“እየሠራን እዚያው መኖር ከባድ ነው” – ወ/ሮ ዘነበች ደምሴ

በሙናጃ ጃቢር

በሀገራችን የሸክላ ዕደ-ጥበብ ሥራ በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረ ክብር ያለው ሙያ ነው። በሙያው ደግሞ በርካታ ኢትዮጵዊያን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ተሠማርተው ይገኛሉ። የዕደ ጥበብ ሙያ የሀገራችን ቅርስ በመሆኑ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ በማዘመን ጥቅም ማግኘት ይቻላል፡፡

በተለይ ሸክላ ሥራ ላይ ለተሠማሩ ሰዎች የሚኖረው አመለካከት የተዛባ ነው። አመለካከቱ ላይ ግንዛቤ ተፈጥሮ ሳይሸማቀቁ ሠርተው እንዲለወጡ ማበረታታት ያስፈልጋል እያልን ለዛሬ የሀላባ ቁሊቶ ከተማን ስም ያስጠሩ የእጅ ጥበብ ሙያ ባለቤት ልምዳቸውን ልናጋራችሁ ወደናል፡፡

ወ/ሮ ዘነበች ደምሴ ይባላሉ። የሀላባ ጉምዝዬ ሸክላ ሥራ ማህበር መስራች እና ሰብሳቢ ናቸው። ተወልደው ያደጉት ሀላባ ዞን ቁሊቶ ከተማ ነው፡፡

ትምህርታቸውን የመማር ፍላጎት ቢኖራቸውም ከ1ኛ ክፍል በላይ መዝለቅ አልቻሉም፡፡ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወላጅ እናታቸውን የሸክላ ሥራ ማገዝ ጀመሩ፡፡ እናታቸው ምጣድ ሲሠሩ እሳቸው ደግሞ ትናንሽ ጉልቻዎችን እና የጎመን መቀቀያ ድስቶችን ይሠሩ ነበር፡፡

ወ/ሮ ዘነበች የሸክላ ሥራ ከጥንት ከቅድመ አያቶቻቸው የወረሱት ነው፡፡ ይህም ሙያቸው አድጎ ዛሬ ላይ አንቱታን አስገኝቶላቸዋል። እውቀታቸውን ሳይሰስቱ ለሌሎች ማጋራት ችለዋል፡፡ በሸክላ ሥራ ከ20 ዓመታት በላይ ሠርተዋል፡፡

ለሌሎች የሥራ ዕድልም መፍጠር ችለዋል። ምርታቸው ከሀላባ አልፎ በጣም ውብ የሆኑ የሸክላ ሥራ ውጤቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ እያስተዋወቁ ይገኛሉ፡፡ ዛሬ ላይ ከልጅነት የቀሰሙት ልምድ አድጎ ቤተሰብ እያስተዳደሩበት ነው፡፡

“ቀድሞ የሸክላ ሥራን በተናጥል ስንሠራ ብዙም ውጤታማ አልነበርንም፡፡ በማህበር ከተደራጀን በኋላ ውጤታማ መሆን ችለናል። መንግስት የብር ድጋፍ አድርጎልን ሥራችንን በተቀናጀ መልኩ መሥራት ጀመረናል፡፡ ካለን ሙያ በተጨማሪ የዞኑ ሴቶች እና ህፃናት ከክልሉ ውሃ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ ጋራ በመሆን ያዘጋጅውን ሥልጠና ወስደን ልምዳችንን አዳብረናል፡፡

“መጀመሪያ ጀበናና ምጣድ ብቻ ነበር የምንሠራው፡፡ ሥልጠናውን ወስደን ለስራችን አጋዥ የሆነ መሳሪያ በተለምዶ አጠራሩ የዊል (ሸክላ መስሪያ ቁሳቁስ) ድጋፍ ከተደረገለን በኋላ ግን የተለያዩ ቅርፃ ቅርፅ ያላቸው ዕቃዎችን እያመረትን ሥራችንን ማሻሻል ችለናል፡፡

“ዊሉ ጉልበት ይቀንሳል፤ ቅርፁንም ያሳምራል፡፡ ዞኑም ለማህበሩ ትኩረት በመሥጠት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገልን ይገኛል” ያሉት ወ/ሮ ዘነበች በዚህም ሥራቸው ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ገልፀውልናል፡፡

