ጨረቃ እና ሙዚቃ

ጨረቃ እና ሙዚቃ

በአንዱዓለም ሰለሞን

በሙዚቃ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ይዳሰሳሉ። እነዚህ ነገሮች የሚገለጹበት ሁኔታም እንደየገጣሚው ስሜትና ችሎታ ይለያያል፡፡

በተለይም ደግሞ ፍቅርን መግለጽ፣ ውበትን መሳል፣ ናፍቆትና ትዝታ እንዲሰማን ማድረግ፣ ከረቂቅ ስሜትነታቸው አንጻር የገጣሚያኑን ብእር የሚፈትን ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ እነዚህን ስሜቶች በተፈጥሮ መስሎ ማቅረብ አንድ የተለመደ ነገር ነው፡፡ እዚህ ላይ ደግሞ የጨረቃ ነገር ይነሳል፡፡

ጨረቃ ለገጣሚያን ሌላ ነገር ነች፡፡ የውበት ተምሳሌት፣ የፍቅር ስጦታ፣ የቃል ኪዳን እማኝ፣ መሀላ ማጽኛ ወዘተ በመሆን ልክ እንደተፈጥሮዋ ሁሉ የስንኞች ሀሳብ ድምቀት እየሆነች ተስላለች፡፡

ውበትን ከጨረቃ ጋር በማነጻጸር በመግለጽ ረገድ ከተቋጠሩት ስንኞች ስጀምር በእጅጋየሁ ሽባባው አንድ ሙዚቃ ላይ ያሉ ስንኞችን ማንሳቴ አይቀርም፡-
“ጨረቃ ባትወጣ ደምቃ ባትታይ፣
አንተ ትበቃለህ ለሀገሬ ሰማይ፡፡”
የማዲንጎ አፈወርቅ አንድ ሙዚቃ ላይ ደግሞ እንዲህ የሚሉ ስንኞችን እናገኛለን፡-
“ዐይኖቿ ጸሀይ ጨረቃ፣
ማራኪ ውስጠ ብርሀን”
የሁለቱን ሙዚቃዎች ስንኞች በንጽጽር ስንመለከታቸው፣ በማዲንጎ ሙዚቃ ጨረቃ የአንዲት ሴትን ማራኪ ዐይኖች ውበት ለመግለጽ ስትውል፤ በእጅጋየሁ ሙዚቃ ላይ ደግሞ፣ የሰውዬውን መላ ነገር ወክላለች፡፡ ከዚህ አንጻር፤ በጂጂ ሙዚቃ ውስጥ ያለውን የጨረቃ ውክልና ከግነት ዘይቤም በላይ ሆኖ ሊሰማን ይችላል፡፡
በዚህ ረገድ በነዋይ ደበበ “ጨረቃ” በሚለው ሙዚቃ ስንኞች ላይ የምናየውም ይህን መሰሉን ነገር ነው፡-
“ነሽ የኔ ጨረቃ ዐይኔም አይቶሽ አያበቃ፣
ልቤም ወዶሽ አያበቃ ነሽ የኔ ጨረቃ፡፡
ካገር ከሰፈሩ እኔ አንቺን አብልጬ፣
ዐይንሽን አያለሁ ከሁሉም አብልጬ፡፡”
ወደጌታቸው ጋዲሳ አንድ ሙዚቃ ሳልፍም፣ ጨረቃ በተመሳሳይ መልኩ ምትሀታዊ ውበት እንዲህ ተገልጾባታል፡-
“እንደ ደማቅ ጨረቃ እንደ አጥቢያ ኮከብ ነሽ፣
አንቺንስ ታይቶ ጠፊ አላፊ ባላረገሽ፣
አያልቅበት አምላክ ለናሙና ፈጥሮሽ፣
እንዳላመልክሽ ነው በሰው የመሰለሽ።”
እንዲህ ባለ መልኩ ውበትን ከመግለጽ ባሻገር፣ በሰውኛ ዘይቤ ተጠቅሞ ጨረቃን ማናገርም በተለያዩ ሙዚቃዎች ውስጥ ተስተውሏል፡፡
የአህመድ ተሾመ አንድ ሙዚቃ ላይ፣ የምናገኛት ጨረቃ ሁለት ፍቅረኛሞች ቃል ሲግባቡ እማኝ በመሆን የጠጠቀሰች ናት። አፍቃሪው ቃሏን ያጠፈችውን ፍቅረኛውን ያቺን ጨረቃ እያሰበ እንዲህ የሚወቅስባት፡-
“ማንነበር ተጠቃሽ ምስክር፣
በወቅቱ ፍቅሬ ቃል ስናገር፣
ከጨረቃ በቀር ማንም ሰው አልነበር፣
ትመስክር ትመስክር ጨረቃ ትናገር!”
በሀና ግርማ አንድ ሙዚቃ ላይ ደግሞ፣ጨረቃ የናፍቆት ስሜት ተጋሪ ሆና ተስላለች፡-
“አንቺ ነሽ ጨረቃ የልቤን ምታውቂ፣
ይልቅ ከጎኔ ሁኚ ተይ አትደበቂ፡፡
ፍቅር አስለምደኸኝ ሁሌ ከመሻሸ፣
ድንገት ዛሬ ብትቆይ ልቤ ተረበሸ፡፡
አፋልጊኝ ጨረቃ እስካገኘው ውዴን፣
ብርሀን ሁኚና ምሪኝ በመንገዴ፡፡”
ከጀምበር መጥለቅ በኋላ የቀጠለ ፍቅር፣ ምሽት በጨረቃም ይደምቃል፡፡ ለዚህም ይመስላል፣ ጥላሁን ገሰሰ እንዲህ ሲል ያዜመው፡-
“በምሽት ጨረቃ በንጋት ጸሀይ፣
ህይወታችን ፋፋ በጣም፣
ተፈጥሮን አድንቀን ውበትን ስናይ፡፡
እኔና አንቺ ሆነን ፍቅርን ቀመስናት፣።”
ወደቀጣዩ የቴዎድሮስ ካሳሁን ሙዚቃ ልለፍ፡፡ በዚህ ሙዚቃ ውስጥ ደግሞ ጨረቃ በውበት ተምሳሌትነት ከመገለጽ ባሻገር፣ በዚህ መልኩ ለፍቅር እማኝነት ተጠቅሳለች፡፡
“ምን ቆንጆ ቢኖር ሚደነቅ ውበት
ለኔ ሌላ ነሽ አንቺ እኮ ማለት
የልቤን ሰማይ ጨለማ ሽሮ
ብርሀን በሞላው ልዩ ተፈጥሮ
በዚህ ጨረቃ እምልልሻለሁ
ፍቅሬ እመኝኝ እኔ እወድሻለሁ”