“በጀት በፍትሀዊነት ካልተመራ በህዝቦች መካከል መተማመን ያሳጣል” – ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ

የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ ናቸው፡፡ ቢሮው በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሰረት ስላከናወናቸው ተግባራት እንዲሁም በክልሉ እየተከናወኑ ባሉ የልማት እና መልካም አስተዳደር ተግባራት ዙርያ ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ

በደረጀ ጥላሁን

ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

/ ወሰነች፦  እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፦ ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ምን ይመስላል?

/ ወሰነች፦ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከተመሰረተ አራት አመት የሆነው ሲሆን በእነዚህ ጊዜያት በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል፡፡ በየጊዜው እየጨመረ ከመጣው የህዝብ ብዛት ጋር ተያይዞ እያደገ የመጣውን የመልካም አስተዳደር፣ የንጹህ የመጠጥ ውሃ እና ሌሎች የመሰረተ ልማት አቅርቦትን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

በክልላችን የህብረተሰቡ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሚወስንበትና የልማት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ለማመቻት ክልሉ የአስር አመት የልማት “የፍኖተ ብልጽግና እቅድ” በማዘጋጀት ወደ ትግበራ የተገባ ሲሆን የህዝቡን ተሳትፎ በመጠቀም የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶችን ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በዚህም ውስን የሆነውን የክልሉን ሀብት በዋናነት ድህነትን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስና የህዝብ ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጡ የልማት ተግባራት እንዲመደብ በማድረግ የክልሉን ቀጣይነት ሊያረጋግጥ በሚችል የእድገት ጉዞ ውስጥ እንዲገኝ እየተሰራ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ የ2022 ፍኖተ ብልጽግና ዓላማን የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ ተወዳዳሪ የሆነ፣ ለኑሮ ምቹና የመልካም አስተዳደር ተምሳሌት የሆነ ክልል የመፍጠር እንዲሁም ለኑሮና ለኢንቨስትመንት በሀገር ደረጃ ተመራጭ ክልል ለማድረግ የሚያስችል የ10 አመት የልማት እቅድ በማዘጋጀት ለተግባራዊነት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

ንጋት፦ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ተግባሩን እንዴት እየተወጣ ይገኛል

/ ወሰነች፦ ቢሮው የክልሉን ራዕይ እውን ለማድረግ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሰረት አጋዥ ሚና የሚጫወት ነው፡፡ በዚህ መሰረት ሴክተሩ ውስን የሆነውን የክልሉን ሀብት ድልድል ከክልሉ የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እና የትኩረት አቅጣጫዎች ጋር ይበልጥ ለማስተሳሰር የበጀት ዝግጅቱን ከአንድ አመት እይታ ወደ መካከለኛ ዘመን እይታ በማሸጋገር ክልሉ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች ትኩረት በማድረግ እየሰራ ነው፡፡ ለዚህም በየዘርፉ የሚተገበሩ ፕሮግራሞች ወጥነት እንዲኖራቸው በማድረግ አስፈላጊውን የመሰረተ ልማትና መሰረታዊ አገልግሎት በተፋጠነ ሁኔታ ለማቅረብ የሚያስችል ሥርዓት የመዘርጋት ሂደት በተጠናከረ መልኩ እያካሄደ ይገኛል፡፡

ከዚህ አኳያ ክልሉ ከተቋቋመ ወዲህ የክልሉ መንግስት ፋይናንስ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እድገት እያሳየ የመጣ ሲሆን በ2014 ዓ/ም ብር 9 ነጥብ 34 ቢሊየን ከነበረበት የክልሉ የመንግስት በጀት በ2017 ዓ/ም ወደ ብር 19 ነጥብ 8 ቢሊዮን አድጓል፡፡ ይህ የፋይናንስ ፍላጎት ባለፉት አራት አመታት ከ2014 እስከ 2017 ዓ/ም በአማካይ በዓመት የ 28 ነጥብ 38 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡

ንጋት፦ በክልሉ የሚሰበሰበው የገቢ እድገት እንዴት ይገለፃል?

/ ወሰነች፦ በክልላችን የሚሰበሰብ ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ነው፡፡ በዚህ መሰረት በ2014 ዓ/ም ብር 3 ነጥብ 14 ቢሊዮን ከነበረበት በ2017 ዓ/ም መጨረሻ ወደ 10 ነጥብ 44 ቢሊዮን እንደሚያድግ ተገምቷል፡፡

ባለፉት አራት አመታት በክልሉ የተሰበሰበው ገቢ ከክልሉ ጠቅላላ በጀት ጋር ሲነፃፀር በ2014 በጀት ዓመት 33 ነጥብ 69 በመቶ፤ በ2015 በጀት ዓመት 42 ነጥብ 32 በመቶ እና በ2016 በጀት ዓመት 45 ነጥብ 43 በመቶ ድርሻ የያዘ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመት ይሰበሰባል ተብሎ የተገመተው ደግሞ የ 59 ነጥብ 25 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡

