እድሜ ጠገቧ ከተማ

እድሜ ጠገቧ ከተማ

መሐሪ አድነው

እንደ ስሟ የረጋችው፣ ምንጮች የከበቧት ውብ ምድር ናት፡፡ ታሪካዊቷ ከተማ ስሟ ከኢትዮጵያ የአርበኝነት ታሪክ ጋርም ይቆራኛል፡፡ ሠላም የበዛላት ከተማ፡፡ እንደ ስሟ ናት ይርጋለም፡፡

በ1923 የተቆረቆረቺው ይርጋ ዓለም ስትወሳ ታላቁ ሰው ራስ ደስታ ዳምጠው ከፊት ይጠራሉ፡፡ ወይና ደጋ ናት፤ አየሯ ሞቀኝ ብለው አይከፉም፣ በረደኝ ብለው አይጨማደዱም፡፡ ለሁሉ የምትሆን ሁሉን የምትማርክ ከተማ፤ ወደ ታላቁ አቦ ወንሾ ለመሄድ የምታሻገር፡፡ የተፈጥሮ መዲናም ናት፡፡ ወንዞች የከበቧት፣ ምንጮች የሞሉባት። ይርጋ ዓለም አንድ ከተማ ሆና በብዙ ትጠራለች፤ በብዙ ትገለጻለች፡፡

በአምስት አመት የፋሺስት ወረራ እንቢኝ ለሀገሬ ተብሎ ታላቅ የጦር ተጋድሎ ከተደረገባቸው የሀገራችን ጥንታዊ ከተሞች መካከል አንዷ ይርጋለም ከተማ ናት። ከተቆረቆረች ድፍን ዘጠና አራት አመት ሆናት፡፡

በ1928 ጣሊያን ከ40 ዓመታት በኋላ ዳግም መምጣቱን ተከትሎ አለም በተናወጠበት በዚያ ወቅት የጠቅላይ ግዛቱ ገዢ ለነበሩት ራስ ደስታ ዳምጠው የመናገሻ ከተማ ነበረች፡፡

“ጊዜ ያመጣውን ጊዜ እስኪመልሰው ሃገረ ሰላምን ይርጋለም ወረሰው” እንደተባለው፡፡

የቀድሞ የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት መቀመጫ የነበረችው ሃገረ ሰላም፤ የጠላትን ጦር ለመመከት ስትራቴጅክ ቦታ በነበራት ይርጋለም ተተካች ማለት ነው፡፡  የጣሊያን ጦር ለመከላከል የሚያስችል ምቹ ቦታ ላይ መሆኗን የሚያሳይ መሆኑ ነው፡፡ በተቃራኒው ሃገረ ሰላሞች ከተማነቱን ተነጠቅን በማለት ቅሬታቸውን ያቀረቡበት ነው፡፡

ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ማግስት ለጠቅላይ ግዛት መቀመጫነት ከመመረጧ አስቀድሞ የተቆረቆረችው ይርጋለም ስያሜዋን ያገኘችው  በጦርነቱ ሳቢያ ካለመረጋጋቱ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የጠቅላይ ግዛቱ ገዢ ራስ ደስታ ዳምጠው አለም እንድትረጋጋና እንድትሰክን ፣ መናወጡም እንዲያበቃ በመመኘት ከተማዋን ይርጋአለም እንዳሉዋት ይነገራል።

የይርጋዓለም ከተማ በወቅቱ በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ስር ለሚተዳደሩ ስድስት አውራጃዎች የመናገሻ ከተማ በመሆን  አገልግላለች፡፡ ጠቅላይ ግዛቱን ይመሩ የነበሩት ራስ ደስታ ዳምጤው እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስ የደቡቡን አቅጣጫ ይመሩ የነበሩት ቤተ መንግስታቸውን በይርጋለም ከተማ አድርገው ነበር፡፡