“ምርታችንን ያየ ሁሉ ጥሩ ነው በርቱ ቢለንም ሸማቹ ማህበረሰብ ብዙም አይደለም። በተለይ ሀላባ ላይ ከጀበና ውጭ ሌላውን ምርታችንን አልፎ አልፎ እንጂ ብዙም ደፍሮ የሚገዛ የለም። የገበያ እጥረት አለብን፡፡ አንዳንዴ ባዛሮች ላይ ስንሳተፍ ግን የተሻለ ገበያ እናገኛለን” ብለዋል፡፡

ወ/ሮ ዘነበች በሸክላ ሥራ ውጤታማ እንዲሆኑ የረዳቸው የወሰዷቸው ሥልጠናዎች እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ ሁሉም አይነት ቅርፅ ያላቸውን የሸክላ ውጤቶችን የመሥራት እና የተበላሸውንም መልሶ የመሥራት ብቃት አላቸው፡፡

“የሸክላ ሥራ ምንም የሚወድቅ ነገር የለውም፡፡” ባይ ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት ሀዋሳ ሴራሚክ ማምረቻ ለጉብኝት ሄደው ብዙ ከጥቅም ውጭ የሆኑ ምርቶችን እንደተመለከቱ ገልፀውልናል።

ከፌደራል እስከ ወረዳ ወርደው ተተኪ ለማፍራት እውቀታቸውን አካፍለዋል። “እዚህ ምድር ላይ ዘላለም የሚቆይ ሰው የለም። የያዝነውን እውቀት ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ አለብን” በሚል ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የተለያዩ ሥልጠዎችን ሠጥተዋል፡፡ ሥልጠናውንም ከሰጡ በኋላ ጥሩ ተቀባይነትን አግኝተው ሥልጠናው መሬት ወርዶ በተግባር ለውጥ ማምጣቱን በተጨባጭ ተመልክተዋል።

ወ/ሮ ዘነበች በውብ እጆቻቸው የሚያመርቷቸው ምርቶች በጣም ማራኪ ቢሆኑም ምርቶቹ ዋጋ እንዳላገኙ ይናገራሉ። የሸክላ ሥራ እንደ ልፋቱ አይደለም፡፡ ሲሸጥ ዋጋው በጣም የወረደ ነው፡፡ ገንዘብ ይዞ ከሚቀመጥ ብለው ለነጋዴዎች በዝቅተኛ ዋጋ እንደሚያስረክቡ ነው የሚናገሩት

“የሸክላ ሥራ በኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት የማህበረሰቡ ሀብት የገቢ ማስገኛ ቢሆንም የሚጠበቀውን ለውጥ አላመጣም” ብለዋል፡፡

“አዲስ አበባ ቀጨኔ የሸክላ ሥራ ማዕከል ላይ ሥልጠና የመውሰድ እድል ገጥሞኝ ነበር። ማዕከሉ በመሥሪያ ቁሳቁስ የተደራጀ ነው። የመሥሪያ፣ የማቡክያ፣ የማቃጠያ እንዲሁም የመሸጫ ቦታውም ለብቻ ነው ያለው፤ በጣም ደስ ይላል፡፡ ሳየው በጣም ነው የቀናሁት።

“የእኛ ምንም ያልተመቻቸ ቦታ ነው፡፡ እዛው እየሠራን ነው የምንኖረው፡፡ እዛው እየሠራን መኖር ከባድ ነው፡፡ ልጆቻችን በየጊዜው ነው የሚታመሙት፡፡ በተለይ ጭሱ ለጤና ከባድ ነው፤ ራሱን የቻለ ቦታ ሊኖረው ይገባል፡፡” ሲሉ አጽንኦት በመስጠት ተናግረዋል፡፡

“ሀላባ ላይ እስካሁን ድረስ ከአመለካከት ጋር ተያይዞ ምንም ነገር አልገጠመኝም። በማህበራዊ ኑሯችን እኩል ተሳትፎ እናደርጋለን፡፡ ሀዘንም ሆነ ደስታን እኩል እንጋራለን፡፡ ከሌላ ብሔር ጋርም በጋብቻ ተሣስረናል፡፡ ጋብቻ ፍቅር ነው፡፡ ዋናው ሠርተው ራሳቸውን ማስተዳደራቸው ነው፡፡

“ቻይና የሸክላ ሥራን ትልቅ ቦታ አድርሳዋለች፡፡ ሀገራችን ላይ ግን አመለካከቱ እና የግንዛቤው እጥረት ወደ ኋላ ጎትቶታል። ከሥር ትምህርት ቤቶች ላይ ግንዛቤው ቢፈጠር መልካም ነው፡፡ ከአገራችን አልፎ ለሌላው ዓለም መትረፍ እንችላለን” ብለዋል፡፡