ከ2014 ዓ/ም ጀምሮ እስካሁን በአራት ዓመት የተሰበሰበው ገቢ በአማካይ በዓመት የ 51 ነጥብ 50 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ እድገቱ የተመዘገበው በክልሉ በሁሉም የገቢ ዓይነቶች ሲሆን የአምስት አመቱ አማካይ እድገት ሲታይ ከቀጥታ ታክስ 41 ነጥብ 3 በመቶ፣ ቀጥታ ካልሆኑ የታክስ ገቢዎች 64 ነጥብ 9 እንዲሁም ታክስ ያልሆኑ ገቢዎች ደግሞ 70 ነጥብ 3 በመቶ እና የማዘጋጃ ቤቶች ገቢ 61 ነጥብ 1 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ባለፉት አራት አመታት የክልሉ ገቢ እድገት ክልሉ ከመመስረቱ በፊት ከነበረበት እድገት በተሻለ ሁኔታ እየጨመረ እንደመጣ ለመገምገም ተችሏል፡፡

ንጋት፦ በሚሰበሰበው ሀብት በዋናነት ምን ተግባራት ተከናወኑ?

/ ወሰነች፦ በሚሰበሰበው ሀብት በክልሉ በርካታ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተግባራት በተሻለ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ከነዚህም ውስጥ በዋናነት ክልሉ ከተቋቋመ ወዲህ በነባሩ ክልል ተጀምረው ያልተጠናቀቁ፣ በጅምር የቀሩና ለመልካም አስተዳደር ችግር ሲሆኑ የነበሩ በርካታ ፕሮጀክቶችን በተለይም ወደ መጠናቀቅ ለደረሱ ፕሮጀክቶች የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት እየተጠናቀቁ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በጤና ዘርፍ ሆስፒታሎች ለምሳሌ ካካ ሆስፒታል፣ ማሻ ሆስፒታል፣ ቦንጋ ደም ባንክ እና ጤና ጣቢያዎች እየተጠናቀቁ ለማህበረሰቡ አገልግሎት እዲሰጡ ማድረግ ተችሏል፡፡ የመጠጥ ውሃ በተመለከተ ብዙ የውሃ ፕሮጀክቶች ተገንብተውና ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል፡፡ በመንገድ ዘርፍም በርካታ ድልድዮች፣ መንገዶች እንዲሁም በነባሩ ክልል ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የታርጫና ሚዛን መናኸሪያዎች፣ ክልሉ ከተመሰረተ በኋላ የተጀመረ የቦንጋ መናኸሪያን ጨምሮ ሶስት መናኸሪያዎች ተገንብተው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በቀጣይም ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በተቻለ መጠን መጠናቀቅ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ንጋት፦ የበጀት ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ የተሰራው ሥራ እንዴት ይገልጹታል?

/ ወሰነች፦ በጀት በፍትሀዊነት ካልተመራ በህዝቦች መካከል መተማመን ያሳጣል፡፡ ከዚህ አንፃር ፍትሀዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የሚገኘውን ገቢ በሚለካ መልኩ በእያንዳንዱ ዞንና ወረዳ ድረስ በተዋረድ ተደራሽ ይደረጋል፡፡

ከፌደራል የሚገኝ ድጎማ /ትሬዤሪ/ ለማከፋፈል የሚያስችል ሥርዓት ዘርግተናል።ይህም በብሄረሰቦች ምክር ቤት የህዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የቀመር ሥራዎች በክልሉ ተሰርቷል፡፡ በዚህ መሰረት በብሄረሰቦች ምክር ቤት የቀረበውን ቀመር መሰረት በማድረግ የምናገኘውን የድጎማ በጀት ለዞኖች እናከፋፍላለን፡፡ ቀመሩ ፍትሀዊነትን ከማረጋገጥ አንፃር ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከሌሎች ረጂ ድርጅቶች የምናገኘውን ሀብት ይህን ቀመር መሰረት በማድረግ ነው የምንሰራው፡፡

በክልሉ የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ተግባሮች በውሃ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርናና ለመሳሰሉ እድገት ተኮር ለሆኑ ተግባራት በተመሳሳይ የሀብት ተደራሽነት እንዲኖር ነው የምንሰራው፡፡ ይህም ከፍተኛ እርካታ ያስገኘ አሰራር ነው፡፡

ንጋት፦ በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ለማረጋገጥ የተዘረጋ የቁጥጥር ሥርዓት ምን ይመስላል?

/ ወሰነች፦ የክልሉ ምክር ቤት እያንዳንዱን የበጀት አፈፃፀም እንዲሁም የተመደበው በጀት በምን ላይ እንደዋለ በቋሚ ኮሚቴ በኩል የሚፈተሽበት አሰራር አለ፡፡ ጉድለት ካለ እንዲስተካከል ብሎም ተጠያቂነትን የሚያስከትል አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራ ነው፡፡

ሌላው በእያንዳንዱ ፕሮጀክት አፈፃፀም የሚደረግ የክትትልና ድጋፍ አሰራር አለ። የተመደበው በጀት ወደ ተግባር መግባቱን የማረጋገጥ ሥራ ይሰራል፡፡ ፊሲካልና ፋይናንሻል አፈፃፀም የሚለው በተደራጀ እና በተቀናጀ መልኩ ከክልሉ ፕላን ኮሚሽን ጋር ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል፡፡ ይህም የዘገዩ ፕሮጀክቶችን ከመፈጸም አንፃር እና በጀቱ በአግባቡ ሥራ ላይ ስለመዋሉ መከታተል የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በፋይናንስ ቢሮም የውስጥ ቁጥጥር ሥራዎችን በማጠናከር በጀት በተመደበው ዓይነት በተግባር መዋሉን የመከታተል ሥራ ይሰራል፡፡

ንጋት፦ የፋይናንስ አሰራሩን ከማዘመን አኳያ የተሰራ ሥራ ካለ ቢገልጹልን?

