የዕልፍ ውበት መገኛ ሥፍራ
በካሡ ብርሃኑ
ሠላም ጤና ይስጥልኝ ውድ አንባቢያን! እንደምን ከረማችሁ? ከሰሞኑ ከተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ(ዶ/ር) ጋር መወያየታቸው ይታወሳል፡፡
ከውይይታቸው መጠናቀቅ በኋላ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶችንና ታሪካዊ የቱሪስት መደረሻዎችን እንዲጎበኙ የተደረገ ሲሆን፤ የገበታ ለሃገር ፕሮጀክት የተደበቀን የቱሪዝም ሀብት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቁ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ ከጎበኟቸው ሥፍራዎች መካከል የገበታ ለሃገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነው የሃላላ ሎጅ ይገኝበታል። ከጉብኝቱ መልስ በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም ሳይገለጡ የቆዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ታሪካዊ ቅርሶች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ አመንጪነት ተገንብተውና ለምተው ለእይታ መብቃታቸው ወደ ውጪ ሃገር የሚያማትሩ ጎብኚዎች ሃገራቸውን እንዲያዩ ዕድል የፈጠረ ነው፡፡
በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች መጎብኘታቸው ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ተጠቅመው የበለጠ እንዲያስተዋውቁ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን በሰጡት አስተያየት አንስተዋል።
አሁን ላይ በሃገሪቱ ብዙ ያልተገለጡና ያልታወቁ ገጾች መኖራቸውን የተገነዘቡበት ወቅት መሆኑን የተናገሩት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋዬ ማሞ ናቸው፡፡
በጉብኝቱ የተገኙ የዞኑ ዋና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃሃፊ አቶ ወንድሙ ወራቦ በበኩላቸው የንጉሥ ሃላላ የድንጋይ ካቦችን ጨምሮ በርካታ ታሪካዊ ቅርስ ባለቤት የሆነው የዳውሮ ሕዝብ ለዘመናት ሳይታወቅ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ አመንጪነት የለማው ታሪካዊ የንጉሥ ሃላላ ሎጅ አካባቢውን ከማስተዋወቅ ባሻገር የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡ ለበርካታ ዜጎችም ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አያይዘው ጠቅሰዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ በጉብኝቱ ደስተኛ መሆናቸውን በመግለፅ በቀጣይ እነዚህን የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ በመስራት የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ጠቁመዋል፡፡
እኛም በዛሬው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አምድ በኪነ-ጥበበብ ባለሙያዎቹ ስለተጎበኘው የቱሪዝም መዳረሻ በማንሳት የእልፍኙን ውበት ለማስቃኘት እንሞክራለን፡፡ እንደሚታወቀው ሃገራችን ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የቱባ ውበቶች መገለጫ ናት። ፈጣሪ በሰጣት የተፈጥሮ ሀብት የታደለችው ሃገራችን በተለይም በተራሮች፣ በሸለቆዎች፣ በወንዞችና በሐይቆች የተሞላች ናት፡፡
በአንድ በኩል ተፈጥሮ በብዙ ያደላላት፣ ልጆቿም በትጋታቸው በየዘመናቱ ያደመቋት ብትሆንም በሌላ በኩል በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች እንዲሁም በመሰረተ ልማት መጓደል ፀጋዎቿን በአግባቡ ሳታስተዋውቅና ሳትጠቀምበት ቆይታለች፡፡
ከሰባት ዓመታት በፊት የመጣውን ሃገራዊ ለውጥ ተከትሎ መንግስት ለብዝሃ-ኢኮኖሚ በሰጠው ትኩረት ቱሪዝም አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ሆኖ ብቅ ማለቱን ተከትሎ ጸጋዎቿ እየተገለጡ ይገኛሉ፡፡
በዚህም የሃገሪቱን የቱሪዝም አለኝታዎች በአግባቡ መለየትና ማልማት፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መሠረተ-ልማት ማጠናከርና ተጨማሪ አዳዲስ መሠረተ-ልማቶችን መገንባት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ሆነዋል፡፡
በዚህ መነሻ ከተገነቡ ሥፍራዎች መካከል የገበታ ለሃገር አካል የሆነው የኮይሻ ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡ የኮይሻ ፕሮጀክት የብዝሃ-ቱሪዝም ባለቤት ለሆነችው ኢትዮጵያ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው፡፡ የኮይሻ ኢኮ-ቱሪዝም በውስጡ ከያዛቸው በርካታ ሀብቶች መካከል የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ አንዱ ሲሆን በማራኪ ጥብቅ ደን የተሸፈነ ብሔራዊ ፓርክ ነው፡፡