በጠቅላይ ግዛቱ ዋና ከተማነት እስከ 1950ዎች የቆየችው ይርጋለም በወቅቱ ከስድስት አውራጃዎች ለሚመጡ የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች ተቀባይ በመሆን በዙሪያዋ ላሉት የእውቀት ማዕከልም ነበረች ያሉን በአንጋፋው የይርጋዓለም ቤተ መጽሃፍት ከአርባ አመታት በላይ ያገለገሉና አሁንም እያገለገሉ የሚገኙት ወይዘሮ መዓዛ አለማየሁ ናቸው፡፡

በተለያዩ የመሰረተ ልማት መስኮች ቀዳሚነቷ ቢነገርም ጦርን ለመከላከል ታሳቢ ያደረገው አቀማመጧ ምቹ አለመሆኑ በተራዋ ከተሜነቷን በሃዋሳ እንደትነጠቅ አድርጓታል።ይርጋዓለም ከሃዋሳ ከተማ በአርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የምትገኘው፡፡

ራስ ደስታ ዳምጠው ከጣሊያን ጋር በተደረገው ጦርነት ህዝባቸውን አስተባብረው ሲታገሉ ተሰው፡፡ ህልፈታቸውን የሰሙት ንጉስ ቀዳማዊ አጼ ሀይለሥላሴ በመናገሻ ከተማቸው ይርገለም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በስማቸው እንዲከፈት አድርገዋል፡፡አሁን ድረስ ይህ ትምህርት ቤት የታሪክ አስረጂ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ፈልገው ለሚመጡ ማዕከል የነበረችው ይርጋለም የተለያየ ቋንቋ፣ ታሪክና ባህል ያላቸውን ተማሪዎች ማስተናገዷ የፈጠረው የእውቀት ሽግግር ለስልጣኔና ጥበብ ቅርብ አድርጓታል፡፡ እናም ይርጋለም ታዋቂ ምሁራንና የጥበብ ሰዎችን አፍርታለች።

በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ከሚገኙት ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል አንዷ የይርጋዓለም ከተማ ስትሆን በተለያዩ ታሪካዊ መስህቦች  የታደለች ከተማ ናት፡፡በውስጧ የራስ ደስታ ዋሻ፣ የልዕልት ተናኘ ወርቅ ዋሻ፣ የጀነራል ባውዛኖ መኖሪያ ቤት ጣሊያን የተጠቀመባቸው የጦር መሳሪያዎች እና ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ይገኙበታል፡፡

ከተፈጥሮ መስህባቸው መካከል የጊዳቦ ፍል ውሃ አገልግሎት ከይርጋዓለም ሆስፒታል በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት በጊዳቦ ዎንዝ አጠገብ የሚገኝ ሲሆን ቦታው ለቱሪስቶችና ለአካባቢው ነዋሪዎች የፍል ውሃ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በስፍራው የሚገኙ እድሜ ጠገብ ዛፎች ለጊዳቦ ፍል ውሃ ልዩ ውበትን ያጎናጽፋሉ፡፡

ከተማዋ እድሜዋን የሚመጥን እድገት ላይ ባለመሆኗ ነዋሪዎቿ ቁጭት ያድርባቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት ወደ ልማት ጎዳና እያመራች የምትገኝ  ከተማ ናት፡፡

አቶ መኮንን ቡዋኔ በይርጋለም ተወልደው ያደጉ የሀገር ሽማግሌ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ራስ ደስታ ዳምጤውን ተከትለው የመጡ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች በይርጋለም ከተማ ይኖራሉ፡፡ ሲዳማም በባህሉ አቃፊ በመሆኑ ሁሉም በየሃይማኖታቸው ተቻችለውና ተከባብረው  በአንድነት ነው እየኖሩ የሚገኙት፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች ለዘመናት ተዘንግታ የከረመችው ይርጋለም አሁን በእድገት ጎዳና ላይ ትገኛለች ይላሉ፡፡ ያረጁ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ተጠግነውና ዋናው የአስፋልት መንገድ  በፌደራል መንግስት ባለ ሁለት መንታ አስፋልት ተደርጎ በመሰራት ላይ በመሆኑ  በጣም ደስተኞች ሆነናል በማለትም ነግረውናል፡፡

