ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተሰራ ነው – የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2017 በጀት አመት አፈፃፀም እና የ2018 በጀት አመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የዉይይት መድረክ በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ የሚመለከታቸው የክልል፣ የዞን የልዩ ወረዳና የወረዳ አመራሮች በተገኙበት እያካሄደ ይገኛል።
በእለቱ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ አመርቂ ስራዎች የሚበረታቱ ቢሆኑም ጊዜው ከሚጠብቀዉ እና ማህበረሰቡ ከሚፈልገው የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት አንፃር ብዙ መስራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ክልሉ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ በጤናው ዘርፍ ስርዓት ለመትከል በተደረገው እንቅስቃሴ ውጤት ማስመዝገብ የተቻለ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።
ለዚህም እንደማሳያ ያሉት ቀድሞ የነበረው የወረርሽኝ ክስተት ስፍት እና ጊዜ አንፃር በእጅጉ መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
የላብራቶሪ አገልግልግሎትን በተመለከተ ከፌደራል ጤና ሚኒስቴር እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ሀብት በማሰባሰብ እና በተጠናከረ መልኩ ላብራቶሪው ወደ ተግባር እዲገባ መደረጉ በአዲስ መልክ ለተዋቀረዉ ክልል ከፍተኛ ውጤት ነው ብለዋል።
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና የጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ማሙሽ ሁሴን፤ ኢንስቲትዩቱ ባሳለፍነው አመት የወረርሽኞችን አሰሳ እና ቅኝት ለማጠናከር፣ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ይበልጥ ለማሻሻል እና ከአጎራባች ክልሎች ጋርም ትብብሮችን ለማጎልበት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።
በክልሉ የተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር የአደጋ ቅድመ ዝግጁነትን ማጎልበት አፍጣኝ ምላሾችን መስጠት እንዲሁም የጤና ፍትሀዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ እምርታ አሳይተናል ሲሉም አክለዋል።
ዘጋቢ፡ አልማዝ ቢረጋ
More Stories
በሽታ መከላከልንና አክሞ ማዳን ላይ ትኩረት በማድረግ በድንገተኛ ክስተት ለተጎዱ ወገኖች እና ወረርሽኝ ምላሽ የሚሆን 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ግብአት ተሰራጭቷል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ
ከደም ተዋፅኦ መድኃኒት በማምረት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡ የደም መድኃኒቶችን ለማምረት እየተሰራ ይገኛል – የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት
ዜጎች የራሳቸውን ጤና ማምረት እንዲችሉ የጤና ማጎልበትና የበሽታ መከላከል ሥራ ላይ የሚዲያ ተግባር ላቅ ያለ መሆኑ ተገለጸ