“አንድ ጊዜ ከየክልሉ ለተወጣጡ የሸክላ ሠሪ ባለሙያዎች ሀዋሳ ላይ ሥልጠና ተዘጋጅቶ ነበር። ሥልጠናውን ያዘጋጁት ከጀርመን የመጡ ዜጎች ነበሩ፡፡ የዘርፉ አስተባባሪዎች ነበሩ ሠልጣኞችን ይዘው የመጡት፡፡

“ክልሎቹን መጥቀስ ባልፈልግም ከአመለካከት ጋር ተያይዞ ንግግር ሲደረግ ጥለው የወጡ ነበሩ፡፡ ይህ የሚያሳየው የተማረውም ማህበረሰብ የግንዛቤ እጥረት እንዳለ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

“ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ቢኖር÷ ሥራዎቼ አዲስ አበባ እንሥራ የሸክላ ሥራ ማዕከል ድረስ ተዋውቀዋል፡፡ እዚህም ድረስ መጥተው ሥራዬን አድንቀው ነው የሄዱት፡፡ ብዙ ጊዜ ኤግዚብሽንና ባዛር ሲኖር ያሳትፉናል፡፡ ነገር ግን ትራንስፖርት አይመቻችልንም፡፡ እቃችን በመንገድ ተሰብሮ ያልቃል፡፡ ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የገበያ ትስስር ቢያመቻቹልን መልካም ነው እላለሁ፡፡

“አፈሩን የምናገኘው ብላቴ ወንዝ ላይ ነው። ከዚህ በፊት አለምንም መሳቀቅ እንደልብ ወስደን ነበር የምንጠቀመው፡፡ አሁን ላይ ግን ዙሪያውን የተለያዩ ይዞታዎች ባለቤት የሆኑት አጥረውታል። እንደ ቀድሞ መውሰድ አንችልም። አትውሰዱ ይሉናል፤ ስለዚህ ወደፊት አፈሩን የማግኘት ዕድል የጠበበ ስለሆነ የሚመለከተው አካል ቦታውን እንደ ቅርስ ከልሎ መፍትሄ ቢያበጅልን ጥሩ ነው፡፡

“በአንድ ወቅት ለሥልጠና መቀሌ ሄጄ ነበር። አንዲት እናት ስትናገር ‘እናቴ ለብዙ ዓመታት የሸክላ ሥራ ሥትሠራ ከሰፈር ሰው ውጭ ሥራዋን ማንም አያውቅም ነበር፡፡ አንድ ቀን ታድያ ጋዜጠኞች ጥቆማ ደርሷቸው ሥራዋን አይተው ህዝብ ጋር እንዲደርስ አስተዋውቀውላታል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሥራዋን ህዝብም መንግስትም አይቶ የሚያስፈልጋትን ሁሉ ድጋፍ አድርጎላታል። አሁን ላይ ስመ ጥር ሸክላ ሠሪ ሆናለች፡፡’ ስትል ተናግራለች፡፡ እኛንም የሚዲያው አካል ሥራችንን አይቶ ለህዝብ ቢያስተዋውቅልን መልካም ነው” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ለወ/ሮ ዘነበች ትኩረት ሰጥተን ሙያቸው አድጎ ከሀላባ አልፈው ወደ ውጭ የመላክ አቅም ስላላቸው የራሱ መሥሪያ፣ ማቃጠያ እና መሸጫ ቦታ አመቻችቶ የሚመለከተው አካል ድካማቸውን ቢጋራ የሚል ጥቆማ ማስተላለፍ እንፈልጋለን፡፡

የሸክላ ሥራ ለውጥ እንዲያመጣ መንግስት እንደ ቀጨኔ እንስራ የሸክላ ሥራ ማዕከል የጀመረውን መልካም ሥራ በሌሎች ማህበራትም ላይ አስፋፍቶ ድካማቸውን የሚቀንሱ ማቡክያ ማሽኖች፣ ማቃጠያ ኤሌክትሪክ እና የመሸጫ ሼዶች ቢመቻቹላቸው ደረጃውን የጠበቀ ምርት አምርተው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በመሆን የውጪ ምንዛሪ ጭምር አስገኝተው ኢትዮጵያን በሸክላው ዘርፍ ማስጠራት ይችላሉ እንላለን፡፡