“መምህርነት ቅናትና ምቀኝነት የሌለበት ንጹህ ሙያ ነው” – መምህር አባተ ሐላሎ
በአብርሃም ማጋ
የዛሬው ባለታሪካችን መምህር አባተ ሐላሎ ይባላሉ፡፡ በመምህርነት ሙያ ለበርካታ አስርት ዓመታት ዘልቀዋል፡፡ ሙያውን በእጅጉ ይወዱታል። ለዚህም ነው ከላይ በርዕሱ የተጠቀሰውን ሃሳብ ያጋሩን፡፡ በተጨማሪም መምህርነት አኩሪና ታላቅ ሙያ መሆኑን በመግለፅ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ፡፡
መምህርነት የዓለም ማያ መነፅር በመሆኑ ትልቅ ክብር የሚሰጡት ሙያ እንደሆነም በአድናቆት ይገልፃሉ፡፡ ከዚህ ውጭም መምህርነት የሰዎች ሥራ ብቻ ሳይሆን የፈጠራ ተግባር ነው ሲሉም አቶ አባተ ይገልፃሉ፡፡
መምህር አባተ ሐላሎ በቀድሞው ሸዋ ጠቅላይ ግዛት በከምባታና ሐዲያ አውራጃ ሶሮ ወረዳ፣ በኡርባጫ ቀበሌ በ1926 ዓ.ም ነበር የተወለዱት። ዛሬ ላይ 91ኛ ዕድሜያቸው ላይ ይገኛሉ፡፡ የትውልድ ዘመናቸውን ያረጋገጡት ከማይጨው ጦርነት ጋር በማመሳከር ነው፡፡
በልጅነታቸው እስከ 16 ዓመታቸው ድረስ ከብቶች እያገዱና እርሻ እያረሱ አድገዋል። በ1942 ዓ.ም ላይ በሆሳዕና ከተማ የቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ለአንድ ዓመት ተምረዋል፡፡
በ1943 ዓ.ም ደግሞ የእንግሊዝ (ራስ አባተ ተብሎ በሚጠራው) ት/ቤት ገብተው በአንድ ዓመት ውስጥ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል፡፡ በወቅቱ በገና፣ በፋሲካ፣ በሰኔ ወቅቶች ውስጥ በሚኖሩ የዕረፍት ጊዜያት ከአንድ ወደ ቀጣዩ ክፍል የመዛወር ዕድሎች በመኖራቸው ነበር በዓመት ውስጥ 4ኛ ክፍል ለማጠናቀቅ የበቁት፡፡
በ1944 ዓ.ም በሁለተኛ ዓመት 5ኛ ክፍል ቢደርሱም ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመልሰው የከብቶች ጠባቂ /እረኛ/ ሆኑ፡፡ 5 ዓመት ሙሉ ትምህርታቸውን አቋርጠው በእረኝነት ቆይተዋል፡፡ በእረኝነት እንዲሰማሩ ያደረጋቸው ቤተሰቦቻቸው ሌላ ወንድ ልጅ ስላልነበራቸውና ከቤት ብቸኛ ወንድ ልጅ በመሆናቸው ነበር፡፡
ቤተሰቦቻቸው ልጃቸው እርሻ እያረሱና ከብት እያገዱ አድገው ትዳር ይዘው ልጆች እንዲወልዱላቸው በመገመት ነበር ተዕፅኖ የፈጠሩባቸው፡፡
በዚሁም ፊደል ያልቆጠረ ልጅ መስለው ሸማቸውን ቅቤ ቀብተው ሙሉ ለሙሉ የገጠር ሰው ሆነው ነበር፡፡ የእረኝነትን ተግባር ያከናወኑት።
ከ5 ዓመታት በኋላ ከካቶሊክ ሚስዮኖች ሥር የተከፈቱ ት/ቤቶች በአካባቢው መስፋፋት ይጀምራሉ፡፡ በመሆኑም ትምህርት አቋርጠው በእረኝነቱ ሥራ መሠማራታቸው በእጅጉ ቆጭቶአቸው ትምህርታቸውን ለመማር ይወስናሉ፡፡
በውሳኔያቸው መሠረት በከምባታ ውስጥ ዋሣራ ቅድስት ትሬዛ በካቶሊክ ሚሲዮን ቤተ ክርስቲያን ሥር በተከፈተችው ት/ቤት ለመማር ሲሄዱ ት/ቤቱ ፈተና ሰጥቶ ዕውቀታቸውን ገምቶ 3ኛ ክፍል ያስገባቸዋል። የ3ኛ ክፍል የገቡት በ1951 ዓ.ም ሲሆን ከ3ኛ እስከ 5ኛ ክፍል በአንድ ዓመት ውስጥ ተምረው ያጠናቅቃሉ፡፡
ከተወለዱበት አካባቢ ከሐዲያ ተጉዘው በከምባታ ውስጥ ተመላልሰው መማር ስለማይችሉ ት/ቤቱ መጠለያ ሰጥቶአቸው እያደሩ ነበር የተማሩት፡፡