በገበታ ለሃገር በኮይሻ ፕሮጀክት ውስጥ ከለሙ የቱሪዝም መስህቦች አንዱ የሆነው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ለአረንጓዴ ቱሪዝም ሁነኛ ማሳያ የሚሆን የሃገሪቱ ታላቅ የመስህብ ስፍራ ነው፡፡
የመካከለኛው ኦሞ ሸለቆ አረንጓዴያማው ጌጥ ጨበራ ጩርጩራ ወደ 50 የሚጠጉ ከትናንሽ እስከ ትላልቅ ወንዞች መነሻ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ጨምሮ አያሌ የዕፅዋት ብዝሃ ሕይወትን የለበሰ ተፈጥሯዊ ፀጋ ነው፡፡
የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ዝርያው እየተመናመነ የመጣው የአፍሪካ የዝሆን ዝርያን ጨምሮ እንደ ጎሽ፣ ዲፋርሳ፣ ከርከሮ፣ ሳላ እና አጋዘን ያሉ የዱር እንስሳት የሚገኙበት ነው። ፓርኩ በደን ሽፋኑ ይበልጥ ጎልቶ ስሙ የሚነሳ ሲሆን፤ በፓርኩ ውስጥ የሚያቋርጡ በርካታ ወንዞችና አምስት ሃይቆችም ይገኛሉ፡፡
በጉያው ካቀፋቸው ፏፏቴዎች መካከል ባርቦ ፏፏቴ አንዱ ሲሆን የፏፏቴው ድምጽ ለፓርኩ ተጨማሪ ድምቀት መሆኑን ኢዜአ በአንድ ወቅት በዘገባው ማስነበቡ ይታወሳል።
የገበታ ለሃገር አካል በሆነው የኮይሻ ፕሮጀክት፤ ፓርኩን ለመጎብኘት የሚያስችል መሰረተ ልማት በማሟላት የአካባቢውን የቱሪዝም ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ የመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ የፓርኩን ተፈጥሮ ሳይረብሽ ከፓርኩ ውጪ የተከናወነ ሲሆን ይህም ቱሪስቶች ፓርኩን በቀላሉ እንዲጎበኙት ያስቻለ ነው፡፡
ሌላው የኮይሻ ውብት የግልገል ጊቤ ሶስት ግድብ የፈጠረውን ሰው ሰራሽ ሀይቅ ተንተርሶ የሚገኘው ሀላላ ኬላ ነው፡፡ ሀላላ ኬላ በዳውሮ ዞን በኮረብታዎች፣ ሰንሰለታማ ተራራዎችና በግልገል ጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ግድብ የተከበበ ስፍራ ነው፡፡
በዳውሮኛ ቋንቋ “ኬላ” ማለት የድንጋይ ካብ ማለት ሲሆን ሃላላ ኬላ በ1532 ዓ.ም ተጀምሮ በአስር የዳውሮ ነገስታት ለሁለት መቶ ዓመታት የተገነባ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ስያሜውንም ከመጨረሻው ንጉስ ሃላላ ስም ያገኘ ሲሆን ቅርሱ 500 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
ስፍራው ፀጥታ የሰፈነበት፣ የተረጋጋና መንፈስን የሚያድስ እንዲሁም ታሪክ፣ ባህልና መልክዓ ምድርን ማድነቅ ለሚፈልጉ ማረፊያና ማራኪ የቱሪስት መስህብ እንደሆነ ይነገርለታል።
ሀላላ ኬላ ሪዞርት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለማጎልበትና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መዳረሻ ለመክፈት በማሰብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አማካኝነት በ2013 ዓ.ም ይፋ በሆነው የገበታ ለሃገር ፕሮጀክት ስር ከተሰሩ የኮይሻ ቅርንጫፍ ስራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
በርካታ የተፈጥሮ በረከቶች በአንድ ቦታ የሚገኙበት ሀላላ ኬላ፤ ጎብኚዎች የሚመኙት አይነት አካባቢ እንዲሁም የተረጋጋ የአየር ጠባይ ያለው በመሆኑ ተመራጭ እንደሆነ ይነሳል፡፡ ሪዞርቱ የተገነባው ኢትዮጵያ ያሏትን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶች በማጎልበት ማራኪነታቸውንና መስህብነታቸውን በመጨመር እንዲሁም ተደራሽነታቸውን በማስፋት ለእይታ እንዲበቁ ለማድረግ ነው፡፡
በተጨማሪም ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ጎብኚዎች በእንቅስቃሴያቸው ሁሉ እንዲደሰቱና ሰፋ ያለ ቆይታ እንዲኖራቸው ጥሩ እይታን ፈጥሮ አካባቢውን በሚገባ የሚያስተዋውቅ ነው፡፡ የሪዞርቱ ንድፈ ሀሳብ የሃላላ ኬላ ግንብና የአካባቢውን ሕዝብ ታሪክ እንዲሁም የቱሪዝም ሀብትን ከማክበርና ከመጠበቅ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡
‹ቱኩል› በመባል በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የሚታወቀውን ባህላዊ የስነ ሕንጻ አሰራር ጥበብ በመከተል የቤቱ ውስጣዊ ክፍል አየር በደንብ እንዲያገኝ፣ ጣሪያቸው ከፍ ብሎ ተሰርቷል። የሃላላ ኬላ ሪዞርት በሚያዚያ ወር 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ባለሀብቶችና እንግዶች በተገኙበት መመረቁ የሚታወስ ነው፡፡
More Stories
“እየሠራን እዚያው መኖር ከባድ ነው” – ወ/ሮ ዘነበች ደምሴ
“ምንም ቢገጥመኝ ከፈተና እማራለሁ” – ወጣት አሸናፊ ሙሴ
ነጩ ወርቅ