ሃምሳለቃ አስፋው ጽጌ እና አቶ አዳነ አውላቸው እንደ ነገሩን የመንገዱ ስራ በተለያዩ ምክንያቶች ተጓትቶ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ስራው ተቀላጥፎ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ የተሸሸገው የከተመዋ ውበትም እየተገለጠ ነው፡፡

እዚህ ለመድረስ ታዲያ ህዝብም መንግስትም ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ይሁን እንጂ ነዋሪው ነገ የተሻለች ከተማ እንደምትሆን በመተማመኑ ለስራው ያሳየው ትብብር የሚደነቅ ነው፡፡

ድብቁ የይርጋ ዓለም ከተማ ውበት ጎልቶ እንደሚወጣ ተስፋ የሰነቁት ነዋሪዎቿ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል፡፡  

አቶ ስማቸው አንጊሶ በይርጋዓለም ከተማ ተወልደው ያደጉና ሰው ናቸው፡፡ እርሳቸውም ይርጋዓም እንደ እድሜ ጠገብነቷ እድገቷ ዘገምተኛ ቢሆንም አሁን ላይ የተጀመረው የልማት እንቅስቃሴና የኮሪደር ልማት እጅግ አስደሳች በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል  ድጋፋችንን እየገለጽን  እንገኛለን ብለዋል፡፡ የከተማው ህዝብ ለፈጣሪም ለመንግስትም ታዛዥ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

በኮሪደር ልማት ከተማዋን ለማስፋት በተያዘው እቅድ መሰረት  በሁለት ክፍለ ከተማና አስራ ሰባት የከተማና ገጠር ቀበሌዎች ተዋቅራ እድገቷ እየተፋጠነ ይገኛል ያሉት ደግሞ የይርጋዓለም ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ታፈሰ ጬኢቾ ናቸው፡፡

የይርጋዓለም ከተማ ከንቲባ አቶ ተረፈ ሙሉነህ እንደገለጹት ሲዳማ ክልል ሆኖ ከወጣ ወዲህ ከተማዋ ከሃዋሳ ቀጥሎ የክልሉ ሁለተኛ ከተማ ሆና ተመርጣ በፈጣን እድገት ላይ ትገኛለች፡፡  ከተማንና ገጠርን የሚያገናኙ የአርባ ሁለት ኪሎ ሜትር መንገድ ከፈታ ስራ የተሰራ ሲሆን  ከአቦስቶ እስከ አራዳ የአስራ አንድ ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ እየተገነባ ይገኛል፡፡ ይህም በሁለት ምዕራፍ የሚሰራ መሆኑን የጠቆሙት ክንቲባው በተለምዶ ስደተኛ ከሚባለው እስከ አራዳ ድረስ ባለሁለት መንታ መንገድ አስፋልት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

ከተማዋ ለሶስት ነገሮች ምቹ ናት የሚሉት ከንቲባዋ፤ አንደኛ የቱሪዝም መዳረሻ ስትሆን የኢንቨስትመንት መዳረሻም ናት፡፡ በሌላ በኩል በከተማ ግብርና ከሚጠቀሱ ከተሞች መካከል ይርጋዓለም ከግምባር ቀደምቶቹ ተርታ ትሰለፋለች፡፡ ከንቲባው ለዚህ እንደ ማሳያ ካነሱት የይርጋዓለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስሪ ፓርክ አንዱ ሲሆን በውስጡ በርካታ ሼዶች የተዘጋጁ በመሆናቸው ልማታዊ ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በይርጋዓለም ቢያፈሱ ከተማዋ ባለ ብዙ ጸጋ ባለቤት ስለሆነች ያተርፉበታል ሲሉ ከንቲባው አቶ ተረፈ ሙሉነህ ጥሪ አቅርበዋል፡፡