በክረምት ወደ 6ኛ ክፍል እንደተዛወሩ ህመም አጋጥሞአቸው በሚስዮኖቹ አማካይነት ለህክምና ሐረር ተወሰዱ፡፡ ከሐረር ከተማ 6ዐ ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ በሚያስገባ አካባቢ ነበር የካቶሊክ ቤተክርስቲያንና ት/ቤት የነበረችው፡፡
በወቅቱ ህክምና ሳይወስዱ ተሽሎአቸው የቤተክርስቲያኑዋ ቄስ ከነበሩት ከአንድ ጀርመናዊ ቄስ ጋር ለሁለት ወራት እዛው ያሳልፋሉ፡፡
በመጨረሻም ከሁለት ወር ቆይታ በኋላ ወደ “ዋሰራ” ከመመለሳቸው አስቀድመው በሐረር ከተማ ልዑል መኮንን ሆስፒታል ተመርምረው ምንም የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ ተረድተው ነበር፡፡ በሐረር ቆይታቸው የተለያዩ የመማሪያ መድሐፍትን በማንበብ የተሻለ ዕውቀት ለመጨበጥ በቅተዋል፡፡
በዚሁም ወደ ዋሰራ ሲመለሱ ሐረር የነበረው ቄስ የትምህርት ችሎታቸውን መዝነው 7ኛ ክፍል መማር እንደሚችሉ አረጋግጠው የሰጧቸውን ደብዳቤ ይዘው ነበር፡፡ ከጉብዝናቸውም የተነሳ የ6ኛ ክፍል ትምህርት ሳይማሩ 7ኛ ክፍል እንዲገቡ ተደረጉ፡፡ 6ኛ ክፍል መማር እንደሚፈልጉ ለት/ቤቱ ቢገልፁም ተቀባይነት ሳያገኝ ይቀራል፡፡
በወቅቱ የ7ኛ ክፍል ተማሪ እያሉ የ4ኛ ክፍል የአማርኛ መምህር ባለመኖሩ እሳቸው ተመድበው ያስተምሩ ነበር፡፡ በ1952 ዓ.ም በዋሰራ ካቶሊክ ት/ቤት 8ኛ ክፍልን አጠናቅቀው በብሔራዊ ፈተና ጥሩ ውጤት በማምጣት ወደ 9ኛ ክፍል ተዛወሩ፡፡
ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የተማሩት በናዝሬት ከተማ አፄገላዲዎስ ት/ቤት ሲሆን ለት/ቤቱ የመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች ነበሩ። ናዝሬት በሚማሩበት ወቅት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቤት ተከራይቶላቸው ነበር። በሌላ በኩል መንግሥትም በወር 2ዐ ብር ድጐማ ይከፈላቸውም ነበር፡፡
በወቅቱ ሙሉ ወጭው በወር ከ9 ብር አይዘልም ነበር፡፡ እናም በወር 11 ብር ይተርፋቸው ስለነበር እያጠራቀሙ ልብስና ጫማ እየገዙ ይለብሳሉ፡፡
በ1956 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ሲያጠናቅቁ ለዲፕሎማና ለድግሪ የሚያበቃ ውጤት አልመጣላቸውም ነበር፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ በነበረው ከፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
በዚሁም በ1957 ዓ.ም ውጤት ያልመጣላቸውን ሁሉ የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገብተው እንዲሰለጥኑ ይጋብዛል፡፡
በመሆኑም በተጠቀሰው ዓመተ ምህረት እሳቸው የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነው በአዲስ አበባ በነበረው መምህራን ማሰልጠኛ ገብተው የአንድ ዓመት ኮርስ አጠናቅቀው በሰርተፊኬት ተመርቀዋል፡፡
ከዚያም ዕጣ አውጥተው በወቅቱ የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት፣ ጌዴኦ አውራጃ ጨለለቅቱ ት/ቤት ተመደቡ፡፡ በትምህርት ቤቱ ከ1958 እስከ 196ዐ ዓ.ም ለ3 ዓመታት ያህል በአክቲንግ ዳይሬክተርነት ሠርተዋል፡፡
