በሽታ መከላከልንና አክሞ ማዳን ላይ ትኩረት በማድረግ በድንገተኛ ክስተት ለተጎዱ ወገኖች እና ወረርሽኝ ምላሽ የሚሆን 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ግብአት ተሰራጭቷል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሽታ መከላከልንና አክሞ ማዳን ላይ ትኩረት በማድረግ በድንገተኛ ክስተት ለተጎዱ ወገኖች እና ወረርሽኝ ምላሽ የሚሆን 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያለውን ግብአት ማሰራጨቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የህክምና አገልግሎት ዘርፍ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ እያካሄደ ይገኛል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የህክምና አገልግሎት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሀኑ እንደገለፁት፤ የማህበረሰቡን ጤና ከማስታጠቅ አኳያ በህክምና ዘርፉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በ5 ጤና ጣቢያዎች በቀዶ ህክምና የማዋለድ አገልግሎት መጀመሩን፤ በቀሪ ቦታዎችም ስራውን ለማስጀመር እንዲረዳ የ4 ወር ስልጠና 13 ጠቅላላ ሐኪሞች እየሰለጠኑ ይገኛሉ ብለዋል።
አቶ ናፍቆት አክለዉም፤ በሆስፒታሎች ጥራት ለጥምረት በ5 መሪ ሆስፒታሎች 26 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችን በማጣመር ከክትትል ባሻገር የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ መደረጉን አንስተዋል።
በበጀት አመቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በተመለከተ የህክምና መሳሪያዎች እጥረት የድጋፍና ክትትል ውስንነት እና የቦርዶች ጠንካራ አለመሆን የሚጠቀሱ መሆናቸውንና በቀጣይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መስራት እንደሚገባም አቶ ናፍቆት አመላክተዋል።
በመድረኩ የተለያዩ ዞኖች የዕቅድ ክንዉን ሪፖርታቸውን ያቀረቡ ሲሆን በድክመትና በጥንካሬ ረገድ የተነሱ ጉዳዮችን ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራም በሪፖርታቸው አንስተዋል።
በመድረኩም ከዞን፣ ከሆስፒታሎች፣ የግል የህክምና ተቋማት እና ጥሪ የተደረገላቸው ተቋማት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ዘጋቢ፡ ስምረት አስማማው – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሣ ወረዳ የሚገኙ አመራሮች ደም በመለገሳቸው በደም እጦት ምክንያት የሚሞቱ ወገኖችን ህይወት በማትረፋቸው መደሰታቸውን አስታወቁ
በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ዙሪያ የሚደረገው ጥንቃቄ በመቀዛቀዙ አሁንም የቫይረሱ ስርጭት እየተስተዋለ መሆኑን ተገለጸ
የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የጤናው ዘርፍ ዕቅድ አፈፃፀም እና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አደረገ