በ5ሺህ ውድድር፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሻለ ሰዓት በማስመዝገብ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የተሻሉ ቢሆኑም፣ ኬንያዊቷ አትሌት ግን ርቀቱን ከ14 ደቂቃ በታች በመሮጥ የመጀመሪያዋ አትሌት ሆናለች፡፡

በርቀቱ ከዚህ ቀደም የተመዘገቡ 10 ምርጥ ሰዓቶችን ብንመለከት እንኳ፣ ለኔዘርላንድ የምትሮጠው ሲፋን ሀሰን በለንደን ኦሎምፒክ 14፡13.42 በመግባት ካስመዘገበችው ድል ቀጥሎ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከ2008 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት በርቀቱ ባስመዘገቡት ጥሩ ሰዓት የበላይነቱን ይዘዋል፡፡

እጅጋየሁ ታዬ በ2022 14፡12.98 በመግባት ስታሸንፍ፣ በ2008 መሰረት ደፋር 14፡12.88፣ አልማዝ አያና በ2016 14፡12.59፣ ጥሩነሽ ዲባባ በ2008 14፡11.15፣ ለተሰንበት ግደይ በ2020 14፡06.62 በመግባት አሸንፈውና የተሻለ ሰዓት አስመዝግበው በርቀቱ የኢትዮጵያን የበላይነት አስጠብቀው ቆይተዋል፡፡

የኬንያዊያኑ ድል የሚመጣው ከዚህ በኋላ ነበር፡፡ በ2023 በፈረንሳይ ፓሪስ በተደረገው ውድድር ፌዝ ኪፕዬጎን 14፡05.20 በመግባት የተሻለ ሰዓት በማስመዝገብ ስታሸንፍ፣ በ2005 ደግሞ አጀንስ ጀቤት 14፡01.29 በመግባት አሸንፋለች፡፡

በወርሀ መስከረም 2023 በዚያው በአሜሪካ በተመሳሳይ ከተማ በተደረገው ውድድር፣ ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ጸጋይ 14፡00.21 በመግባት አሸንፋ ድሉን ዳግም ወደ ኢትዮጵያ መልሳው ነበር፡፡ ይህ በሁለቱ ሀገራት አትሌቶች መካከል የሚደረገው ፉክክር ቀጥሎ፣ እነሆ ኬንያዊቷ አትሌት ከሁለት ዓመት በኋላ በርቀቱ ምርጡን ሰዓት ያስመዘገበችበትን ውጤት ለማግኘት በቅታለች፤ ርቀቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ከ14 ደቂቃ በታች በመሮጥ፡፡

በ2024 የፈረንሳይ ኦሎምፒክ በ5 እና 10 ሺህ ሜትር አሸናፊ የሆነችው የ 25 ዓመቷ ቼቤት፣ 10ሺህ ሜትርን ከ29 ደቂቃ በታች በመሮጥ (28፡54፡14) የመጀመሪያዋ አትሌት መሆኗ የሚታወስ ነው፡፡ ይህም የሆነው በአሜሪካዋ ኢውጅን ነበር፡፡ በወቅቱ ውድድሩን አስመልክታ በሰጠችው አስተያየትም እንዲህ በማለት ተናግራ ነበር፡-

“በኢውጅን ያደረኩት የ10ሺህ ሜትር ውድድር ለኦሎምፒክ ውድድር የሚያበቃኝን ሰዓት ለማግኘት ነበር፡፡ ከዚያ ባሻገር ምናልባትም የሀገሬን ክብረ ወሰን አሻሽል ይሆናል እንጂ የዓለምን ሪከርድ እሰብራለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡”

አስተያየቷን ስትቀጥልም፡-

“የዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድርን ካሸነፍኩና ይህን የዓለም ክብረ ወሰን ካሻሻልኩ በኋላ፣ የተለየሁ አትሌት መሆኔን ተገነዘብኩ፤ በጥሩ ሁኔታ የምሮጥ፣ የተሻለና የሚያስደንቅ ስራ የምሰራ” በማለት ስለራሷ ተናግራለች፡፡

በእርግጥም ይህ ብዙ ጊዜ የተናገረችውን በተግባር በሜዳ ላይ ለምታሳየው፣ በመጨረሻዎቹ ዙሮች ከተፎካካሪዎቿ ተነጥላ በመውጣት በድንቅ የአጨራረስ ብቃቷ ለምትታወቀውና “ሳቂታዋ ገዳይ” የሚል ቅጽል ስም ለወጣላት ቼቤት የሚበዛባት አይሆንም፡፡

ኬንያ የምትታወቅበት የሻይ ቅጠል ከሚበቅልባቸው የኬሪቾ ኮረብታዎች አካባቢ የተገኘችው አትሌቷ፣ በእርግጥም ገና በወጣትነቷ ነበር በአትሌቲክሱ ውጤታማ ለመሆን እንደምትችል የተረዳችው፡፡ የሌምቲት አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ካምፕን ስትቀላቀል ደግሞ በእርግጥም ለሩጫ እንደተፈጠረችና ሩጫም የወደፊት እንጀራዋ እንደሚሆን ተገነዘበች፡-

“ከሴት አያቴ ጋር ነበር የምኖረው። ወደ ማሰልጠኛው የወሰደችኝም እሷ ነበረች። በብዙ መልኩ ድጋፍ ታደርግልኝና ውጤታማ እንድሆን ትጸልይልኝ ነበር” የምትለው ቼቤት፣ ይህ መሆኑ መነቃቃትን እንደፈጠረላት፣ ስኬታማና አንጸባራቂ አትሌት እንደምትሆን ለራሷ እንድትነግረው እንዳደረጋት ትገልጻለች፡፡

ወደ 1500 ሜትሩ ውድድር ስንመጣ፣ በውድድሩ የኪፕዬጎን የአጨራረስ ብቃት ልዩ ነበር፡፡ ውድድሩን 3:51.44 በመፈጸም በሁለተኛነት ካጠናቀቀችው ከኢትዮጵያዊቷ ድርቤ ወልተጂ በ 3 ሰከንድ ልዩነት መግባት ችላለች፡፡ የኦሎምፒክ የነሀስ ሜዳሊያ ባለቤቷ ጆርጂያ ሀንተር ቤል ደግሞ 3:54.76 በመግባት በሶስተኛነት ፈጽማለች፡፡

ኬንያዊቷ አትሌት ውድድሩን ክብረ ወሰን በመስበር ካሻሻለች በኋላ በሰጠችው አስተያየት፣ ድሉ ባለማቋረጥ በሰራችው ልምምድ፣ በአሰልጣኟ፣ በማናጀሯና በሌሎችም ድጋፍ የተገኘ መሆኑን በመጠቆም ምስጋናዋን አቅርባለች፡፡ ከዚህ ባሻገርም፤ ወጣቶችና ሴቶች ህልማቸውን እውን ለማድረግ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስባለች፤ “ሁሉም ነገር ይቻላል” በማለት፡፡