ከዚህም በመቀጠል በነበራቸው ሥራ ብቃት ተመዝነው በትምህርት አስተዳደር የትምህርት ዕድል ተሰጥቶአቸው በአዲስ አበባ ለአንድ ዓመት ተከታትለው በሙሉ ርዕሰ መምህርነት ተመርቀዋል፡፡
በዚህም በ1962 ዓ.ም ካሳበር /በአሁኑ ሐቤላ /ጊደ/ ተብሎ በሚጠራው ት/ቤት ዋና ርዕሰ መምህር ሆነው ለአንድ ዓመት ሠርተዋል፡፡
ትምህርት ቤቱን በተገቢው ሁኔታ በመምራታቸው ዕድገት አግኝተው በ1963 ዓ.ም ወላይታ አውራጃ ቦዲቲ 1ኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ዋና ር/መምህር ሆነው ለ4 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡
በወቅቱ በት/ቤቱ መንግሥት የወረሰው ቤት በመኖሩ ከሩቅ ከገጠር መጥተው የሚማሩ ተማሪዎች እንዲያድሩበት ሰጥተዋቸው የት/ቤቱን ውስጣዊና ውጫዊ ገፅታዎችን በመቀየር ግንባር ቀደም ተግባር አድርገው ምቹ አካባቢን ፈጥረዋል።
ግቢውን ከማሳጠር በተጨማሪ የተለያዩ ማራኪ አበቦችንና ለጥላ የሚሆኑ ዛፎችን አስተክለው ት/ቤቱ ውበት እንዲጐናፀፍ አድርገዋል፡፡
ውስጣዊ ይዘቱን በተመለከተ የተማሪዎችንና የመምህራንን ግንኙነትን በማጠናከርም የመምህራንን ሚና ከፍ አድርገዋል፡፡ እያንዳንዱ መምህር ሀላፊነት ኖሮት በትምህርት ሥራ ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጥበትን ሁኔታ አመቻችተዋል፡፡
የራሳቸውን ሙሉ ስልጣን ለመምህራን አከፋፍለው በመስጠት ላቅ ያለ ሚና እንዲጫወቱ አድርገዋል፡፡ መምህራንን መጉዳት በፍጹም እንደማይወዱና ጐድተው እንደማያውቁም አብራርተዋል፡፡
በ1966 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ወደ ሐዋሳ ታቦር 1ኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተዛውረው በዋና ር/መምህርነት እስከ 1971 ዓ.ም ድረስ ለ5 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡
በ1972 ዓ.ም በሐዋሳ ታቦር አጠቃላይ ሁለተኛ ከፍተኛ ደረጃ ት/ቤት በአስተዳዳሪነት ተመድበዋል፡፡ የት/ቤቱን አበባ እና ዛፎች ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተከሉ ሲሆን ት/ቤቱ ውበት እንዲኖረው ላቅ ያለ ሚና ተጫውተዋል፡፡
በመቀጠልም በት/ቤቱ የሪከርድ ክፍል ኃላፊ ሆነው እስከ 1991 ዓ.ም ካገለገሉ በኋላ በጡረታ ተገልለዋል፡፡ የሪከርድ ኃላፊ ሆነው በሠሩባቸው ጊዜያት የፀዳ አሠራርን በመዘርጋት የተለያዩ ብልሹ ተግባራትን አስቀርተዋል፡፡
ተማሪዎች በሠሩት ልክ ውጤታቸውን እንዲያገኙ አስደርገዋል፡፡ የሙስና ተግባራትንም አስቀርተው የተሻለ አፈፃፀም በት/ቤቱ እንዲኖር አድርገዋል፡፡ ጡረታ ከወጡ በኃላ በንጋት የህፃናት ት/ቤት ተቀጥረው ለሁለት ዓመታት ያህል በርዕሰ መምህርነት አገልግለዋል፡፡