/ ወሰነች፦ አሰራራችንን ዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግ አስፈላጊና ሥራን ለማቅለል እገዛው ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህም የፋይናንስ አሰራርን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የሚያስችል አሰራር አለን፡፡ በተለይም የበጀት ሲስተም፤ አይቤክስና ሌሎች የፋይናንስ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ አስደግፈን እየሰራን ነው። ይህንንም የበለጠ ለማጠናከር እየሰራን ነው። በቀጣይ የኤሌክትሮኒክስ የግዢ ዘዴ ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡ ይህም ብዙ ሀብትና የሰው ሀይል የሚፈልግ በመሆኑ በፌደራል መንግስት ድጋፍ እና በተባባሪ አካላት የተለያዩ ሥልጠናዎች በመስጠት የባለሞያዎች አቅም እንዲጎለብት እየተደረገ ነው፡፡

ለአብነትም አሰራራችንን ዘመናዊ ለማድረግ በተለይ የገንዘብ ሚንስቴር ከፍተኛ እገዛ እያደረገልን ነው፡፡ ለፋይናንስ ሥራችን ከፍተኛ እገዛ የሚያደርጉ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን በማቅረብ እና የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎች በመስራቱ ምስጋና ይገባዋል።

ንጋት፦ በየተቋማቱ በግዢ ሥርዓት ላይ ቅሬታዎች ሲነሱ ይደመጣሉ፡፡ ይህን ለመቅረፍ ምን እየተሰራ ነው?

/ ወሰነች፦ በእርግጥ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የግዢ ሥርዓቱ ላይ የተለያዩ ቅሬታዎች ሲነሱ ይስተዋላል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ሥራዎች ይሰራሉ። ቢሮው የግዢ ሥርዓቱን በትክክለኛው መንገድ እንዲሄድ ከፌደራሉ ጋር የተናበበ አዋጅ አውጥተን እየሰራን ሲሆን፤ ከአዋጁ ጋር ተያይዞ የግዢ መመሪያ እና የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ እየተሰራበት ነው። እንደሚታወቀው ለግዢ ብዙ ሀብት ይፈሳል። የእቃ ግዢ፣ የአገልግሎት ወይም የኮንትራት ግዢ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር የግዢ ሥርዓቱ ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው መመሪያው እንዲተገበር ከመስራት ባለፈ የግዢ ፈፃሚ ተቋማት ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ነው፡፡

በግዢ ላይ፣ በግዢ ሂደት አፈፃፀም፣ በጨረታዎች ላይ እንዲሁም በውሳኔዎች ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎች አሉ፡፡ ይህን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚሰሩ ሥራዎችን በማጠናከር በተለይ እንዲህ አይነቱን ቅሬታ ለመቅረፍ የኤሌክትሮኒክስ ግዢ ሥርዓቱ ከፍተኛ እገዛ ስለሚያደርግ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራበታል። ይህም ተጫራቾች በግልጽ መስፈርት መወዳደር ስለሚችሉ የቅሬታ መነሻዎችን ዝግ ያደርገዋል። ለዚህ ደግሞ የባለሞያዎችን አቅም ከማጎልበት በሻገር የንግዱ ማህበረሰብ ላይ የግንዛቤ ሥራ መሰራት ስላለበት በትኩረት የምንሰራው ይሆናል፡፡

ንጋት፦ ቀረ የሚሉት ሀሳብ ካለ?

/ ወሰነች፦ ክልላችን በርካታ ሀብቶች ቢኖሩም ያልተዳሰሱና ሥራ ላይ ያልዋሉ ሀብቶች ብዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም የህብረተሰቡን አጠቃላይ የልማት ፍላጎቶች መመለስ እንዲቻል የክልሉን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም የህበረተሰቡን ህይወት እንዲሻሻል በቅንጅት መሥራት አለብን፡፡

በሌላ በኩል በክልላችን በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተሰሩ ሥራዎች በርካታ ናቸው። በተለያዩ ወረዳዎች ድልድዮችና መንገድ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ተሰርቷል፡፡ ይህም ህዝብን በማሳተፍ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚቻል የተረጋገጠበት በመሆኑ ይህን አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡ ከልማቱ ባሻገር በሰላም እና በሌሎች ሥራዎችም ተሳትፎ በማድረግ ላይ ነው፡፡ ይህን ተሳትፎ በተጠናከር መልኩ ማስቀጠል የሁላችንም የቤት ሥራ መሆን አለበት እላለሁ፡፡

ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

/ ወሰነች፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