በ1994 ዓ.ም በሰንሻይን ት/ቤትም በርዕሰ መምህርነት ሰርተዋል፡፡ ይህ ትምህርት ቤት መምህራን በማህበር ተደራጅተው የከፈቱት ሲሆን በአሁኑ ወቅት እስከ 12ኛ ክፍል እንደሚያስተምር ያብራራሉ፡፡ ከትምህርት ቤቱ ባለቤቶች አንዱ እሳቸው እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ለሥራ ያላቸውን ፍቅር ሲገልፁ ሥራ የህይወታቸው መሠረት መሆኑን ጠንቅቀው በመረዳት ሁሌ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይሉ በፍቅር እንደሚሠሩ ይናገራሉ፡፡ በትምህርት ሥራ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ የማስተባበር ችሎታቸውን ተጠቅመው ሁሌ ውጤታማ እንዲሆኑ ካደረጋቸው ነገሮች አንዱ ከፍተኛ የሥራ ፍቅር መጐናፀፋቸው እንደሆነም ያብራራሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም መምህር አስተማሪ ብቻ ሳይሆን አባትም በመሆኑ እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል “መምህርነት በእጅጉ የሚያስደስተኝ ሙያ ነው” ሲሉ የተደመጡት። “መምህር ግድ የለሽ አይደለም፤ ራሱን አሳልፎ የማይሰጥ ጥንቁቅ ነው” በማለትም ለመምህር ያላቸውን ፍቅር ይገልፃሉ፡፡
“በእምነትም በጣም አክራሪ መሆኔ ልዩ ባህሪዬ ነው” በማለትም ስለራሳቸው ይገልፃሉ፡፡ አቶ አባተ ሐላሎ በ1959 ዓ.ም ወደ ትዳር ዓለም ገብተዋል፡፡ የ5 ወንድ እና የ6 ሴት በድምሩ የ11 ልጆች አባት ናቸው፡፡
ታዲያ ዛሬ ላይ በሐዋሣ ከተማ ልጆቻቸውን አስተምረው ለቁም ነገር ከበቁ አባቶች አንዱ ናቸው፡፡ ልጆቻቸውን ከመቅጣት ይልቅ መክረው በማሳደግ ጥሩ መስመር ይዘው እንዲማሩላቸው በማድረግ ሁሉንም ውጤታማ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡
በዚህ መሠረት ሁሉም ከመጀመሪያ ድግሪ በላይ ናቸው፡፡
ልጆቻቸውም ዶ/ር ሀሊማ አባተ የመድን ድርጅት ኃላፊ፣ ዶ/ር በረከት አባተ በአሜሪካ ሀገር ነዋሪ፣ ዶ/ር ቢኒያም አባተ በአሜሪካ የሚኖር፣ የመጀመሪያ ልጃቸው ተስፋዬ አባተ በወንጌላዊነት የሚያገለግል ሲሆን በመጽሃፍ ቅዱስ ትምህርት ከሁለተኛ ድግሪ በላይ ተምሮአል፡፡
አንዱ ልጃቸው ደግሞ በህግ ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቆ በሐዋሳ ንግድ ባንክ ውስጥ ይሠራል፡፡ ራሔል አባተ በኤች ኦ በጤና ትምህርት በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቃለች፣ ዮሱፍ አባተ የተባለው ልጃቸው የኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ መሐንዲስ ነው፡፡
ዘቢባ አባተ በላብራቶሪ በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቃለች፤ ሮዛ አባተ በኢመርጀንሲ ትምህርት ሁለኛ ድግሪ አላት፡፡ ምስጋና አባተ በሶሾሎጂ ትምህርት የመጀመሪያ ድግሪ፣ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ትምህርት ሁለተኛ ድግሪ አላት፡፡ ብሩኬ አባተ የተባለች ልጃቸው ደግሞ በሁለተኛ ድግሪ ተመርቃ በቢልጌት ግብረሰናይ ድርጅት ውስጥ ሃላፊ ሆና ትሠራለች፡፡
More Stories
በሃሳብ የበላይነት ዘመን በጠብመንጃ ማሰብ
“በጀት በፍትሀዊነት ካልተመራ በህዝቦች መካከል መተማመን ያሳጣል” – ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ
ጨረቃ እና ሙዚቃ